ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Saturday, October 24, 2015

የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክ ከአራት ሺሕ ዓመታት የሚያዘልለው ግኝት

 በ ሔኖክ ያሬድ


ጥንታዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሳ ‹‹የሦስት ሺሕ ዓመት››
የሚለው ጎልቶ ይሰማል፡፡ የሥልጣኔው መንደርደሪያ ከአክሱም
ዘመን ሲያልፍም የይሓ እና የደአማት ሥርወ መንግሥትም
ይጠቀሳሉ፡

ከሦስት ሺሕ ዘመን ጋርም የንግሥተ ሳባና የልጇ ቀዳማዊ ምኒልክ ታሪክ
ይነሳል፡፡ በምሥራቅ ትግራይ የቀድሞው ዓጋመ አውራጃ ዋና ከተማ
ዓዲግራት በሰሜን አቅጣጫ 8 ኪሎ ሜትር ተሂዶ የሚገኘው የጉለ
መኸዳ ወረዳ ከቀዳሚቷ ንግሥት ጋር የሚያያዝ ታሪክ አለው፡፡ ንግሥቲቱ
በኢትዮጵያ ታሪክ ሦስት ዓይነት ስም ሳባ፣ ማክዳ እና አዜብ አላት፡፡
የወረዳው መጠሪያ ‹‹ጉለ መኸዳ›› ከማክዳ ጋር ሲያያዝ ‹‹ጉለ›› (ጐል)
የሚለው ቃልም በረት የሚል ትርጉም እንዳለው ይነገራል፡፡ ከሳባ ጋር
የተያያዘው ስምም ሶበያ በሚባል የሚጠራውና በወረዳው ውስጥ
የሚገኘው ጥንታዊ ስፍራ ነው፡፡

ከ43 ዓመት በፊት በጉለ መኸዳ አካባቢ ጥናት ያደረገው ፈረንሣዊው
አንፍረይ፣ ባገኛቸው መረጃዎች መሠረት ከሦስት ሺሕ ዓመት በፊት
አካባቢው ሰዎች ይኖሩበት እንደነበር ገልጿል፡፡
በቀጣይ ጥናትና ምርምር የሚደገፍ ቢሆንም ንግሥተ ሳባ በዚህ አካባቢ
ትኖር እንደነበረ ለመረዳት አያዳግትም ይላሉ የአካባቢው ነዋሪዎች፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጉሎ መኸዳ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ሥልጣኔ
የሚያመለክቱ በርካታ ቅርሶች እየተገኙበት ነው፡፡ የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ
ሌክቸረሩ አቶ ሐጎስ ገብረማርያም እንደሚገልጹት፣ ከ10 ዓመት በፊት
የጉለ መኸዳን ኦርኪዮሎጂካዊ ሀብቶችም ሕቡዕ ምሥጢር አስመልክቶ
ለሁለት ዓመት ዳሰሳና ጥናት ተካሂዶ ነበር፡፡



ጥናቱ የምሥራቅ ትግራይ አርኪኦሎጂ ፕሮጀክት የሚባል ሲሆን፣
መቀመጫውን በካናዳ ባደረገው ሳይመን ፍሬሰር ዩኒቨርሲቲ የሚደገፍና
በዩኒቨርሲቲው የአርኪዮሎጂ ፕሮፌሰር ካትሪን ዲአንድሪያ የሚመራ
ነው፡፡ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በመስቀል በዓል አጋጣሚ ባዘጋጀው
ሁለተኛው የአርኪዮሎጂ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የጉለ መኸዳ አዳዲስ
ግኝቶችን የተመለከተ ጥናት በፕሮፌሰሯ ቀርቦ ነበር፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ካትሪን ማብራሪያ የሁለት ዓመቱ ዳሰሳዊ ጥናት
ከተጠናቀቀ በኋላ በቀጥታ የተገባው ወደ ቁፋሮ ነበር፡፡ የመጀመሪያው
ቁፋሮ የተካሄደበት ቦታ የተመረጠው መዝበር ከአክሱም ሥልጣኔ በፊት
የነበረን ከተማ የሚያመላክት ፍርስራሽ ሕንፃ ስለተገኘበት ነው፡፡ ይህም
ከተማ ከክርስቶስ ልደት በፊት 800 ዓመት ላይ የነበረ መሆኑ
ተረጋግጧል፡፡ ሁለተኛው ቁፋሮ የተካሄደበት ቦታ ዖና ዓዲ የሚባልና
በሸዊት ለምለም ቀበሌ መነበይቲ መንደር የሚገኝ ነው፡፡
መነበይቲን ከመዝበር የሚለየው ከአክሱም ሥልጣኔ በፊትና በዘመነ
አክሱም መካከል መኖሩ ነው፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ካትሪን ማብራሪያ
መዝበር ጥንታዊ ማዕከል ሲሆን፣ መነበይቲና አካባቢው ደግሞ
ከአክሱም ሥልጣኔ ጋር የሚያመሳስለው ቅሪቶችን ይዞ መገኘቱ ነው፡፡
በዋናነት በመዝበር የተካሄደው ጥናት እጅግ ጥንታዊና በጊዜው
የነበረውን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊን ይዞታ ምን
ይመስል እንደነበር ምላሽ የሚሰጥ ነው፡፡

መዝበር

      በጻሕዋ አካባቢ የሚገኝና ለአምስት ዓመት ያህል ቁፋሮ የተካሄደበት
ስፍራ ነው፡፡ ግኝቱም የሚያሳየው በአክሱም ሥልጣኔ በፊት ከክርስቶስ
ልደት 1000 – 1500 ዓመት በፊት ታላቅ ማዕከል ሆኖ መኖሩ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ትልቅ ቦታ ካለው ከይሓም ከ400 እስከ 450 ዓመት በፊት
እንደሚቀድም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በመዝበር ረዥም ዕድሜ
ያስቆጠረ ሥልጣኔ እንደነበረም ተረጋግጧል፡፡ ይህም ከደቡብ ዓረቢያ
የፈለሱ ሰዎች ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት የነበረ
ሥልጣኔ መሆኑን መረጋገጡን ፕሮፌሰር ካትሪን ገልጸዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰሯ አገላለጽ፣ ቀደም ሲል የአርኪዮሎጂ ተመራማሪዎች
ጥንታዊ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ መነሻን ከዓረብ ከፈለሱ ሰዎች ጋር የተያያዘ
ነው የሚለው እምነታቸው ትክክል አለመሆኑን ኢትዮጵያውያን የራሳቸው
ጥንታዊ ሥልጣኔ እንደነበራቸው በመዝበር የተገኘው መረጃ
አረጋግጧል፡፡ የመዝበር ሥልጣኔ ፍልሰተኞች ከመምጣታቸው 800
ዓመታት በፊት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ሲሉም አስምረውበታል፡፡
ሌሎቹ ግኝቶች በዘመኑ የተላመዱ የቤት እንስሳት እነ በግ፣ ግመል፣
ፍየል፣ ውሻ፣ አህያ፣ እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ የተሟላ መረጃ የያዘ
የዶሮ ቅሪተ አካል በዚሁ ስፍራ መገኘቱም ተጠቁሟል፡፡ ለተለያዩ
አገልግሎቶች የሚውሉ ጥንታዊ የድንጋይ መሣርያዎችም መገኘታቸው
የዘመኑን ዕደ ጥበብና ሥነ ጥበብ ምን ያህል እንደነበርም ተመራማሪዋ
አመልክተዋል፡፡

ዖና ዓዲ (መነበይቲ)

መነበይቲ ከአዲስ አበባ 916 ኪሎ ሜትር ግድም የምትገኝ ከፋፂ ወደ
ዛላምበሳ በሚወስደው አውራ ጎዳና በምሥራቅ አቅጣጫ ተገንጥሎ
ሁለት ኪሎ ሜትር ተጉዞ የሚገኝ ስፍራ ነው፡፡
በአፈ ታሪክ የንግሥተ ሳባ ጥንታዊ ቤተ መንግሥት የሚገኝበት፣
ቀዳማዊ ምኒልክ ማይበላ (አስመራ አካባቢ) ከተወለደ በኋላ ወደዚህ
ቤተ መንግሥት መምጣቱና ማደጉ ይነገራል፡፡ የመንደሩ ነዋሪ የሆኑት
ቄስ ገብረ ሕይወት ምኒልክ እዚህ ቦታ እንዳገሩ ባህል ቃርሳ
እየተጫወተ ማደጉን ወላጆቻችን ያቆዩልን ታሪክ ነው ይላሉ፡፡
በመነበይቲ በቁፋሮ የተገኙት የሕንፃ ፍራሾች፣ የሸክላ ሥራዎች፣ የሰውና
የእንስሳት ቅሪተ አካል ቅድመ አክሱምና በዘመነ አክሱም የነበሩ
መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡
የመነበይቲ ቁፋሮ ተጀመረ እንጂ አልተገባደደም የሚሉት ፕሮፌሰር
ካትሪን ለሦስት ዓመት የተከናወነው ቁፋሮ ተጨማሪ ሰባት ዓመታት
ያስፈልገዋል፡፡ በመነበይቲ እየተካሄደ ያለው ቁፋሮ ለበርካታ ጥያቄዎች
ምላሽ እንደሚሰጥ፣ ይህም የአክሱም ሥልጣኔ ገንኖ በነበረበት ጊዜ
በመነበይቲ የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ ምን ይመስል እንደነበር፣ ራሱን
ችሎ ነው ወይስ ከሌሎች ጋር ተሳስሮ ነው የሚለው ወደፊት የሚታይg
ነው፡፡
እንደ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዓለም መብርሃቱ
አገላለጽ፣ የትግራይ አካባቢ የሃይማኖቶች ሁሉ መጀመሪያ፣
የሥልጣኔዎችም ከይሓና ከአክሱም ጀምሮ የሚታወቅ ነው፡፡ በዋናነት
ደግሞ መነበይቲ የንግሥት ማክዳ (ሳባ) የቅድመ የሓ የቅድመ አክሱም
ቤተ መንግሥት እንደነበረ የካናዳ ፕሮፌሰሮች ከኢትዮጵያውያን ምሁራን
ጋር ሆነው እየሠሩት ያለው ጥናት እንዲሁም በመነበይቲ የተገኘው
የንግሥት ማክዳ ቤተ መንግሥት ፍራሽ የኢትዮጵያን ታሪክ በአንድ
ዕርምጃ ወደፊት የሚወስድ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በመዝበርም ሆነ በተለያዩ አካባቢዎች የተገኙ ልዩ ልዩ ቅርሶችን
የሚቀመጡበት ሙዚየም ለማስገንባት እንቅስቃሴ የተጀመረ መሆኑንና
የዓዲግራት ከተማ አስተዳደርም ለሙዚየሙ መገንቢያ የሚፈለገውን
ያህል መሬት ለመስጠት በዓለም አቀፍ ጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ቃል
ገብቷል፡፡

No comments:

Post a Comment