ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Tuesday, June 19, 2012

ይድረስ በአባቶቻችን ላይ የስደብና የማዋረድ ዘመቻ ለከፈታችሁ ብሎጎች፡-

‹‹ደፋሮችና ኩሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም፣ ዳሩ ግን መላእክት በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ በጌታ ፊት በእነርሱ ዘንድ የስድብን ፍርድ አያመጡም…፡፡›› ፪ጴጥ ፪፣፲፩፡፡

ፀሐፊ፡ ፍቅር ለይኩን፡፡
********************************************************************

       አባቶችን ማዋረድ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር ማዋረድ ህልውናዋንስ መዳፈር እንደሆነ አታውቁምን…?!

መንፈሳዊ ድባብ ያላቸው የሚመስሉና ግን መንፈሳዊ ወዝና ሽታን የተራቆቱ በቤተ ክርስቲያን ስም በተከፈቱ መጦመሪያ መድረኮችና ድረ-ገጾች ዛሬ በእኛ ዘመን በአባቶች ላይ እየወረደው ያለው ስድብና እርግማን፣ እየተገለጸ ያለው ገመና ጆሮን ጭው የሚያደርግ ነው፡፡ እንዲህ የቤተ ክርስቲያኒቱን ገበና ለአደባባይ በማብቃትስ የሚገኘው ትርፍና ጥቅም ምንድን ነው? እባካችሁ ቆም ብለን እናስብ፣ እናስተውል እንጂ ወገን፡፡ ምን ዓይነት ድፍረት ምን ዓይነት ዝቅጠት ነው ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የተባሉትን ሊቀ ጳጳስ- የአንተ ያለህ…! ‹‹ቀውስ እና ጦስ›› ናቸው ብሎ መጻፍና ማዋረድ፤ ሰውን ያህል ክቡር ፍጥረት ብፁዕ አቡነ አብርሃምን ‹‹የጉድ ሙዳይ›› በማለት የመንፈሳዊነቱ ክብር ቢቀር ከሰብአዊ ክብር ማውረድ፣ ይህ በምንም ዓይነት መለኪያ፣ በምንም ዓይነት መንገድ ክርስቲያናዊነት ሊባል ይችላል፣ በምንስ መስፈርት ሞራላዊና ግብረ ገብነት ሊሆን ይችላል???
ምንም ከክርስቲያናዊ ጨዋነትና ግብረ ገብነት ብትፋቱም ይሄ አካሄዳችሁ ሕግ ወጥ እንደሆነ አስባችሁበት ታውቁ ይሆን?! እንዴት በቤተ ክርስቲያን ስም  ብሎግ ከፍቶ እንዲህ ዓይነቱ ተራና ወራዳ ሥራ ውስጥ ይገባል፡፡ አባቶችን ለማዋረድ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብርና ህልውና ለመድፍር ይህን መብት የሰጣችሁ ማነው? እናንተን በፍርድ ወንበር ላይ እንደትቀመጡ ያደረጋችሁስ ማነው? እናም እባካችሁ ምን እየሰራችሁና እያደረጋችሁ እንዳለ ቆም ብላችሁ ብታስቡ ደግ ነው እንላለን፡፡ ወይ ስማችሁ ከግብራችሁ ጋር ይስማማ አለበለዚያ ደግሞ ስማችሁን ቀይሩ፡፡
‹‹ሊቀ መልአክ ሚካኤል ከዲያቢሎስ ጋር ስለ ሙሴ ሥጋ በተከራከረ ጊዜ እንኳን ሚካኤል ዲያብሎስን የስድብ ቃል ሊናገረው አልደፈረም እግዚአብሔር ይገስጽህ አለው…፡፡›› እንጂ ነው የሚለን ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ፡፡ ታዲያ ቅዱሱ መልአክ የስድብንና የፍርድን ቃል ለመናገር ካልደፈረ እኛ ማን ነን በአባቶቻችን ላይ እንዲህ ዓይነቱን ለጆሮ የሚቀፍና የሚዘገንን ስድብና የድፍረት ቃል ለመናገር፣ ደግሞስ እንዲህ ዓይነቱን የፍርድ ቃል ለማስተላለፍ ማን መብት ሰጠን፡፡ የአንዳንዶች ድፍረት፣ እርግማንና ክስ ከራሱ ከክፋት አባትና ከጽኑ ከሳሽ ከጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ የማይተናነስና የሚልቅ ነው የሚመስለው፡፡
ለገባንበት መንፈሳዊ ክስረት፣ ውድቀትና ድቀት እርስ በርስ መካሰሱ፣ ማዋረዱና መዘላለፉ እንዲያም ሲል መረጋገሙና መወጋገዙ በምንም መንገድ የምንፈልገውን መፍትሔ ይዞልን ሊመጣ ይችላል፡፡  ይኸው ስንት ዘመናችን እርስ በርሳችን ስንፈራረድና ስንካሰስ ግን አሁንም መፍትሔያችን የሰማይ ያህል የራቀን ነው የሚመስለው፡፡ እናም እባካችሁ እንደ ባለአእምሮ እያሰብን እንደ ሰው እንስራ እንጂ፡፡
በመንፈሳዊነት ሽፋን በቤተ ክርስቲያን ስም የክፋት አንደበታቸውንና እኩይ ትንታግ የሆነ ብዕራቸውን ለዘረጉ ሰዎች ከዚህ ክፋታቻውና አመጻቸው ይመለሱ ዘንድ እባካችሁ ተመለሱ፣ አስተውሉ ልንላቸው እንወዳለን፡፡ የገዛ አባትን፣ ወንድምንና እህትን በማዋረድ ምን ትርፍ ይገኛል? ከእርግማን በስተቀር፣ ክርስቲያን ከሆናችሁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ከሆናችሁ እንዲህ ዓይነቱንስ ዓይን ያወጣ ድፍረት ከየት ነው ያገኛችሁት፣ ከየትስ ነው የተማራችሁት? ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል፡፡›› ነው የሚለው፡፡ ምናለ ባልተረጋገጠና ባልተጨበጠ መረጃ ደግሞስ እንደው በአባቶቻችን ላይ የምንሰማው ገመና ሆኖስ ቢሆን የክርስትና ወግና ስርዓቱ እንዲህ ነው እንዴ…?! እንዴት እንደ ካም የአባቶቻችንን ገመና በመሸፈን ፈንታ በመግለጽ እርግማንና መዓትን በገዛ ፈቃዳችን ወደራሳችን እንጋብዛለን፡፡
እንደው የሆነውስ ሁሉ ሆኖ የአባቶቻችንንና የወንድሞቻችንን በደል፣ ኃጢአትና ገመና በፍቅር መሸፈን ቢያቅተንና ወደዛ የከበረ ታላቅ የመንፈስ ልእልና ላይ ካልደረስን ምናለ ዝም ማለት ማንን ገደለ፡፡ እንዴት በነጋ ጠባ አባቶቻችንና ወንድሞቻችን በማብጠልጠልና ኃጢአታቸውን በመግለጽ ሰው ከመሆን ክብር ራሳቸሁን ዝቅ ታደርጋላቸሁ የሌሎችንስ ኅሊና ለምን ታቆሽሻላችሁ፣ ታቆስላላችሁ…?
እንዴትስ በስማ በለው በአያችሁትም ባላያችሁትም እየገባችሁ አባቶቻችንና ወንድሞቻችንን ሰድቦ ለሰዳቢ በመስጠትና በሌሎች ድካም ላይ በመፍረድ ወደር የሌለውን ግብዝነታችሁንና ፈሪሳዊነታችሁን እንዲህ በአደባባይ ለመግለጽ ትሸቀዳደማላችሁ፡፡ ይህ በእውነቱ በእጅጉ የሚያሳዝንና ከዓለማውያን ከምንላቸው ሰዎች እንኳን የማይጠበቅ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱንስ ጹሑፍ በብሎጎቻችሁና በድረ ገጾቻችሁ የምታስተናግዱ ሰዎች መንፈሳዊነቱ ቢቀር ከክርስቲያናዊ ጨዋነት ብትሰደዱ እንደው ሰብአዊ/ሰው የመሆን ክብርና መብት ምን እንደሆነ አታውቁም ማለት ነው እንዴ… እናም እባካችሁ እንደ ባለ አእምሮ እናስብ እንደ ባለ ኅሊና እንደ ሰው እንስራ እንጂ ወገን!!! እንዴት ያለ ነገር ነው እባካችሁ…!!!

ሰላም! ሻሎም!

እግዚአብሔር አጥራረ ቤተ ክርስቲያንን ያስታግስልን!!!


3 comments:

  1. ከባድ ነው የዋልድባ የተሰበሰቡትን ጳጳስ ሰምተሀል መቼስ አንድ አባት ፍርሃትን ካልጣረ እውነተኛ መፍትሄ ካልሰጠ ለነፍሱ ካላደረ በሃይማኖት ስም ቀንበር ህዝቡ ላይ መጫን ከባድ ዘለፋውን መደገፌ አይደለም ግን መፍትሄውንም አብረክ መጠቆም አለብህ አንተ እንዳልከው ዝምታ መፍትሄ ይሆናል ብዬ አልገምትም።እግዚሄር ይባርክ።

    ReplyDelete
  2. መሳደብም መፍትሔ አይሆንም መፀለይ እንጂ፤ እነሱ ዓላማቸው ቤተክርስትያንን ቢችሉ ማፍረስ ነው አይችሉም እንጂ ከዝንብ ማር አይጠበቅም ያው ቆሻሻ ነው፡፡ ለእነሱ ማስተዋልን ለኛም የጸሎት ህይወትን እግዚአብሔር ይስጠን፡፡አሜን

    ReplyDelete
  3. true our Ethiopian Father and Mother thinking. that is the truth and that is the spritualitiy. God bless you
    Keep it up !
    From Sweden

    ReplyDelete