ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Tuesday, January 17, 2012

የገና በዓልና አከባበሩ


"ታኅሣሥ ገሠገሠ ከተፍ አለ ገና፣
እጠብቅሃለሁ አንተ ልጅ ቶሎ ና፡፡
የታኅሣሥ ትውው የገና ፍቅር፣
ይላል ቅር ቅር፡፡"


ዓመት ጠብቀው፤ ዐውደ ዓመትን ዙረው ከሚመጡት በዓላት አንዱ የገና (ልደት) በዓል ነው፡፡ በያመቱ ታኅሣሥ 29 ቀን ይከበራል፡፡ "ዮም ተወልደ ቤዛ ኵሉ ዓለም" (ዛሬ የዓለም ቤዛ ተወለደ) እያሉ ኢትዮጵያውያኑ በደማቅ ሥነ ሥርዓት በዓሉን ያከብራሉ፡፡ ይህን በዓለ ልደት ለማክበር በመንፈቀ ኅዳር የጀመሩትን ጾም ለ43 ቀኖች አሳልፈዋል፡፡
"ያለም ሁሉ መድኃኒት
ተወለደ በበረት፣
እያሞቁት እንስሳት
ብርሃን ሆነ በዚያች ሌት
ሲዋዥቡ መላእክት
ደስ አሰኙ ለኖሩት" የሚለው ኅብረ ዝማሬ የበዓሉ መገለጫ ነው፡፡
ልደት የእምነታችን መክፈቻ በር
ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያኖችን መንፈሳዊ ሕይወት ከዕለት ዕለት በጋለ ሁኔታ ለማሻሻል እንዲረዳ በዓመቱ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ በዓላትን ታከብራለች ከእነዚህም በዓላት በጣም በደመቀ ሁኔታና በታላቅ ደስታ የሚከበረው የልደት በዓል ነው፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት የክርስቶስ ልደት የእምነታችን መክፈቻ በር በመሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም  በየትኛውም የዓለም ክፍል አዲስ ህፃን ተወልዶ ወደ ህብረተሰቡ በሚቀላቀልበት ጊዜ የሚኖረው ደስታና ፈንጠዝያ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ የህፃኑም ልደት በየዓመቱ በሚከበርበት ጊዜ በመጀመሪያ የቤተሰቡ ከዚያም የወዳጅ ዘመድና የጓደኛ ደስታ ፍፁም ልዩ ነው፡፡ ለዚህም ነው የክርስቶስ ልደት በክርስቲያን ቤተሰቦች ዘንድ በትልቅ ጉጉትና ደስታ የሚጠበቅ ልዩ ቀን የሆነው፡፡

‹‹ እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት የሆነ ተወልዶላችኋል፡፡››
 በሰማይና በምድር ለሚገኙ ነገዶች፣ የእልልታና የምስጋና ምንጭ የሆነው ነቢያት የተመኙት፣ መላእክት ያወደሱት፣ እረኞች ያወሩለት፣ ሰብዓልሰገል የሰገዱለት፣ ኃጢያተኞች የዳኑበት፣ ግዞተኞች የተፈተኑበት፣ ሀዋርያት ያከበሩት፣ ክርስቲያኖች የወረሱት፣ ለሰዎችና ለመላእክት ታላቅ ደስታ የሆነው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓል አከባበር አጀማመር እንዲህ ነበር፡፡
በወቅቱ የነበረው አውግስጦስ ቄሳር የተባለ ንጉሥ ሰው ሁሉ ይቆጠር ዘንድ ትዕዛዝ አዘዘ፡፡ በትእዛዙ መሠረትም ሰው ሁሉ ሊቆጠር ወደየትውልድ ከተማው ሄደ፡፡ ዮሴፍና እመቤታችንም ሊቆጠሩ ከናዝሬት ወደ ትውልድ ሥፍራቸው ወደ ቤተልሔም ሄዱ፡፡ በቤተልሔም ሳሉም እመቤታችን የምትወልድበት ቀን ደረሰ፡፡ በዚያ ሥፍራም ብዙ እንግዳ ስለነበር እነ ዮሴፍ የሚያርፉበት ቦታ አላገኙም ነበር፡፡ ማደርያም ስላልነበራቸው በከብቶች ማደርያ በበረት ውስጥ እመቤታችን ልጅዋን ወለደችው፡፡  
በጨርቅ ጠቅልላ እዛው በበረት ውስጥ አስተኛችው፤ በዚያ ሀገር ይኖሩ የነበሩ እረኞችም ሌሊት ከብቶቻቸውን ይጠብቁ ነበር፤ የእግዚአብሔር መልአክም በእረኞቹ አጠገብ ቆመ፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በዙሪያቸው በራ፤ በጣምም ፈሩ፡፡ መልአኩም እንዲህ አላቸው ‹‹እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ‹‹ እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት የሆነ ተወልዶላችኋል፡፡ ይኸውም ጌታ እና እግዚአብሔር የሆነ መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እናንተም ባገኛችሁት ጊዜ ምልክቱ እንዲህ ነው፡፡ ሕፃን በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ ታገኙታላችሁ›› ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ መላእክት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ እነዚህ እረኞች እርስ በርሳቸው ‹እስኪ ቤተልሔም እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን ነገር እንወቅ አሉ፡፡ ፈጥነውም ሄዱ፡፡ ማርያምንና ዮሴፍን አገኙአቸው፡፡ ሕፃኑንም በበረት ውስጥ አገኙት፡፡ በአዩትም ጊዜ የነገሩአቸውን ሰምተው በጣም ተደነቁ፡፡ እረኞቹም እንደነገሩአቸው ባዩትና በሰሙት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን በምድርም ለሰው ልጆች በጎፈቃድ ሆነ›› ብለው እያመሰገኑና እያከበሩ ወደመጡበት ተመለሱ፡፡ 
ምክንያተ ልደት
 በገና በዓል ቀን እያንዳንዱ ክርስቲያን በሀሳብ ወደ ኋላ ተመልሶ በቤተልሔም በከብቶች ግርግም ውስጥ ክርስቶስ የተወለደበትን ምሽት ያስታውሳል በጣም ጣፋጭ ምሽት አብዛኛውም ክርስቲያን ወንድ ሴት ህፃን ሽማግሌ መስዋእተ ቅዳሴን ለመስማት በምሽት ወደ ቤተክርስቲያን ያዘግማል፡፡ ምክንያቱም አምላክ ሰው የሆነበት የተባረከች እለት ናትና ለአምላኩ ምስጋና ያቀርባል ለክርስቲየኖች ትልቅ በዓል በመሆኑ አብያተ ክርስቲያናት በልዩ ሁኔታ ያሸበርቃሉ አበባዎች፣ ምንጣፋ፣ሻማው ጌጣጌጡ ሁሉም ልዩ ነው እንዲሁም በማንኛውም ቋንቋ የሚዘመሩት የልደት መዝሙሮች በጣም ውቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህንን በዓል በውጫዊ መልኩ በድምቀት እንደምናከብረው ሁሉ በውስጣችንም ህፃኑ ኢየሱስ መቀበል ይገባናል ምክንያቱም ክርስቶስ የተወለደው ሰው መሆን ምን እንደሚመስል አይደለም አምላክ ነውና ሁሉን ያውቃል ይልቁንም ከገባንበት የኃጢአት ማቅ ውስጥ ሊያወጣን በትምህርቱና በህይወቱ አብነት ሊሆነን በመጨረሻም በሞቱ የክብሩ ተካፋዮች ሊያደርገን በማሰብ ነው፡፡
ጌታችን በተወለደበት በዚያች ሌሊት መንጋቸውን ለሚጠብቁ እረኞች የእግዚአብሔር መላእክት “በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሰላም ይሁን” ሉቃ 2፡14 ብለው እንደዘመሩ ክርስቶስ የመጣው በሰዎች ሰላምን ለማምጣት ነው፡፡ ስለዚህም በጌታ ልደት ቀን አሁንም ደግሞ በልባችን ሊወለድ የሚፈልገውን ክርስቶስ ሰላሙን ይሰጠን ዘንድ በንጹህ ልብ እንቀበለው፡፡
 እንዲሁም በጌታችን ልደት በዓል ልናስተውለው የሚገባ የእመቤታችንን ታላቅነት ነው፡፡ አምላክ ከሁሉም በላይ ወዶና መርጦ ማደሪያው እንድትሆን የመረጣት እመቤታችንን ነው፡፡ እመቤታችን መልአኩ ገብርኤል “ያለ ወንድ ትወልጃለሽ” ብሎ የነገራት ትርጉሙ ባይገባትም በእግዚአብሔር ላይ በነበራት ታላቅ ፍቅርና ትህትና በእምነት ሁሉን ተቀብላለች እመቤታችን ማርያም በጊዜዋ እንዲሁ ያለ ባል መውደሉ በድንጋይ ተወግሮ ለመገደል የሚያበቃ ኃጢያት መሆኑን ብታውቅም በእግዚአብሔር በመታመን ከሰዎች የሚመጣባርን ይሉኝታ ወደ ጐን በመተው ይህንን ታላቅ ሚስጢር ተቀብላ በአለም ብርሃንን ሰጥታናለች፡፡ ይህም ወደ ትልቅ ክብር እንድትደርስ አድርጓታል፡፡ እኛም በክርስቶስ ፍቅር ብለን “አንተ እንዳልክ ይሁንልኝ” ብለን የእግዚአብሔርን ፍቃድ ለመፈጸም ያለ ይሉኝታ ለምናደርገው ጥረት በቃላት ሊገለጽ የማይችል ክብር ይጠብቀናል፡፡
 የልደት በዓል በምናከብርበት ጊዜ በየቤተክርስቲያናችን አንድ ለየት ያለ ልማድ አለ ይኸውም በልደት በዓል ከሁለት ሺ ዓመት በፊት በቤተልሔም ክርስቶስ በበረት የተወለደበትን በማስታወስ በተለያየ ሁኔታ የበረት ቅርጽ ይደረጋል፡፡ ይህ በየአብያተ ክርስቲያኑ የሚገኘው በፊት በእያንዳንዱ ክርስቲያን በልቡ ውስጥ ልዩ መንፈሳዊነትንና ደስታን ይፈጥራል፡፡ ይህ ልማድ የተጀመረው በ13ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በትልቁ ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ሲሆን በወቅቱም ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ጌታችን የተወለደበትን ሁኔታ ለማስታወስ ይህን በረት ሰርቶ በቅዳሴው መሀል በሕፃኑ እየሱስ መልክ የተቀመጠውን አሻንጉሊት ባነሳ ጊዜ ህፃኑ ህይወት ዘርቶ እንዳቀፈው በቅዱስ ፍራንቸስኮ ታሪክ ተጽፎ እናገኛለን ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ይህ የበረት አምሳል በየቤተክርስቲያኑ እየተሠራ በጌታችን ክርስቶስ ልደት ወቅት በቤተክርስቲያናችን ልዩ ድምቀትን ይሰጣል፡፡ ክርስቲያኖችም በዚህች ሌሊት ወደ በረቱ በመጠጋትና ተንበርክከው በመጸለይ ከ2ዐዐዐ ዓመት በፊት የተወለደውን ክርስቶስ ዛሬም በየቤተክርስቲያናችንና በየልባችን እንደሚወለድ ያስታውሳሉ፡፡
December 25(ታህሳስ 16) ወይስ ታኅሣሥ 29

        በ16ኛው ምእት ዓመት ከጁሊያንን ቀመር ተከልሶ የተዘጋጀውን የጎርጎሪያን ቀመር የተከተሉት ምዕራባውያን በነርሱ "ዲሴምበር 25" ባሉት ታኅሣሥ 16 ቀን ያከብሩታል፡፡ በዓሉ አንድ ሆኖ የቀኑ ልዩነት የተፈጠረው መሬት ፀሐይን ለመዞር የሚፈጅባት ጊዜ በምሥራቆች 365 ቀን ከ6 ሰዓት ነው በማለታቸው ምዕራቦች ደግሞ 365 ቀን ከ5 ሰዓት 48 ደቂቃ 46 ሰኮንድ ነው በሚል ልዩነት በመፈጠሩ ነው፡፡በዋናነት ግን
 ከጥንት ጀምሮ ሮማውያን ታህሳስ 16 (December 25 ) ቀንን እውነተኛ ፀሐይ የተወለደበት ቀን እያሉ ያከሩ ነበር ምክንያቱም በሮማውያን ግዛት የረጅሙ የክረምት ወቅት አብቅቶ በመጀመሪያ ጊዜ የፀሐዩን ብርሃን የሚያዩት በዚህች ቀን ነው፡፡ ሮማውያን በተለምዶ ከዚያ ከሚያኮራምት የክረምት ወቅት በማለፍ ብርሃንና ሙቀትን ስለሚያገኙ ለተክሎቻቸው ልማት ለከብቶቻቸውም የፍንደቃ ወቅት ስለሆነ ለዚህ ብርሃን በየዓመቱ የምስጋና መስዋእትን በመያዝ ሁሉም ወደ ተራራ ጫፍ ላይ በመውጣት መስዋዕትን ያቀርቡ ነበር፡፡
 ክርስቲያኖች እስከ አራተኛ ክፍለ ዘመን ድረስ በስደት ላይ ባልተረጋጋ ህይወት ውስጥ ስለነበሩ እምነታቸውም በዓለም ላይ በሰፊው ያልታወቀበት ዘመን ስለነበር ስለ ጌታችን ልደት ብዙም ትኩረት አይሰጡም ነበር፡፡ ስለዚህ እንደማንኛውም ሮማዊ በአባቶቻቸው የወረሱትን አምልኮ /የፀሐይ አምልኮ/ መስዋዕትን ይሰው ነበር፡፡ ወደ 320ዎቹ ገደማ ለመጀመሪያ ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች በእርጋታ መኖር የጀመሩ ክርስቲያኖች የጌታችን ልደት በታህሳስ 29 ማክበር ጀመሩ፡፡ በ354ዓ.ም ግን ሮማዊው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊብሮስ ክርስቲያኖች “ሳትሩን” እየተባለ በሚጠራው የፀሐይ አምላክ ፈንታ መንፈሳዊ የፍትህ ፀሐይ ክርስቶስ የተወለደበት የደስታና የነፃነት አብሳሪ ልደት በታህሳስ 16 ቀን እንዲከበር ለዓለም ሁሉ አዋጅ አስተላለፋ፡፡ በወቅቱ ብዙ የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት የ­­ ሊብሮስ አዋጅ አልተዋጠላቸውም ነበር፡፡ በኋላ ግን ር.ሊ.ጳ ግርጐሪዮ ቀዳማዊ በ601ዓ.ም ለሚስዮናውያን በሙሉ እንዲህ የሚል መምሪያ አወጡ “ የጣኦት ጐጆ አይፍረስ በውስጣቸው ያለ ቁሳቁስ ሁሉ ይፈራርስ በተባረከ ውሃ /ፀበል/ ቤተ መቅደሶቻቸውን እርጩት መንበረ ታቦት ይቀደስ ሕዝቡም የቤተመቅደሶቻቸውን መፈራረስ አይተው በስሕተት እንዳያዝኑ እውነተኛ አምላክን ተረድተው ኮርማዎቻቸውን ከጣኦት ይልቅ ለእውነተኛ አምላክ እንዲሰውና እንደሰግዱ አድርጉ ለዚህም አምልኮ የተለየ አከባበር ይሰጠው በዓላቸውንም መንፈሳዊ በማድረግ እግዚአብሔርን እያመለኩ በዚህ አጋጣሚ ወደ መንፈሳዊ ደስታ በመለወጥ ይበልጥ ይጓዙ፡፡ ከዚህ በኋላ አብዛኛዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ታህሳስ 16ትን እንደ ጌታ ልደት ቀን ተቀበሉ፡፡ የአርመንያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዘግይታም ቢሆን በ16ኛ ክፍለ ዘመን እንደ ኩላዊት ቤተክርስትያን የሊብሮስን አዋጅ ተቀበለች የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም ኤርትራ፣ ግብፅ እና በመካከለኛው ምሥራቅና በምሥራቅ አውሮፓ ያሉት ሀገሮች እስከ ዛሬ በታህሳስ 29 የጌታን ልደት ያከብራሉ፡፡ ገናና የገና ጨዋታ

ልደት በኢትዮጵያ ዐውድ ከገና ጨዋታ ጋር ተያይዞ በባህላዊ ጨዋታዎች ይከበራል፡፡ የተለያዩ መንፈሳዊና ባህላዊ አከባበር ከሚከበርባቸው ስፍራዎች አንዱ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው ጃንሜዳ ተብሎ የሚታወቀው ገናን ነው፡፡

በዓሉ በሁለት ቡድኖች መካከል ሚና ለይተው በሚጫወቱበት ጊዜ ተጫዋቾቹም ሆኑ ታዳጊዎች በሆታና በዕልልታ ከሚያዜሟቸው መካከል በዚህ ጽሑፍ መግቢያው ላይ የተጻፈው አንጓ ይጠቀሳል፡፡

የገናን ባህላዊ ጨዋታን ስንመለከት አስቀድሞ የቡድን አባላት የሚሆኑ ሁለት ሰዎች ይመረጣሉ፡፡ ሁለት ሁለት ተጫዋቾች ወደ አባቶች ይቀርቡና በምርጫው ወደ ቡድን ውስጥ ይገባሉ፡፡ የሚያስፈልገው የተጫዋች ቁጥር ሲሞላ ወገን ወገናቸውን ይዘው በዱላ ቀልጣፋ የሆኑ ተጫዋቾች ጥንጓን( መጫወቻ ኳሱ) ወደፊት እንድትቀጥል ይመቷታል ወይም ይመልሷታል፡፡ ተጫዋቾች ብዙ ጊዜ በጨዋታው ስለሚሰጡ ጥንጓን ከእግር መካከል በገባች ጊዜ ከሰው እግር ጋር ደርበው ስለሚመቱ የእግር መሰበር በዚህም ሳቢያ ወገን ለይተው እስከመፈናከት ይደርሳሉ፡፡ በንጉሳውያን ዘመን የመኳንንቱም አሽከሮች፣ የንጉሡና የንግሥቲቷ አሽከሮች የጌቶቻቸውን ስም በጉብዝና የሚያስጠሩት በባህላዊው የገና ጨዋታ ነው፡፡

ጨዋታው በመንደር ልዩነት ከሆነ የታች አምባ ቡድን ሀምሳ ተጫዋቾች ቢሆኑ የላይ አምባ ቡድን ሰባ ሆነው ቢጫወቱ የሚከለክል ደንብ አልነበረም፡፡ ጨዋታው በመጨረሻ ፀብ ስለሚያነሳ ብዙ ጊዜ ጉዳት ያጋጥማል፡፡ ጥንጓም ኃይለኛ ለጊ በመታት ጊዜ ዐይን እስከ ማጥፋት ትደርሳለች፡፡ ተጫዋቾች "በሚና" ብለው በሚጫወቱበት በቆልማማ ዱላ ቢደባደቡም የሚገላግል ዳኛ አልነበረም፤ ጨዋታውን በሚመለከቱ አባቶችም በድብድብ ከመሳቅ በስተቀር ሽምግልናቸው ለገና ጨዋታ አልተለመደም፡፡ "እግር ይብሳል፣ ያንከላውሳል፡፡" እያለ ማስፈራራት፣ ራስን መቀወር ወይም እንቆራቆስ ብሎ እጅና እግርን በዱላው መምታት በገና ጨዋታ የተለመደ ነበር፡፡

የገና ጨዋታ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮች የታወቀውና በኦሊምፒክ የስፖርት በዓል ከሚደረጉ ውድድሮች አንዱ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህም ጨዋታ ሆኪ በሚል ስም ይጠራል፡፡ ፈረንጆች የፊት አደጋን መከላከያ ዘዴ ይጠቀማሉ፡፡ በኢትዮጵያ ያገር ባህል ገና ጨዋታ በሚደርስ አደጋ ማንም ተጫዋች አይጠይቅም፡፡

በገና ጨዋታ አሸናፊ ለሆኑት ቡድኖች ፊሪዳና ጠጅ ተሰጥቷቸው እየበሉና እየጠጡ፣ እየዘፈኑ ሲሸልሉና ሲያቅራሩ ሜዳውን የጦርነት ድል ያገኙበት ያስመስሉት ነበር፡፡ ከሚዘፍኑትና ግጥሞች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
"ማታ ነው ድሌ፣
ይሄ ነው አመሌ፡፡
አሲና በል አሲና ገናዬ፡፡
ኦ! ጉ! አሲና በል አሲና ገናዬ፡፡
ግፋው ግፋው አለኝ እኔ እንደምን ልግፋው፣
የአንድ በሬ ጨጓራ እንደ ቅል የነፋው፡፡
የብብቱ ሽታ፣ የመንፈቅ በሽታ፡፡
የጀርባው መርሬ፣ ያውላል ጥድ በሬ፡፡
ካስር ጋን አተላ፣
አይተርፈው በአንኮላ፡፡
እግርህ የሸረሪት ሆድህ የእንቁራሪት፣
ቀን እንደጠላሁ ና እንዳትመጣ ሌሊት፡፡"

ስድብ ለተራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በመኳንንቱና በነገሥታቱም ላይ ሊሰነዘር ይችላል፡፡ በሚደርስባቸው ስድብ ግን ምንም ዓይነት ቁጣና ቅጣት አያደርጉም፡፡

"በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ
በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ፡፡" የሚለው የዘፈን ግጥም ይህን ባህል ይገልፃል፡፡
የገና ጨዋታ ከክርስትና ሃይማኖት በፊት ይዘወተር እንደነበርና በኢትዮጵያ ከታኅሣሥ የመኸር ወቅት ጋር የተያያዘ ባህል ነበረ፡፡ ከበዓሉ ጋር የተያያዘ ብዙ የስነቃል ግጥሞችን ይገኛሉ፡፡
"ታኅሣሥ ገሠገሠ ከተፍ አለ ገና፣
እጠብቅሀለሁ አንተ ልጅ ቶሎ ና፡፡
ይወዘውዘኛል አልጠላኝም ገና፣
ፍቅር ሞገደኛው እየነሳኝ ጤና፡፡
ምግብ አያስበላ አያስለብስ ልብስ፣
ሞገደኛው ፍቅሩ ይዞኝ በታኅሣሥ፡፡
በማለዳ ጀንበር በገና ጨረቃ፣
እኔን እኔን ብላ መጣች ተደብቃ፡፡"ምስጋና
በሔኖክ ያሬድ
በወ/ኪዳን ጸጋ ኪሮስ
በአዜብ ገብሩ
መልካም
ዜና -እሌኒ ይሁኔ

5 comments:

  1. it' too great..............GOD bless u

    ReplyDelete
  2. What a blessing! God blesss you.

    ReplyDelete
  3. thank you for sharing...God bless you

    ReplyDelete