ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Wednesday, July 13, 2011

ከጣይቱ ሆቴል እስከ ጃዝ አምባ

በጥበበሥላሴ ጥጋቡ
Reporter-Amharic Version




በኢትዮጵያ የመጀመርያው ሆቴል በፊት እቴጌ ቆይቶም ጣይቱ ሆቴል የተባለውና የእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን ምረቃ የሚያያዙበት ታሪክ አላቸው፡፡

ጳውሎስ ኞኞ ‹‹አጤ ምኒልክ›› በሚለው መጽሐፉ፣ የመጀመርያ ስለሆነው ሆቴል አጀማመርና በዚያ ጊዜ ኅብረተሰቡ ሆቴልን ለመልመድና በሆቴል ለመመገብ ያሳየውን እንቢተኝነት አስፍሯል፡፡


እቴጌ ጣይቱ እንዲያ በልመናና በብሉልኝ ልምምጥ ዛሬ እንዲሁ በተአምር ተነሥተው አሁን ያለውን የሆቴሉን ሁኔታ ቢያዩ ከመገረም በላይ እንደሚሆንባቸው መገመቱ ለምን አያስብልም፡፡

በተለይ ባለፈው ሳምንት በጣይቱ ሆቴል የሚከፈተውን የጃዝ አምባን ክለብ በጭራሽ አያስቡትም ይሆናል፡፡


የጃዝ ክለቡ የአፍሪካ ጃዝ ሙዚቃ ትምህርት ቤት አካል ሲሆን፣ ለሙዚቃ አፍቃሪው በሳምንቱ ቀናት ሁሉ መድረክ ላይ በባንድ የሚቀርቡ ሙዚቃዎችን ለማስደመጥና እንደ ምግቡ ሁሉ የሙዚቃውንም ማዕድ ለማቋደስ ተሰናድቷል፡፡

ክለቡ በጣይቱ ሆቴል ቦታ ውስጥ ተሰጥቶታል፡፡ 150 ያህል ሰዎችንም የመያዝ አቅም አለው፡፡ ቦታው የዱሮ መልኩን በማይለቅ መልኩ የታደሰ ሲሆን፣ የምንጣፍ ቀለም፣ የወንበሮቹ አቀማመጥ፣ መድረኩ፣ አዲሱ ባር ሁሉ ተመልካቹ የዱሮውን ጊዜ እንዲያስታውስ ለማድረግ እንዲችሉ የታሰበባቸው ይመስላሉ፡፡

ጣይቱ ሆቴል በ1898 ዓ.ም. ሲቋቋም አጀማመሩም የእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያንን ሊመርቅ የመጣው ሕዝብ ምግብና ማረፊያ ስለታጣለት ለዚያ የሚሆነው መላ ሲፈለግ ነበር፡፡ አጤ ምኒልክ የሌሎችን አገሮች ልምድ ሲያጠያይቁ ሆቴል ስለሚባለው ሐሳብ ይሰማሉ፡፡ በ1898 ዓ.ም. የመጀመርያው ሆቴል ‹‹ሆቴል›› በሚል ስያሜ ሥራውን ጀመረ ያም የአሁኑ ጣይቱ ሆቴል ነው፡፡

‹‹በዛን ጊዜ ወጥቶ መብላትም ሆነ ከፍሎ መብላት ነውር ስለነበር ሆቴሉን የሚጠቀምበት ሰው ጠፋ፡፡ በዚህም ምክንያት አጤ ምኒልክ የመጀመርያው የሆቴል ተገልጋይ ሆኑ፡፡ በመጀመርያው ቀን አጤ ምኒልክ መኳንንቱን የጋበዟቸው ሲሆን፣ ያወጡትም 30 ብር ነበር፡፡ እንዲህም እያለ መኳንንቱ ምኒልክን እየጋበዙ ምኒልክም መኳንንቱን እየጋበዙ የሆቴልን ምሥረታ ሀ ብለው ጀመሩት፡፡›› በማለት ጳውሎስ ኞኞ የሆቴሉን አጀማመር ከትቧል፡፡

ከዓመታት በኋላ የሆቴሉ አካባቢና ፒያሳ ሰው የሚውልበት ሥፍራ ሆነ፡፡ በተለይም በአምስቱ ዓመታት የጣሊያን ወረራ ጊዜ የተለያዩ ሆቴሎችና ክለቦች መምጣት ሲጀምሩ በተለምዶ እንደሚታወቀውም ፒያሳ የጆሊዎች መዋያ ሆነ፡፡

በተለይም በ1960ዎቹ የነበሩት ክለቦች እነውቤ በረሀ፣ በዚያን ጊዜ ለነበሩት አርቲስቶች፣ ደራሲዎች፣ ስፖርተኞችና ጥበበኞች ሁሉ መገናኛ ነበር፡፡

ነጋ አስፍሃ፣ የጃዝ አምባ አስተዳዳሪ፣ ፒያሳ አካባቢ ተወልዶ ማደጉ በዚያን ጊዜ የነበረውን ሞቅታና ድምቀት፣ ጭፈራና ዳንኪራ፣ የአራዳዎች መናኸሪያ በነበረችው ፒያሳ እየከመኮመ፣ በትዝታው እየነጎደ እንዲኖር አስችሎታል፡፡

በዚያን ጊዜ የነበሩትም ታዋቂ አርቲስቶች እንደነ ባህታ ገብረ ሕይወት፣ ዓለማየሁ እሸቴና ጌታቸው ካሳ በውርርድ ከዛ ቦታ አይታጡም ነበር ይባላል፡፡ አቶ ነጋም ያኔ የነበረውን ሁኔታ እንደዚህ ገልጾታል፡፡

‹‹እነዚህ ሙዚቀኞች የሙዚቃ ችሎታቸውን ያሻሻሉት ፒያሳ አካባቢ በነበሩት ቤቶች ነው እነ ሲምቢሮ ቬነስ የሚባሉ ክለቦችም ነበሩ፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን ጣይቱ ሆቴል ታዋቂና ስመጥር ሆቴል ነበር፡፡››

የጃዝ አምባ ክለብም ፒያሳ አካባቢ በመጀመርያው ጣይቱ ሆቴል ውስጥ መጀመሩ ፒያሳ የነበራትን ድምቀት ለመመለስ እንዲያስችልና የጥንቱን የሙዚቃና የአሁኑን ሙዚቃ በጃዝ ለማሳየት ነውም ብሏል፡፡

ቦታውን ለማደስ አራት ወራት ያህል የፈጀበት ሲሆን፣ ውስጡንም በዱሮዎቹና በአሁኖቹ ሙዚቀኞች ፎቶ አካቶ አስጊጦታል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ግርማ በየነ፣ ጌታቸው ካሳ፣ አስቴር አወቀ፣ አበጋዝ ሺዎታና ሔኖክ ተመስገን ይገኙበታል፡፡

‹‹በዚህ ክለብ ዱሮ የነበረውን ስሜት ለተመልካቹ ማምጣት እንፈልጋለን፤›› ብሏል፡፡

ክለቡ ሲከፈት የሳምንቱን ቀናት ሁሉ ክፍት ይሆናል፡፡ ዘሪቱ፣ ሙኒት እና ዮርግ የመሳሰሉት ድምፃውያን እንዲሁም የባህል ባንዱ ኢትዮ ከለር፣ የ60ዎቹን ሙዚቃ የሚጫወቱት ኤክስፕረስ ባንድ፣ ጃዝ እና ጃዝን ከሌሎች ሙዚቃዎች ጋር እያቀላቀሉ የሚጫወቱት ኧርባን ቫይብስ፣ አዲስ አኩስቲክ ፕሮጀክት፣ ትሪዮሎጂ እና ጃዝማሪስ እንዲሁም በአር ኤንድ ቢ የሙዚቃ ስልት የሚታወቀው ኬኒ አለን ከ251 ባንድ ጋር ለሰኔ ወር ከተደለደሉት ውስጥ ናቸው፡፡

ምንም እንኳን ቦታው የጃዝ ሙዚቃና ሙዚቀኞች ጐልተው የሚታዩበት ነው ቢባልም፣ አዘጋጆቹ እንደሚናገሩት ሌሎች የሙዚቃ ዓይነቶችም ይደመጡበታል፡፡ ‹‹እስካሁን ድረስ ሁሉም ባንዶች ቦታውን አይተው ወደውታል፡፡ የክለቡም ባለድርሻ አካላትም ሙዚቀኞች ስለሆኑ ክለቡ ውስጥ ይጫወታሉ፡፡ ስለዚህ ሰባት ቀን መሆኑ ይከብዳል ብለን አናስብም፤›› ይላሉ፡፡

አቶ ነጋ እንደሚገልጸው ጐላ ብሎ የሚታይ፣ መልሶ የመገንባት ሥራ እንደተከናወነ ከሚታዩትም ውስጥ ለየት ባለ በሥነ ሕንፃዊ ውበት የተሠራው እናት ሕንፃ፣ አዲስ የተሠሩት ካፍቴሪያዎች፣ ታድሰው አገልግሎት ላይ የዋሉት የዱሮ ሲኒማ ቤቶች ይጠቀሳሉ፡፡

አዘጋጆቹ የክለቡ መከፈት ቦሌ አካባቢን ብቻ አማራጭ ላደረጉ የሙዚቃ ወዳጆች ፊታቸውን ወደ ፒያሳ መለስ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል ብለው ያምናሉ፡፡

‹‹የእኛ ዓላማ በጥሩ ሙዚቃ ተዝናንተው እንዲሔዱና ከዚያም በላይ የዱሮውን ጊዜ አስታውሰው፣ የአሁኑንም አይተው አዲስ ልምድ ይዘው እንዲሔዱ ለማድረግ ነው፡፡››

የቦታውን ታሪካዊ ዳራ ትልቅነት ለማሳየት ፒያሳን እንደገና ወደ ቀድሞ የሙዚቃ መንደርነቱ መመለስ የጃዝ አምባ ዋና ዓላማ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም ቦታውን የጥበብ ማዕከል የማድረግም ዕቅድ አላቸው፡፡

‹‹ይኼ ቦታ ለንግድ ተብሎ ብቻ የተቋቋመ ቦታ አይደለም፡፡›› የሚሉት የክለቡ ኃላፊዎች፣ ለተለያዩ የጥበባዊ ውጤቶች ለግጥም፣ አዲስ መጽሐፍ ሲመረቅ ወይም አዲስ ሲዲ ሲወጣ፣ አዳዲስ ለሚመጡ አርቲስቶች ያገለግላል ብለውም ያምናሉ፡፡

በየወሩ አዳዲስ ፕሮግራሞች የሚወጡ ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ ታዋቂዎቹ የዱሮ ዘፋኞችም በዚህ ቦታ ላይ እንዲዘፍኑ ጥርጊያው ተመቻችቷል፡፡

ክለቡ ለኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ብቻ የተተወ ሳይሆን፣ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ እንዲሁም ከሌሎች አፍሪካ አገሮች የሚመጡ አርቲስቶች መታደሚያም ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

‹‹ከሙዚቃ በተጨማሪ የጃዝ ሴሚናሮች እና ወርክሾፖች ይኖራሉ፡፡ ታዋቂ ዘፋኞችን ማስመጣት እንፈልጋለን፡፡ ማንኛውም ሰው መጥቶ ፒያሳ አካባቢ ተዝናንቶ በሙዚቃችን የማይረሳ ጊዜ አሳልፎ እንዲሔድ እንፈልጋለን፤›› በማለት ነጋ ገለጻውን ያጠቃልላል፡፡

No comments:

Post a Comment