ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Monday, August 6, 2012

አደራ ኢትዮጵያን ፡ ለስም ሳይሆን ለባንዲራ ሩጡ



የለንደን ኦሎምፒክ ከተጀመረ ቀናቶች ተቆጥረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በቦታው ተገኝተዋል፡፡ ዛሬ ላተኩር የፈለኩት ሀገራዊ ግዴታ በሚለው ላይ ነው፡፡ 

      እስቲ ከመክፈቻው ልጀምር በዚህ ውድድር ላይ የመጀመሪያው ጥያቄ  የመክፈቻው  ስነ-ስርዓት ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ለዓለም የቀረቡት ጥቂት ሰዎች ላይ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች እራሳቸውን በታሪክ መዝገብ ላይ ማስፈራቸው ዕድለኛ ያስብላቸዋል፡፡ ለነገሩ ካልተሳሳትኩ ሁሌም የሚታዩት እነዚሁ ናቸው፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ መነሳት አለበት ብዬ የማምነው በእንደዚህ ዓይነት የመክፈቻ በዓል ላይ ሁሉም አትሌትና አብረው የተጓዙ አካላት በሙሉ የዚህ ክብር ፣ ታሪክ ተቋዳሽ መሆን አለባቸው ብዬ ነው፡፡  ምክንያቱም በደንብ ካሰብነው በስነ-ስርዓቱ ላይ መሳተፍ በራሱ ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ በዋነኛነት ግን በእንዲህ ዓይነት የመክፈቻው  ስነ-ስርዓት ላይ አዳዲሶቹን ልጆቻችንን ማሳተፍ በራሱ የሚያመጣው የአሸናፊነት ስነልቦና በተጨማሪም የማሸነፍ ተነሳሽነትን መጨመሩ ነው፡፡
ብዙዎቹ ወጣቶች እንደመሆናቸው ይህን የመሰለ ማራኪና ታሪካዊ፤ ውበቱን የጠበቀ አንዳች ስሜትን ከውስጥ ፈንቅሎ የህልም ዓለም ውስጥ የሚከት የኦሎምፒክ ስሜትን ያሟላ ዝግጅት ውስጥ እራሳቸውን  ማግኘታቸው እጅግ አስደሳች ነው ለነሱ፤ ይህ ደግሞ ይጠቅመናል፡፡ በዛ ላይ ሁሉም ተወዳዳሪ ሀገሩን ወክሎ በደስታና በጩኸት የሚያደርጉትን ሲያጡ ማየትም እንዲሁ የሚፈጥረው ብርታትና ተነሳሽነት ትልቅ ሊባል የሚችል ነው፡፡
እዚህ ላይ በገንዘብ ችግር ይሁን በሌላ በማላውቀው ሌላ ምክንያት (የገንዘብ ችግር ነው ብዬ በግሌ አላምንም ) በጣት የሚቆጠሩ ተወካዮቻችን ብቻ ነው  ያየነው፡፡ ሁሉንም ባይሆን እንኳን የተሰወሰኑትን ብናይ ጥሩ ነበር ግን አልተቻለም፡፡ ለምን ተብሎ መጠየቅ ግን ተገቢና ልክ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ያሉንን ታዳጊ ወጣት ልጆቻችንን ‹‹. .  .አይዟችሁ በርቱ. . . . የአበበ ቢቂላ ሀገር. . . . አረንጓዴ ጎርፍ. . . .ሁሌም አሸናፊዎች ነን. . . . ››  በሚሉና በመሳሰሉት ማነሳሻዎች  ከሚደረጉ ጥረቶች በተጨማሪ የመክፈቻ ዝግጅት ላይ መገኘትም የሚያመጣው የራሱ ግፊት አለ፡፡ ይህንን በመጠቀም የማሸነፍ ፍላጎትን በልጆቻችን ላይ ማስረፅም  መጫንም እንችላለን፡፡ 46 ሚሊዮን ብር የተሰበሰበው  አትሌቶችችን አዲስ አበባ ሲገቡ ለመደገሻ  ወ
ይም ለሌላ አላማ ማዋያ ሣይሆን ለእንደዚህ ዓይነት ስራዎች ሆኖ ቢሆን እንዴት መልካም ነበር፡፡ በአራት ዓመት አንዴ ለሚዘጋጅ ውድድርማ ስለአቅም ማጣት ማውራት ያስቃል፡፡
በተጨማሪ አትሌቶች ሳይሄዱ ዶክተሮች ወይም የስራ አመራሮች ቢሄዱ ብዙም ጥቅሙ ያን ያህል ነው፡፡ ይህን በዚህ ሳበቃ ሌላው የገረመኝ ሰማንያ( 80) ሚሊዮን ህዝብን መወከልን የሚያበስረውን ባንዲራችንን በአንዲት ቆንጆ ልጅ(ያኔት ስዩም) ተይዞ ማየቴ  ነው፡፡  ኢትዮጵያውያን እራሳቸው በውል(በደንብ) እንኳን የማያውቋት ልጅ ይህን ዕድል ማግኘቷ አስገራሚ ነው፡፡ ይህ በራሱ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ልጅቷ አዲስም ብትሆን ወጣትም ብትሆን ለሷ ያለኝ አክብሮት እንዳለ ሆኖ ነገርግን ትልቁን ባንዲራችንን ግን በእንዲህ ያለ መድረክ ላይ የመያዝ አቅሙም ብቃቱም አላት ብዬ አላምንም፡፡ ከላይ እንዳልኩት የአሸናፊነት ስነልቦና  የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡
መላው ዓለም የኢትዮጵያን ቡድንን ለመመልከት በሚጓጓ ጊዜ እኛ ልናደርግ የሚገባው ይህንን ስሜታቸውን ከፍ የሚያደርግ ካስፈለገም ፍርሀትን፣ ለማሸነፍ እንደመጣን ማሳየት ነው እንጂ የሚገባን መጥተናል ዓይነት ነገር ሊሆን አይገባም፡፡ እስቲ የሌሎቹን ሀገራት ተወካዮች ተመልከቱ እጅግ ብዙ ሆነው በመታየታቸውም በላይ ሰንደቅ ዓላማቸውን ያስያዙት በታዋቂ በሆኑ እንዲሁም ሀገራቸውን ብዙ ጊዜ ባስጠሩ ጀግኖቻቸው ነው፡፡ እርግጥ ነው አንዳንድ ሀገራት በወጣቶቻቸው አስይዘዋል፡፡ እነዚህ ሀገራት ግን ከኛ የሚለዩት አብዛኛውን  የቡድናቸውን አባላት
በመክፈቻው  ስነ-ስርዓት ላይ አሳትፈዋል ፡፡ ይህን ያደረጉት በለንደን የሆነ ነገር ለመፍጠርና ታሪክ ለመስራት መምጣታቸውንና ዝግጁነታቸውን ለማሳየት ነው፡፡ በኋላ ላይ ያሸንፉ አያሸንፉ ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ እዚህ ላይ እኛም ግር ብለን መሄድ አለብን ለማለት አይደለም፡፡  ስድስት እና ሰባት ሰው ልኮ ዕድሉን እንደቀለድ ለምን እናልፈዋለን ነው፡፡  ለምን ቀነኒሳ በቀለ ባንዲራውን አይዝም?! ኢትዮጵያን ያኮራ ነው ጀግና ነው. . . .  . ለምንስ መሰረት ደፋር ባንዲራውን አትይዝም?!. . .  . ጥሩነሽም ባንዲራውን ለመያዝ ከበቂ በላይ ነች፡፡. . . እጅግ የበዙ ብቁ የሆኑ ሰዎች አሉን፡፡ እነዚህ ጀግኖች ለባንዲራው ከፍ ማለት ብዙ ለፍተዋልና ባንዲራችንን ይዘው ቡድናችንን ቢመሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ  ደስ ይለው ይሆናል እንጂ የሚከፋ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡

እዚህ ላይ ለምን እነሱ አልያዙትም ተብሎ ቢጠየቅ  የረባ መልስ ወይም ምክንያት ይኖራቸው ይሆን? አላውቅም፡፡  ግን ሁሉን ለምን አቅልለን እንደምናይ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ በስራቸው ምክንያት ወይም በሙያቸው ይህንን ሀገራዊ ግዴታ የተቀበሉት ግለሰቦችም እናት ሀገራቸውን ‹‹ ኢትዮጵያ ››ን በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ማሳወቅ እንዲሁም አሸናፊ ማድረግ ሲገባቸው  ውድድሩን ብቻ በማሰብ እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎችን ማባከን አይገባቸውም ነበር፡፡ መሄድ የሚገባቸው ሳይሄዱ የስራ አመራሮች ሄደው እራሳቸውንም ባያስተዋውቁ ጥሩ ነው፡፡ እንደው የምለው ከገባችሁና ካመናችሁበት በሚቀጥለው ኦሎምፒክ ይህን ነገር አ እሻሽላችሁ ለማየት እፈልጋለሁ፤አደራም እላለሁ ፡፡ አምላክ የዛ ሰው ይበለን፡፡

ወደ ሌላኛው ያስገረመኝና በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ወዳልተለመደው ጉዳይ ስገባ በብሔራዊ ቤተ-መንግስት የሽኝት ስነ-ስርዓት ሲደረግ ምሽት ላይ ዜናውን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ETV) ሳይ ያሳቀኝ የአንዷ አትሌት አስተያየት ነው፡፡
‹‹. . . . ስሜንና ሀገሬን ለማስጠራት ነው የምሮጠው. . . ›› ነበር ያለችው በወቅቱ፡፡ እንግዲህ እንዲህ ዓይነት ሯጮች ናቸው ኢትዮጵያን የሚወክሉት፡፡ የቀድሞዎቹ ስለራሳቸው ለማውራት እንኳን ይፈሩ ነበር፡፡ ለውጡ ግሩም ቢሆንም ነገር ግን ለስማቸው መሮጥ ያለባቸው እዚህ አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄ ሀገራዊ ትርጉሙ ከፍ ያለ ውድድር ነው፡፡ ካስፈለገ ለስማቸው ‹‹ ዱባይ ›› ይሩጡ. . .  . ለክብራቸው ኒውዮርክ ይሩጡ. . . .  ሌላም ቦታ መሮጥ ይችላሉ፡፡ እንግዲህ እንዲህ ያለ ፍላጎት የያዙ አትሌቶችን ይዞ አሸንፋለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡ ለስሙ የሚሮጥ ለቡድን ስራ፣ ለመተባበር ፣ ለመተጋገዝ ፍቃደኛ ነው ብዬ አላስብም፡፡ እርግጥ ነው አትሌቷ ልታሸንፍ ትችል ይሆናል ፤ ስሟንም ልታስጠራ ትችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የህዝብ ፍቅርን ማግኘት ክበሬታን ከሀገር ልጅ ማግኘት ይከብዳታል፡፡ በፍቅርና በመተጋገዝ እንጂ የሀገር ስም የሚጠራው ለብቻ ለስም ስለተሮጠ አይደለም፡፡ ቢጠራም ጨው ጨው ነው የሚለው፡፡
ኢትዮጵያውያን የምንታወቀው በቡድን ስራ እና እርስ በራስ ባለን ፍቅርና አክብሮት ነው፡፡ ይኸውም እሰከ ዛሬ እንደተከበርን አቆይቶናል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ እራስ ወዳድነት፣ፀብና ጥላቻ እየተንሰራፋ አንድ አለን ብለው የምንኮራበትን አትሌቲክሳችንን እየጎዳብን ነው፡፡ ነገር ግን ሀገር ሀገር ነው፣ ተባብሮ መስራት ጥሩ አክብሮትን ያመጣ ይሆን እንጂ ጉዳት አያመጣም፡፡በዛ ላይ የህዝብንና የሀገርን አደራ መሸከም ክብር ከመሆኑም በላይ እድለኛም መሆን ነው፡፡   እንደኔ እንደኔ ለዚህ ግዳጅ የሚመጥኑት ሠዓት ያሟሉና የሚያሟሉ ብቻ ሳይሆኑ ለሀገራቸው ስምና ክብር የሚደክሙ፣ ለባንዲራቸው ፍቅር መስዋዕት ለመሆን የተዘጋጁት ቢሆኑ ድላችን ዘላቂነት ይኖራዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከላይ ያልኩትም ባንዲራችንን መሸከም ያለባቸው ፣ ሀገራዊ ግዴታቸውን ፣ ትልቅነታችንን፣ ጀግናነታችንን የሚያሳዩ አሸናፊዎች የሆኑ የበረቱ እንጂ ዛሬ አዋርደው ነገ ያቆሙናል በሚባሉ ወጣቶች መሆን የለበትም፡፡


ኢትዮጵያ የብዙ ጀግኖች ሀገር ናት


ድል ለኢትዮጵያ!

1 comment:

  1. You are right. i appreciat you.
    vi är stolta " we are proud"
    Good job

    ReplyDelete