አባታችን አቡነ ሳሙኤል ደብረ ዓባይንና ዋልድባን ያቀኑ ታላቅ ጻድቅ ሲሆኑ የተወለዱት ቦታም በትግራይ ክፍለ ሀገር በርዕሰ ገዳማት ወአድባራት አክሱም ጽዮን በ 1298 ዓ.ም ከአክሱም ባላባቶች እና ካህናት እንዲሁም የአክሱም ጽዮን ገበዝ ከሚሆን ከጌዴዎን ዘር ከእስጢፋኖስና ከዓመተ ማርያም ተወለዱ።
በተወለዱም በ7 ዓመታቸው ወደ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተው በአጭር ጊዜ ትምህርታቸውን አጠናቀው በ 1314 ዓ.ም መንነው ወደ ደብረ በንኮል ገዳም ገብተው በአቡነ መድኃኒነ እግዚእ እጅ መነኮሱ። በደብረ በንኮል 3 ዓመት በርድና 9 ዓመት በምንኩስና ጠቅላላው 12 ዓመት አገለገሉ። ከዚያ በኋላ ከዚያ ወጥተው ወደ በጌምድር በመሄድ በወይና ፣ በመንዳባ ፣ በዞዝ ፣ በአዘዞና በአብጠራ ወዘተ እየተዘዋወሩ በየዋሻው ሱባዔ እየገቡ በጾም በጸሎት በስግደት በአርምሞ በተለያየ ገድል 19 ዓመት ከተቀመጡ በኋላ ወደ ሽሬ አውራጃ ተመልሰው በየቦታው እየተዘዋወሩ የገበሬዎችን ዘር እየባረኩ ሕሙማንን እየፈወሱ ሙታንን እያስነሱ ትምህርተ ወንጌልን እየሰበኩ ብዙ ሕዝብን ካሳመኑ በኋላ በ1353 ዓ.ም ወደ ደብረ ዓባይ ገቡ። ገብተውም የቦታውን ጽሙናና የቦታውን ስፋት አይተው በጣም ተደስተው ሱባዔ ቢገቡ ብዙ ተአምራት ተደርጎላቸዋል።ከተአምራቶቹም ጥቂቶቹ ውዳሴ ማርያምን እና ቅዳሴ ማርያምን ደግመው ውሃውን ቢባርኩት ኅብስት ሆኖላቸው አርድእቶቻቸውን መግበዋል።
እስከ ዛሬ ድረስ ገዳሙ የሚገለገልበት "ማይ ምንጭ" የሚባለውን ውሃ ባርከው አፍልቀዋል። ቅዱስ ሚካኤል ወደ ሰማይ አሳርጎ የሰማይ መኖሪያቸውን አሳይቷቸዋል። እራሱ ጌታችንም ከንጽሕት እናቱና ከአእላፍ መላእክት ጋር ሰማያዊ የመድኃኔዓለም ታቦትን ይዞ መጥቶ ሰጥቷቸው ይህች ቦታ ቦታህና መካነ ርስትህ ናት ብሎ ቃል በቃል ተነጋግሯቸው ዐርጓል።
በተነጋገሩበት ቦታ የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተሰርቶበት እስከ ዛሬ ድረስ ይገኛል።