ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Thursday, April 4, 2013

ደብረ ዘይት ፡- የዓለማችን ታሪክ ፍፃሜ ቅዱስ ተራራ


ፀሐፊ፡- በፍቅር ለይኩን

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ቀኖና መሠረት የዓብይ ጾም ወይም የሑዳዴ ጾም አምስተኛ ሳምንት ‹‹ደብረ ዘይት›› በመባል ይጠራል፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት አስተምህሮ የዓብይ ጾም ሳምንታት በሙሉ ከክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ታሪክ ጋር የተያያዘ የራሳቸው የሆነ ስያሜ አላቸው፡፡
የዚህ ስያሜ አመንጪም የ6ኛው መቶ ክ/ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቅና የዜማ ደራሲ የሆነው ቅዱስ ያሬድ እንደሆነ ነው የታሪክ ድርሳናት የሚመሰክሩት፡፡ ገና አውሮፓና እስያ በከፊል፣ አሜሪካና እንዲሁም የተቀረው የዓለማችን ክፍል በሙሉ ባልነበሩበትና ወንጌልን ባልሰሙበት በዛ የጥንት ዘመን ኢትዮጵያውያን ታላላቅ የሆኑና ዓለምን ዕፁብ ድንቅ ያሰኙ የሥነ ሕንጻ ጥበብና ክህሎት የተንጸባረቀባቸው ቤተ መቅደሶችን ገንብተው፣ መጽሐፍትን መርምረው፣ ዜማ ደርሰው፣ ቅኔ ፈጥረው ልዩ በሆነ መንፈሳዊ ሥርዓት ለረዥም ዘመናት አምላካቸውን ሲያመልኩ ቆይተዋል፡፡

አውሮፓ የሙዚቃ ኖታ ለመፍጠር አይደደለም ገና እንኳን ለማሰብ ባልደፈሩበት በጥንቱ ዘመን ቅዱስ ያሬድ ከሺሕ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ዜማ ከነምልክቱ ወይም ኖታው በቀመር ዛሬ ዓለም የሚደነቅበትን ሰማያዊና መንፈሳዊ ምሥጢር ያለበትን የቤተ ክርስቲያኒቱን አምልኮተ ሥርዓት መሠረት ለመጣል ችሏል፡፡

ማሕሌታዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በተጨማሪም በዓብይ ጾም ውስጥ ያሉትን ሳምንታት በሙሉ ከብሉይ መጻሕፍት፣ ከመዝሙራት፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ትምህርትና ታሪክ ጋር በሚገባ አስማምቶ በመከፋፈል ቀምሮታል፡፡ በዚህም በቅዱስ ያሬድ ስያሜ አከፋፈል መሠረትም የዓብይ ጾም አምስተኛ ሳምንት እሑድ ጀምሮና ሳምንቱ በሙሉ ‹‹ደብረ ዘይት›› በመባል ይታወቃል፣ ይዘከራል፡፡
እስቲ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በተለምዶ ጾመ እኩሌታ ወይም ደብረ ዘይት ተብሎ ስለሚከበረው በዓል ከማውራቴ በፊት በእስራኤል ምድር ስለሚገኘው የደብረ ዘይት ተራራ ጥቂት ነገሮችን ለማለት ልሞክር፡፡
ደብረ ዘይት ማለት ቃሉ “ደብር” ሲል ተራራ ሲሆን “ዘይት” ሲል የወይራ ዛፍን ያመለከታል፡፡ ባጠቃላይ ደብረ ዘይት የወይራ ዛፍ (የዘይት ዛፍ) የበዛበት ተራራ ማለት ነው፡፡ ቦታው የሚገኘው በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ከጎልጎታ (ቀራንዮ) ተራራ በስተምስራቅ በግምት ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ታላቅ ተራራ ነው፡፡ በሁለቱ ተራሮች መካከል ጌቴሴማኒ የሚባለው ለምለም ስፍራ ይገኛል፡፡ በዚህም ስፍራ የኢየሱስ ክርስቶስ እናት የቅድስት ድንግል ማርያም የመቃብር ስፍራ አለ፡፡
የደብረ ዘይት ተራራ ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ የሚያድርበት፣ የሚያስተምርበት፣ ውሎ የሚያርፍበት ሥፍራ ነው፡፡ እንደ ወንጌሉ ጸሐፍትና የክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ መሠረት ከዚሁ ከደብረ ዘይት ተራራ ላይ ነው ኢየሱስ ክርስቶስ ያረገው፡፡ ኋላም በዳግም ምጽአት እዚሁ ተራራ ላይ ነው ለፍርድ የሚመጣው፡፡
በተጨማሪም ደብረ ዘይት ተራራ ወገብ ላይ በሰፊው ተንጣሎ የሚታይ አንድ ነገር አለ ፤ ይኸውም የአይሁድ መቃብር ነው፡፡ ይህን ስፍራ አይሁዳውያኑ ለመቃብርነት የመረጡበት ምክንያትም ወደፊት መሢሑ መጥቶ እስራኤልን ነፃ አውጥቶ ወደ አባቱ ያርጋልና ፣ ኋላም ለፍርድ ሲመጣ በመጀመሪያ የሚፈርድበት ስፍራና ሙታንም የሚነሱበትና የሚሰበሰቡበት ተራራ ይህ በመሆኑ እኛ መሢሐችንን ለማግኘትና ከሙታንም ለመነሳት የመጀመሪያዎቹ እንሆናለን ብለው በማመናቸው ነው፡፡
አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስን መሢሑ እርሱ ነው ብለው አያምኑም ፣ በዘመኑም አልተቀበሉትም ፣ አሁንም አይቀበሉትም፡፡ መሢሕ ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ የተቀባ ማለት ሲሆን በግሪክ ቋንቋ ደግሞ ክርስቶስ ማለት ነው፡፡በመሆኑም እስራኤል ወደፊት አንድ ታላቅ መሢሕ እግዚአብሔር እንደ ሚልክላቸው ባላቸው ተስፋ መሠረት ገና አሁንም ድረስ መሢሐችንን እንጠብቃለን ይላሉ፡፡
ስለ ደብረ ዘይት ተራራና ተራራዋን በኢየሩሳሌም ወይም በዓለማችን ካሉ ተራራዎች ሁሉ ልዩ እንድትሆን ስላደረጋት ስለ መሢሑ ይህን ያህል ካልኩ አሁን ደግሞ በመጠኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ አስተምህሮና ሥርዓት መሠረት ጾመ እኩሌታ ተብሎ ስለሚጠራው ስለ ደብረ ዘይት በዓል ምንነትና ታሪክ ከአይሁዳውያኑ ታሪክና ከክርስትና ሃይማኖት ጋር አያያዤ ጥቂት ነገሮችን ልበል፡፡
እስካሁን እንዳየነው በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሕግና ሥርዓት መሠረት የዓብይ ጾም እኩሌታ ደብረ ዘይት በመባል ተሰይሟል፤ ይኽውም ወንጌላውያኑ እንደዘገቡት በዚሁ ሰንበት ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ ለቅዱሳን ሐዋርያቱ ስለዓለም መጨረሻና ስለዳግም ምጽአቱ ምልክቱን በዝርዝር ነግሯቸዋል፡፡
ደቀ መዛሙርቱ ከመምህራቸውና ከጌታቸው ከኢየሱስ ጋር በደብረ ዘይት ተራራ ላይ በአንድነት ተቀምጠው ሳለ፣ ደረቱን ለደብረ ዘይት ተራራ ሰጥቶ በሚያስገርም ግርማና ውበት በፊለፊታቸው የተንጣለለውን የኢየሩሳሌምን መቅደስ እያስተዋሉ፣ ጌታ ሆይ ይህን ባለ ልዩ ግርማ መቅደስና የተሠራበትን ውብ ድንጋዮች ታያዋለህን አሉት፡፡
ታሪክ ጸሐፊውና ሐኪሙ ሉቃስና ወንጌላዊው ማቴዎስ እንደጻፉት ኢየሱስም መልሶ፡- ‹‹ይህን ታደናቃላችሁን እውነት እውነት እላችኋለሁ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም፡፡›› ሲል ደቀ መዛሙርቱና አይሁዳውያኑ የሚኮሩበት መቅደስና ከተማቸው ኢየሩሳሌም እንደ ጥንታዊቷ ባቢሎን የፍርስራሽ ከተማ፣ የኃጢአት፣ ያለመታዘዝ፣ የጥፋትና የውርደት ምልክት ይሆናሉ፡፡ ሲል አስቀድሞ በትንቢት መልክ በግልፅ  ለተከታዮቹ ለሐዋርያቱ ነገራቸው፡፡
በኢየሩሳሌም መቅደስ አስገራሚ ውበትና ግርማ ልዩ አድናቆት ውስጥ ለገቡት ለተከታዮቹ ሐዋርያት መምህራቸው ኢየሱስ የነገራቸው ትንቢትም፣ አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ እንደዘገበው በ70 ዓ.ም. ሮማውያን ኢየሩሳሌምን በወረሩ ጊዜ ትንቢቱ ፍጻሜውን እንዳገኘ ይነግረናል፡፡
‹‹አፍሪካ ባይብል ኮመንታሪ›› እንደሚያትተው ከሆነ ይህ የኢየሩሳሌም ጥፋትና የመቅደሱ ውድመት አስቀድሞ በአይሁድ ቅዱሳን ነቢያት በሆኑት በነቢዩ ኤርምያስ፣ ዳንኤልና ሚክያስ ተገልጾ እንደነበር ይገልጻል፡፡
‹‹ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን (እስራኤል) እንደ እርሻ ትታረሳለች፡፡ ኢየሩሳሌምም የድንጋይ ክምር ትሆናለች፡፡ የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል፡፡›› በማለት አስቀድሞ በነቢዩ ሚክያስ አፍ መነገሩን ‹‹አፍሪካን ባይብል ኮመንታሪ›› መጽሐፍ በሰፊው ያብራራል፡፡
ሐዋርያት በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆነው በሚያስገርም ውበቱና ግርማው የተመሰጡበት ቤተ መቅደሳቸውና የአባቶቻቸው የቃል ኪዳን ምድር የሆነችው ቅድስቲቱ ከተማቸው ኢየሩሳሌም በጌታ ዘንድ ለእሳት ፍርድ የተጠበቁ፣ የመጥፋትና የውርደት ምልክት መሆናቸውን አስቀድሞ የሚያውቀው አምላክ፣ የፍርድ ሰዓትን የቀጠረላቸው የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያቱ ውርንጫ ላይ ሆኖ በታላቅ ድል፣ ዝማሬና ሆታ ወደ ከተማይቱ በገባበት ሰዓት ኢየሩሳሌም በዝማሬ፣ በሆታና በሐሴት ተሞላች፡፡
በዛ ሁሉ ሆታ፣ ደስታና ሐሴት ውስጥ ተከታዮቹ ሐዋርያት፣ አይሁዳውያኑ፣ የኢየሩሳሌም ሴቶች፣ ጎበዛዝትና ሽማግሌዎች ሰማይ ሰማያትን በታላቅ ዝማሬና ሆታ በሞሉበት ቅፅበት፣ የቢታንያ ድንጋዮችና በእናቶቻቸው እቅፍ ውስጥ ያሉ ሕጻናት እንኳን ሣይቀሩ ለአይሁድ ንጉሥ የምስጋና ቅኔ በሚደረድሩበት አስደናቂ የማሕሌት ስርዓት ላይ አንድ ፈፅሞ በማንም ያልተጠበቀ እንግዳ ክስተት በኢየሩሳሌም ስለ ኢሩሳሌም ሆነ፡፡ በታላቂቱ የንጉሥ ከተማ፣ በሳሌም፣ በሰላም ከተማ በኢየሩሳሌም፡፡
ይህን በአይሁዳውያኑ ዘንድ እንግዳና ፈፅሞ ያልተጠበቀ ክስተት ወንጌላዊው ሉቃስ እንዲህ ሲል በወንጌሉ ውስጥ አስፍሮታል፡-
ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት እንዲህ እያለ፡- ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ እንኳን ብታውቂ፣ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል፡፡ ወራት ይመጣብሻልና፣ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል፣ ይከቡሻልም፣ በየበኩሉም ያስጨንቁሻል፡፡ አንቺንም በአንቺም ውስጥም የሚኖሩትን ልጆችሽን ይጥላሉ፡፡ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተውም፡፡ የመጎብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና፡፡
አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ እንደዘገበው ቅኝ ገዢዎቹ ሮማውያን ኢየሩሳሌምን ለቀናት ከበው፣ የከተማይቱን መውጫና መግቢያ ዘግተው፣ አይሁዳውያኑ መውጣትም ሆነ መግባት እንዳይችሉ አድርገው አስጨንቀዋቸው ነበር፡፡ በዚህም ንጉሣቸው ኢየሱስ እንደተናገረው ኢየሩሳሌም፣ ሕዝቦቿና ልጆቿ ሁሉ ሳይቀር እንደ መርግ በከበደ መከራ፣ በጭንቀትና በምጥ ጣር ውስጥ ገብተው ነበር፡፡
በቅድስት ከተማቸው ቅጥር መያዝ ለራብ የተጋለጡት አይሁዳውያን ከበባው በተጠናከረ ቁጥር የሚላስ የሚቀመስ በማጣታቸው የተነሳ የፈረሶቻቸውን ኮርቻ፣ የዛፍ ፍሬዎች፣ ስራ ስርና ቅጠላ ቅጠል እንኳን ሣይቀር ለመብላት ተገደው ነበር፡፡
የሮማውያኑ ከበባ አላፈናፍን ሲልና ራቡ በእጅጉ እየከፋ በሄደበት ወቅትም ይህንኑ የዛፍ ቅርንጫፍና ፍሬም ሆነ ስራስርና ሳር ለመብላት በሚደረግ ሽኩቻ በርካታ አይሁዳውያን እርስ በርሳቸው በመጋደል፣ አባት ለወንድ ልጁ፣ እናትም ለሴት ልጇ መራራት ያልቻለችበትና ሁሉም ራሱን ለማዳን የሚፍጨረጨርበት ክፉና አሰቃቂ የሆነ እልቂት ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ በዛን ቀውጢ ወቅትም የገዛ ልጆቻቸውንና ወገኖቻቸውንም የበሉ ሰዎች እንደነበሩ ጽፏል ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ በአይሁዳውያን ታሪክ መጽሐፉ፡፡
መቼም ራብ ቀን አይሰጥም፡፡ በአገራችን በኢትዮጵያ በተከሰተው በተለምዶ ክፉ ቀን በሚባለው የራብ ዘመን አንዲት እናት ሕጻናትን እየያዘች በመብላት ነፍሷን ለማቆየት ባደረገችው ጭካኔ የተነሣ ተከሳ ንጉሡ አፄ ምኒልክ ፊት ቀርባ እንደነበርና ይህን የሰሙት አፄ ምኒልክም በሁኔታው አዝነው ዕንባቸውን ማፍሰሳቸውን ታሪካችን ይነግረናል፡፡
በዚህ ሁሉ ራብና ሰቆቃ ውስጥ የነበሩት አይሁድ የጠላቶቻቸው ከበባ በቀረበ ቁጥር ነፍሳቸውን ከጠላቶቻቸው እጅ ለመታደግ ሲሉ የኢየሩሳሌም መቅደስን ተገን አድርገው ነበር፡፡ ምንም ጠላቶቻችን ቢበረቱብንና ቢያሸንፉንም የአባቶቻችን አምላክ ይህን መቅደስ በአሕዛብ እግር ይረገጥና ይዋረድ ዘንድ አሳልፎ አይሰጠውም በሚል ተስፋ ከራብ እልቂት የተረፉ በርካታ አይሁዳውያን የኢየሩሳሌሙን መቅደስ የሙጥኝ ብለውት ነበር፡፡
ግና ያ የተመኩበት፣ ያ የአባቶቻችን አምላክ በምንም ሁኔታ ለጠላቶቻችን አሳልፎ አይሰጠውም፣ የአሕዛብ እግርም አይረግጠውም ባሉት መቅደስ ውስጥ አይሁዳውያን በመጨረሻ ሰዓት በአረመኔዎቹና በአሕዛብውያኑ በሮማውያን እጅ ከምንሞት በማለት እርሰ በርሳቸው በሰይፍ ተራርደው ተላለቁበት፡፡ አይሁዳውያኑ በዚህ የእርስ በርስ እልቂት ደማቸው በመቅደሱ መሠዊያ መካከልና በመቅደሱ በር ታች እንደ ጎርፍ መፍሰሱን አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ ይተርክልናል፡፡
ጆሴፈስ የቅዱስ መቅደሱን ፍፃሜ፣ የከተማይቱን የኢየሩሳሌምን ውድመትና ጥፋትም በእንዲህ ልብን በሚሰብር ሁናቴ ትረካውን ይቀጥላል፡፡
ሮማዊው ጄኔራል ቲቶና ሠራዊቱ ወደእዛ ባለ ታላቅ ግርማና ለ46 ዓመታት ሲሠራ ወደነበረው ውብ ቤተ መቅደስ ዓይኖቹን ባማተረ ጊዜ ከውበቱና በቤተ መቅደሱ ጣራዎችና ግድግዳዎች ላይ በፈሰሱት ወርቆችና የከበሩ ማዕድኖች በእጅጉ ተገርሞ ነበር፡፡ እናም ጄኔራል ቲቶ በምንም ሁኔታ ቢሆን በዚህ ውብ መቅደስ ላይ ማንም እጁን እንዳያነሳ ጥብቅ የሆነ ማስጠንቀቂያን ለሠራዊቱ አስተላልፎ ነበር፡፡
ለቀናት በሮማውያን ከበባ ስር የወደቁት አይሁዳውያን ግን እንደ ምንም የሞት ሞታቸውን ከራብ የተረፋቸውን ጉልበታቸውን አሰባስበው በሮማውያኑ ላይ የደፈጣ አደጋ ጣሉባቸው፡፡ ‹‹ብጥለው ገለበጠኝ›› እንዲሉ አበው በዚህ የደፈጣ አደጋ በእጅጉ ከተበሳጩት ሮማውያን መቶ አለቃ መካከል አንዱ በእሳት የተቀጣጠለ ችቦ አይሁዳውያኑ ወደተከማቹበት ወደ ቤተ መቅደሱ በመወርወር፣ ቤተ መቅደሱ በእሳት እንዲጋይ የመጀመሪያውን እርምጃ ወሰደ፡፡ ቀጥሎም ሌሎቹም የሮማ ወታደሮች ወዳዛ አይሁዳውያኑ ወደሚኮሩበትና እንደ ነፍሳቸው ወደሚሳሱለት ቤተ መቅደስ የጥፋትና የእልቂት ሰይፋቸውን መዘው በመግባት መዓታቸውን ማዝነቡን ተያያዙት፡፡
ቤተ መቅደሱ በእሳት እየተቀጣጠለ መሆኑ መልእክት የደረሰው ሮማዊው ጄኔራል ከልዩ ጠባቂዎቹ ጋር በፈረስ ገስግሶ ከቦታው ሲደርስ ነገሮች ሁሉ ከቁጥጥር ውጪ ሆነው ነበር፡፡ ቤተ መቅደሱ በእሳት እየተያያዘና ሮማ ወታደሮችም በቤተ መቅደሱ ተተገነው ያሉትን አይሁዳውያን ላይ እርምጃ እየወሰዱ ነበር፡፡ በመቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ያሉት አይሁዳውያንም በአሕዛብ እጅ ከመውደቅ በማለት እርስ በራሳቸው በሰይፍ አንገታቸውን እየተቀላሉ በራሳቸው ላይ አሰቃቂ የሆነ ሞትንና እልቂትን አወጁ፡፡
በእሳት እየጋየ ያለው መቅደሱና በመቅደሱ ውስጥ እንደ ጎርፍ እየፈሰሰ ያለው የአይሁዳውያኑ ደም፣ ቤተ መቅደሱ ከተሠራበት ወርቅና የከበሩ ማዕድናት ጋር እየተዋኸደና እየቀለጠ የፈጠረው ልዩ ህብር ኢየሩሳሌምን ሀምራዊ የእሳት ከተማ፣ የነበልባል አምድ አስመሰላት፡፡ ልባቸው በመቅደሱ ወርቅና የከበሩ ማዕድናት የነኾለለው ሮማውያኑ ወታደሮችም የመቅደሱን ድንጋይ እያፈረሱና እየናዱ ለዘረፋ ተሸቀዳደሙ፡፡
The Great Controversy መጽሐፍ ደራሲ የሆነችው የቤ/ን ታሪክ ጸሐፊ ኤለን ጂ. ኋይት የሮማውያኑ የመቅደሱን ወርቅ ለመዝረፍ በወሰዱት የመቅደሱን ድንጋይ የማፍረስ ድርጊት ኢየሱስ ስለ መቅደሱ ሲናገር ‹‹ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም፡፡›› ያለው ትንቢት እንዲህ ባለ አሰቃቂና ዘግናኝ ሁኔታ ፍፃሜውን አገኘ ስትል ጽፋለች፡፡
ኤለን በዚህ መጽሐፏ ውስጥ ለዘመናት አይሁዳውያኑ ሲኩራሩበት የነበረው ቤተ መቅደስም ሊያድናቸውና ሊቀድሳቸው የመጣውን ጌታቸውንና መሢሐቸውን በመግፋታቸውና ለሞት አሣልፈው በመስጠታቸው የተነሣ ኢየሩሳሌም እንዲህ ላለው የእግዚአብሔር ፍርድ፣ ቁጣና መዓት ተላልፈው ተሰጡ በማለት አስረግጣ ጽፋለች፡፡
ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ትላለች ኤለን በዚሁ መጽሐፏ፣ ኢየሱስ በመጨረሻ ጊዜ ወደዚህ መቅደስ በገባበት ጊዜ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን ነጋዴዎች፣ ዘራፊዎችና ወንበዴዎች በጅራፍ ገርፎ ካሰወጣና ‹‹የአባቴ ቤት የጸሎት ቤት ይባላል፤ እናንተ ግን ወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኹት፡፡›› በማለት ቅዱስ መቅደሱን የንግድ ቤት ያደረጉትን ወንበዴዎች ከገሰጻቸው በኋላ፣ ‹‹… ከእንግዲህ ቤታችኹ የተፈታ ይሆናል፡፡›› ብሎ በተናገረው ትንቢታዊ ቃል መሠረት በመቅደሱም ሆነ በኢየሩሳሌም ከተማ ላይ የጌታ ትንቢት አንድ በአንድ ተፈፅሟል ስትል ትደመድማለች፡፡
በዘመናችንም ‹‹የአባቴ ቤት የጸሎት ቤት ይሆናል፡፡›› በሚል የድኾችና የምስኪኖች መጠጊያ እናት ናት ተብላ የተነገረላት ቤተ ክርስቲያን በተቃራኒው የንግድ ቤትና የወንበዴዎች ዋሻ ወደመሆን የተሸጋገረች ነው የምትመስለው፡፡ በርካታ ድሆች፣ አረጋውያንና መበለቶች፣ እናት አባት የሌላቸው ሕጻናት፣ ድውያንና መጻጉዎች በደጇ የወደቁ ቤተ ክርስቲያን የእነዚህን ድሆችና ምስኪኖች ጩኸትና ዋይታ አላየኹም አልሰማውም በሚል የንግድ ቤት ግንባታ ውድድር ውስጥ የገባች ነው የምትመስለው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ዙሪያዋን በንግድ ቤትና በሱቆች ተንቆጥቁጣ በገንዘብ ባሕር ውስጥ እየዋኘች፣ ሀብትና ንብረቷ በአስመሳዮች፣ በወንበዴዎች፣ በሙሰኞችና በአጭበርባሪ ነጋዴዎች እየተዘረፈ ባለበት በዚህ ወቅት በደጇ ለወደቁ ድሆችና ምስኪኖች ምዕመኖቿ ከሚጥሉላቸው የሳንቲም ሽርፍራፊ በስተቀር ቤተ ክርስቲያኒቱ ለእነዚህ ድሆች ዘላቂነት ያለው ሥራ ከመሥራት ይልቅ የመቃብር ሥፍራ እንኳን ሁሉ ሳይቀር እያፈረሰች የንግድ ቤትና ሱቆችን እየገነባችና እያስፋፋች ነው ያለችው፡፡
እስቲ ለመሆኑ በከተማችን የትኛው ቤተ ክርስቲያን ነው ለአረጋውያን መጦሪያ፣ ለድኾች መርጃ የሚሆን ተቋም የገነባው፡፡ በጣም ጥቂትና በጣት የሚቆጠሩት አብያተ ክርስቲያናት ለትውልድ ማፍሪያ የሚሆን የትምህርት ተቋማት መገንባታቸውን አይተናል፡፡ እነዚህም የትምህርት ተቋማትም ቢሆኑ በአብዛኛው በራቸው ክፍት የሚሆነው ኪሳቸው ደጎሰ ላሉት እንጂ ለድሆችና ረዳት ለሌላቸው አይደለም፡፡ ቢሆንም ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን ዙሪያና አጥር በንግድ ቤተ ከሞሉት እነዚህኞቹ መቶ በመቶ ሳይሻሉ አይቀርም፤ ቢያንስ ትውልድ እየቀረጹ ነውና፡፡
በከተማይቱ እምብርት ባሉ አንዳንድ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የመዝናኛ ስፍራዎችና ጭፈራ ቤቶች አንኳን ለሀያ አራት ሰዓት የማይቋረጥ አገልግሎት በሚሰጡበት በዚህ ዘመን የዘመናችን ቤተ ክርስቲያን ግን እህል ውኃ የማያሰኝ ቆመጥና ነፍጥ ባነገቱ ዋርድያዎቿ በሯ ከምሽት ሰዓት በኋላ በትላልቅ ሰረገላና መሸጎሪያዎች ተቆልፈው ድሆች ከግቢዋ ተገፍትረው እየወጡ ለሌሊቱ ብርድና ቁር ተጋልጠው እንዲኖሩ ይፈረድባቸዋል፡፡ እናም እነዚህ ድኾችም በሺሕዎችና በአስር ሺሕዎች በሚቆጠር ብር በሚከራዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ የንግድ ማእከላት በረንዳ ላይ ወድቀው ኑሮአቸውን በምሬት ይገፋሉ፡፡     
በእኛ ዘመን ላለችው ቤተ ክርስቲያን ቅዱሱ ስፍራ፣ ቤተ መቅደሱ፣ ‹‹የአባቴ ቤት የጸሎት ቤት ይሆናል፡፡›› ቤተ ክርስቲያን የድኾች መጠጊያና እናት ናት፡፡ የሚለው ኃይለ ቃል ከንግግር ወይም ከስብከት ወጥቶ ተግባራዊ መሆን ያቃተው ነው የሚመስለው፡፡ እስቲ ብዙም ሳልርቅ ወደተነሣኹበት ዋና ርዕሰ ጉዳዬ ወደ በዓለ ደብረ ዘይት መደምደሚያ ሐሳብ ልመለስ፡፡
70 ዓ.ም.ጀምሮ ከምድረ ገጽ ጠፍታ የነበረችው እስራኤል እንደ አገር በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1948 ወደ ዓለም መድረክ ብቅ ብትልም በ70 ዓ.ም. በሮማውያኑ የፈረሠው የቤተ መቅደሷ ጉዳይ ግን አሁንም ያልተፈታ እንቆቅልሽ እንደሆነ ዘልቋል፡፡ ኤለን ጂ. ኋይትም ሆነች ሌሎች በርካታ የሥነ መለኮት ሊቃውንት እንደሚያብራሩት የኢየሩሳሌም መቅደስ መፍረስ እስካሁንም ድረስ በርካታ አይሁዳውያን በሐዘንና በሰቀቀን የሚያስታውሱት የታሪካቸው ዋና ክፍል ነው፡፡
እናም የእስራኤል እንደ መንግሥት መመሥረትና በተለይም ደግሞ አይሁዳውያኑ በዓለም ፍፃሜ የፈረሠውን መቅደሳቸውን እንደገና ለመገንባት የሚነሡበት ቀን በዓለም ታሪክ ውስጥ የምድራችን ታሪክ የመጨረሻው መጀመሪያ ይሆናል ሲሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ ትንቢቶችን በማስደገፍ ያብራራሉ፡፡
ይኸው ከደብረ ዘይት በዓል ጋር በተራራዋ ደብረ ዘይት የተነሣ ተደጋግማ የምትነሳውና የዓለማችን ታሪክ ፍፃሜ መድረክ ናት ተብላ የምትታወቀው እስራኤል አሁንም ድረስ ዓለምን ሁሉ የልብ ትርታ ይዛ ያለች አገር እንደሆነች ቀጥላለች፡፡ የምድሪቱ ዕጣ ፈንታ መዘውር በእጇ የያዘች የምትመስለው እስራኤል የምድራችን ኃያላን ሁሉ ዓይን ማረፊያ ናት፡፡ እናም ዘወትር የዓለም ሁሉ ሕዝብ ዓይንና ጆሮም ወደዚህች ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ቅድስት ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ነው፡፡
በዚህ በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ስርዓት በሚከበረው በዓለ ደብረ ዘይት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ተዋሕዶ ቤ/ን ቅዳሴው፣ ዝማሬው፣ የቅዱሳት መጽሐፍት ንባባት ሁሉ ከዚሁ ከዓለም ፍፃሜ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዕለቱም የዓለም ፍፃሜ፣ የመጨረሻው ፍርድና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት የሚታሰብበት ቀን እንደሆነ ነው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንቶች በስፋትና በጥልቀት ሚያስተምሩት፡፡
የደብረ ዘይት በዓል በትግራይ ክልል በማይነብሪ ናዝሬት የምትባል ቦታ አለች፤ በዚሁ በማይነብሪ በናዝሬት በምትገኘው የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ በዓሉ ታላቅ በሆነ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓትና ድምቀት እንደሚከበር ታሪክ አዋቂ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ይናገራሉ፡፡
በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ቅርብ ርቀት በሚገኘው በሳማ ሰንበት የደብረ ዘይት በዓል በርካታ ምእመናን በተገኙበት በደማቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡ በአጠቃላይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገደማትና አድባራት የደብረ ዘይት በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት በድምቀት ይከበራል፡፡
ከበዓሉ ፍፃሜ በኋላም ምዕመናን እህል ከመቀመሳቸው በፊት የሚበሉት ከጥራጥሬ የተዘጋጀ በቆልት ነው፡፡ ይኽም ታላቅ የሆነ መንፈሳዊ ምስጢርና ትርጓሜ እንዳለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ የዚህ በቆልት የመብላት ተምሳሌትነቱ የሞተ፣ የደረቀ ከሚመስለው ጥሬ ዳግም ሕይወት ዘርቶ መብቀሉ የትንሣኤ ምልክት ሲሆን ምዕመናን ይህን በቆልት መብላታቸው በዳግም ትንሣኤ እንደሚነሡ ለማጠየቅ ነው፡፡
ምናልባትም ምእመናን ይህን በቆልት ሲበሉ ያልበቀለ ጥሬ ካገኙ ከአፋቸው አውጥተው ይተፉታል፡፡ ይኽም  ተምሳሌትነቱ በዳግም ትንሣኤ ለኩነኔና ለዘላለም ጥፋት ከሚነሡት ፈጣሪያቸው እንዳይደምራቸው ለማጠየቅ ነው፡፡ ይህ የደብረ ዘይት በዓል ታላቅ ከሆነው መንፈሳዊ ምሥጢሩና ድባቡ ባሻገር ታሪካዊና ባህላዊ አንድምታ ያለው የቱሪስት መስህብ ሊሆን የሚችል ታላቅ በዓል ነው፡፡
ሰላም! ሻሎም!

2 comments: