ሰላም ወዳጆች እንዴት ከረማችሁ?
ፌስቡክ መጠቀም ማቆም እረፍት አይደል እንዴ?ከዚህ በኋላም በተጠናከረ ሁኔታ ከፌስቡክ ዓለም ለመውጣት ዝግጅት ላይ ነኝ።
ሃሃሃሃ
የምን ዝግጅት ?....... ወጥቻለሁ።
ደህና የጨመርኩትን ኪሎማ አልቀንስም...
ቁም ነገር ግን ለምን አትሉም?
ከልብ ስሙን.... ፌስ ቡክ ከገባሁ አርባ ቀናት አለፉኝ። ከዝቋላ አባቶች ግድያ ጀምሮ...
ይኸው #የዝቋላ አባቶችን በነፈስ በላው ስርዓት ካጣን እና አርባ ቀናቸውን ካወጣን ቀናት ተቆጠሩ። እኔም ቤተሰቤም አባ ኪዳነ ማርያም (የገዳሙ ጸሐፊ የነበሩት) የእኔ ደግ አባት በረከታቻው ይደርብኝና ካጣኋቸው ሰነበትኩ ፤ ሰነበትን። እኔም ዜና እልፈታቸውን ከሰማሁ በኋላ እኔም እኔ አይደለሁም። ብዙ ነገሬ ወድቆ ተሰባብሯል።
ኡፍፍፍ ህይወት እንደ ቀልድ የምታልፍበት ሀገር ላይ ሆኖ ተስፈኛ መሆን እንዴት የሚያደክም መሰላችሁ። ያደክማል። ላለፉት አርባ ቀናት ከአንድ ወይም ሁለት ቀን ውጪ ከቤቴ አልወጣሁም።
ምን ለማየት ምን ለማግኘት ልውጣ?
ወዳጆቼ አሁን ላይ በመንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ ትምህርት የትኛውም ከፍታ ላይ ብትገኙ የእናንተን የመኖርና የአለመኖር ሁኔታ በደቂቃ ውስጥ የሚወስኑት . . . . . . . ሁነዋል ሀገራችንን የሚመሯት ። ይሄ እንዴት አያስከፋ አያሳዝን። ሀገሬ ማልቀስ ከጀመረችና ሀዘኗ ከበረታ ከጨለመች ሰነበተች።
ምን ብርሃን ምን ተስፋ ይታየኝ ዝም ከማለት ውጪ...
ጥቅመኛ ካልሆነ አሁን ላይ በሀገሩ ተስፋ የሚታየው አለ ይሆን?#አባ_ኪዳነ_ማርያም የብዙ ነገሬ ብርታት ነበሩ። ሚስጥረኛዬም... አባቴም... የቤተሰቦቼም ቀኝ እጅ... የባለቤቴ ወዳጅ..... ክፉ እንዳይነካኝ አሳቢዬ .... ጸሎተኛዬ .... ዝቋላ ስሄድም እንደ ንጉስ ተቀብለው አብልተው አጠጥተው እንዳይበርደኝ ተጨንቀው.... እንግዳም ይዤ ከሄድኩ ከእኔ በላይ ተቀብለው በክብር በደስታ አቆይተው ባርከው በርቱ ጸልዩ ብለው ጉልበት ኃይል ሰጥተው የሚሸኙ አባቴ ነበሩ።
በአንድ ወቅት ከእሳቸው ፍቃድ አግኝቼ የህይወት ታሪካቸው በድረ ገጼ መጻፍ ጀምሬ ነበር። ነገር ግን ገና አንድ ክፍል እንደ ጀምርኩ ሌሎች እሳቸውን የሚያውቁ አባቶች ጽሑፉን አይተው ኖሮ "ልጅ ብስራት ይህን ጽሑፍ ለጊዜው ተወው" ብለው እንድተወው ሆነ። የሚገርም የህይወት ታሪካቸው እንደፍላጎቴ እንደመሻቴ ተነባቢ ሳይሆን ቀረ።
(ማንበብ ለሚፈልግ የመጀመሪያው ክፍል ጽሑፍ አሁንም ድረስ አለ ከስር አስቀምጠዋለሁ።)
እግዚአብሔር ከፈቀደና በህይወት ከቆየሁ ወደፊት ታሪካቸውን በመጽሐፍ መልክ ለማውጣት እሞክራለሁ።
የአባ ኪዳነ ማርያም ስብዕና ሁሌም የሚስቀናኝና ሰው እግዚአብሔርን በዚህ መልክ በዚህ ደረጃ በዚህ ሁኔታ ለማገልገል እንዴት ይችላል የሚለውን ጥያቄዬን በሚገባ አሳምነው የሚመልሱልኝ ወጣት መናኝ ነበሩ። ፍጹም የተረጋጉ በይቅርታና በፈገግታ መንፈስ የሚኖሩ አባት።
ስለ ፌስቡክ ስለ ተለያዩ social media መድረኮች ብዙ ጊዜ እናወራ ነበር። በየጊዜው የዝቋላ ጫካ ሲቃጠል ብዙ ስራ ሰርተን ነበር። ጨለምተኛ እንዳልሆን በሁኔታዎች አስገዳጅነት ጥላቻ በውስጤ እንዳይኖር ብዙ ጊዜ የሚመልሱኝ እሳቸው ነበሩ።
አሁን እርሶን የመሰለ ከመንገድ መላሽ አባት የለኝም። ጎድያለሁ። ባጠፋም የሚመልሰኝ ያለ አይመስለኝም። ስለዚህም ዝም ብዬ መኖርን መርጫለሁ። ከሁሉም ነገር መሸሽን መርጫለሁ። እርሶ ፍጹም የሚጠየፉትን የዚህን መንግስት ወሬና የአጨብጫቢዎቹን ድምጽ ለመስማት የተበዳዮችን እንባ ለማየትና ለመስማት እዚህ መገኘትን አልሻም ፤ አልገኝም። በዚች አምስት ዓመታት ያሳለፋችሁን መከራና ስቃይ የሚያውቀው ያውቀዋል።
የእኔ አባት....😭😭😭
ዝቋላ አቡዬ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አባታችንን ብለን በብዙ ፈተናና መከራ ውስጥ አልፈን ለንግስ ለሱባዔ ስመጣ ስንመጣ አንድም ቀን ለምን መጣህ ለምን መጣችሁ ቶሎ ተመለስ ቶሎ ተመለሱ ብለውን ብለውኝ አያውቁም። ከዚህ ይልቅ የከተማ ጀግኖች ብለው ከመገረምና ከማበረታታት ውጪ....
ዘንድሮ ግን ባለቤቴን የጥቅምቱ አቦ ይዤ በበምጣቴ አቤትትት የተቆጡኝ ቁጣ ... አቤት ለምን መጣህ ለምን እሷንስ ይዘሃት መጣህ ብለው የተቆጡኝ ቁጣ። መቼም በህይወቴ አልረሳውም። ቶሎ ወደ አዲስ አበባ እንድንመለስ የገፋፉኝን ሁኔታ አሁን ሳስበው በወቅቱ ብዙ ነገር ችላችሁ ዝም እንዳላችሁ ብዙ መከራ እየተቀበላችሁ ሌሎች ምዕመናንን ግን የዚህ ፈተና መከራ ሞት እስር ተቋዳሽ እንዳይሆኑ ነበር። እንደዛ ተጨንቀው እንደዛ በሃሳብ ተይዘው እርሶ ቤት ለመጣ እንግዳ ሲጨነቁ አይቼ አላውቅም።
ይቅር ይበሉኝ አባቴ ይፍቱኝ አባቴ
መከራውንም ፈተናውም አብሬዎት ስላልተካፈልኩ...
አሁንም እኔ የማልረባው በእናንተ ቦታ ድፍት ያድርገኝ ብል ደስታዬ ነበር። እግዚአብሔር አይሳሳትም የሚያደርገውን የሚያውቅ አምላክ ነው ያለን። ባንበረታም መበርታት አለብን!
በረከታችሁ ይደርብኝ ይደርብን አሜን።
የጻድቁ የአቡነ ተክለሃይማኖት ፣ የዝቋላው ኮከብ የአቡዬ ወዳጅ የሆንሽው ድንግል ወላዲተ አምላክ እመ አምላክ ምነው የአስራት ሀገርሽን ኢትዮጵያን ተውሻትሳ?
የሀዘን ለቅሷችን ማብቂያ በአንቺ እጅ አይደለምን?
በቃችሁ ይበለን።
No comments:
Post a Comment