ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Thursday, September 21, 2017

መስከረም 10፡ ሥዕለ ጸዴንያ ማርያም

   ምንጭ፦ የመስከረም አሥር ሰንክሳር እና ተአምረ ማርያም  

     ጸዴንያ በምትባል ሀገር ማርታ የምትባል ደግ ሴት ነበረች፡፡ ይህች ደግ ሴት በቤቷ ትልቅ አዳራሽ ሰርታ እንግዶችን እንደ አባታችን አብርሃም
ተቀብላ አብለታ አጠጥታ ማደሪያ ቦታም ሰጥታ ታስተናግድ ነበር፡፡ አባ ቴዎድሮስ የሚባል ኢትዮጵያዊ መነኩሴ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሔድ
መሽቶበት ከማርታ ቤት በእንግድነት አድረ ጠዋት ለመሔድ ሲነሣ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ሲነግራት የእመቤታችንን ሥዕል ገዝተህ
አምጣልኝ ዋጋውን ልስጥህ አለችው፡፡ ገንዘቡን ሥዕሉ ን ሳመጣልሽ ትሰጪኛለሽ ብሏት ሄደ፡፡

         ቅዱሳት ቦታዎችን (መካናትን) ተሳልሞ ሥዕሉን ረስቶ ሳይገዛ ሲመለስ « አደራ ጥብቅ አይደለምን? ያቺ ሴት አደራ ያለችህን ለምን ረሳህ» የሚል
ድምጽ ሰማ ተመልሶ ሄዶ ገዝቶ በረሃ በረሃውን መጓዝ ጀመረ፡፡
በመንገድም እየተጓዘ አንበሳ ሊበላው አየሮጠ ወደ እሱ ሲመጣበት አየ መነኩሴው አንበሳውን ከመፍራት የተነሣ ደነገጠ ተንቀጠቀጠ ደንግጦ
ቁሞ ሳለ ያች ሥዕል ከአንበሳው ጩኸት ሰባት እጅ በሚበልጥ አስፈሪ ድምጽ ጩሃ ተናገረች፡፡ ያን ጊዜ አንበሳው ደንግጦ ፈጥኖ ሸሸ፡፡
መነኩሴውም መንገዱን ቀጠለ፡፡ በመንገዱም ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ወጥተው ወንበዴዎች ሊቀሙትና ሊገድሉት ከበቡት፡፡ ከሥዕለ
ማርያሟም እንደ መብረቅ ያለ ታላቅ ቃል ወጣ ፡፡ ወንበዴዎችም እጅግ ፈርተው ሸሽተው ከጫካው ውስጥ ገቡ፡፡

ያም መነኩሴ እኝህን የሚያስደንቁ ተአምራት በሰማና ባየ ጊዜ በልቡ « ለእኔ ረዳት ትሆነኝ ዘንድ ወደ ሀገሬ ይዣት እሄዳለሁ እንጂ ለላከችኝ
ሴት አልሰጥም» ብሎ ወደ ሀገሩ ሊሄድ በመርከብ ተሳፈረ፡፡ በባሕር ላይም ሳለ ጽኑ ነፋስ ተነስቶ መርከቡን እየገፋ ማርታ ወዳለችበት
ሀገር ወደ ጼዴንያ ዳርቻ አደረሰው፡፡ ማደሪያም ስለሌለው ወደ ደጓ ሴት ወደ ማርታ ቤት ከእንግዶች ጋር አብሮ ገብቶ አደረ፡፡


ሲነጋ ወጥቶ ሊሔድ ከደጃፍ ሲደርስ ደጃፉ ጠፍቶት ከአጥሩ ሲታገል ዋለ፡፡ ማርታም «አባቴ ያመመህ የደከመህ ትመስላለህ ዛሬ ደግሞ እዚህ እደርና ነገ
ትሔዳለህ» አለችውና አደረ፡፡ በሁለኛውም ዕለት እንደ መጀመሪያው ቀን በሩን አልፎ መሄድ አቃተውና እዚያው ማርታ ቤት አደረ፡፡ በሦስተኛው
ቀን መውጣት ፈልጐ ከአጥሩ ጋር ሲታገል አይታ «አባቴ የሆንከው ምንድነው እነሆ ዛሬ ሦስተኛ ቀንህ ነው፡፡» አለችው፡፡ መነኩሴውም «
ይህችን ተአምረኛ ሥዕል አልሰጥም ብዬ ነው፡፡ እኔኮ ሥዕል ከኢየሩሳሌም ግዛልኝ ያልሽኝ መነኩሴ ነኝ» ብሎ ሥዕለ ማርያምን
አውጥቶ ሰጣት፡፡

 እርሷም እጅግ በጣም ተደስታ እግዚአብሔርን አመሰገነች፡፡ በሥዕሏም ፊት ሰግዳ ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም
ምስጋናን አቀረበች፡፡ ተቀብላም የተጠቀለለችበትን ልብስ ስትፈታ ፈሳሽ ወዝ ከስዕሊቱ ሲንጠፈጠፍ አገኘች። ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የዚያን መነኩሴ እጆቹንና እግሮቹን ሳመች። ከዚህም በኋላ ያቺን ሥዕል ወደ ጸሎት ቤቷ ወስዳ በታላቅ ክብር የምትቀመጥበትን አዘጋጅታ አኖረቻት ማንም
እንዳይዳስሳትም የነሐስን መስኮትን ሰራችላት። በሌሊት የሚያበሩ መቅረዞችን በፊቷ ሰቀለች። ከመቅረዞችም ውጭ የሐር ፡ መጋረጃን
ጋረደች ከሥዕሊቱ እየተንጠፈጠፈ የሚወርደው የወዝ ቅባት የሚጠራቀምበት ከዕብነ በረድ የተሰራ ወጭት አኖረች። ያም መነኮስ
እስከሚሞትበት ቀን ፡ ድረስ ፡ የእመቤታችንን ድንግል ማርያምን ሥዕል እያገለገለ ኖረ።

            የሀገሩም ሊቀ ጳጳሳት የዚያችን ሥዕል ዜና በሰማ ጊዜ ከኤጲስቆጶሳትና ከካህናት ከሕዝቡም ሁሉ ጋር መጣ በሠሌዳም ውስጥ ሆና አገኙዋት
ከዚህ ከአምላካዊ ግብር የተነሣ አደነቁ። ከዚያም ቅባት ቀድተው ለበረከት በተካፈሉ ጊዜ ወዲያውኑ በውጭቱ ውስጥ ይሞላል። ወደ ሌላ
ቦታ ሊወስዷት በፈለጉ ጊዜ ንውጽውጽታ ሁኖ ብዙዎች በድንጋጤ ወደቁ ሥዕሊቱም እስከ ዛሬ በዚያች አገር ትኖራለች። ይህችም ሥዕል ቅዱስ ሉቃስ የሳላት ናት ሥጋ የለበሰች ትመስላለች፡፡ ከፊቷም ወዝ ይንጠባጠባል፡፡ በዚህችም ሥዕለ ብዙ ተአምራት ተደረገ
ሕሙማን ተፈወሱ ዓይነ ስውራን ማየት ቻሉ፡፡

         በዚያ ዘመን የነበረው ሊቀ ጳጳስ ተአምሯን ሰምቶ ሥዕሏ ወደ ማርታ ቤት የገባችበት ዕለት መስከረም 10 ቀን እንዲከበር ሥርዓት ሠራ፡፡

እግዚአብሔር አምላክ የእመቤታችንን ፍቅሯን በልቦናችን ጣዕሟንባንደበታችን ያሳድርብን። አሜን።


No comments:

Post a Comment