ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Tuesday, December 12, 2017

በዓታ ለማርያም ( በኣታ ማርያም )

   
  በተዋህዶ እምነታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም በምናምነው ዕምነት ሌሎች ከሚቀበሉትና ከሚያምኑት ልዩ ከሚያደርጉት ዓበይት ነጥቦች፦
* በጥፋት መርገም ከአዳም የወረደ የዘር ኃጥያት ያልተላለፈባት ቅድስተ ቅዱሳን
* አስራ ሁለት ዓመት በቤተመቅደስ ማደጓ
* በንፅሕና የተዘጋጀች ፣ በቅድስና ያጌጠች ፣ ቅድመ ፀኒስ ፡ ጊዜ ፀኒስ : ቅድመ ወሊድ : ድኅረ ወሊድ በፍፁም ድንግልና የፀናች ማህተመ ድንግልናዋ የማይናወጥ ዘላለማዊት ድንግል መሆኗን ማመንና ማስተማር ነው።

    የዓለማት ፈጣሪ ልዑል እግዚአብሔር «በልዕልና ሆኖ ተመለከተ: ሁሉ እንደፈረሰ ጆሮ : እንደ ጦር ጎረሮ ተሰተካክሎ በደለ : በጎ ነገርን የሚሰራት የለም» (መዝ, 52) ተብሎ በተነገረለት ትውልድ በአዳም ዘር መካከል በእሾህ ውስጥ እንደ አጌጠች ፅጌሬዳ : በመዓዛ ቅድስና የተጠበቀች ንፅሕ ነፍስ: ንፅሕ ስጋን: ንፅሕ ልቡናን ይዛ የተገኘች የንጉስ ክርስቶስ መቅደስ ድንግል ማርያም ከሁሉ ትበልጣለች… ከሁሉ ትከብራለች። « መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ » ናት። ከፈጠራት ጀምሮ ስጋዊ ሀሳብ በህሊናዋ ያልተመላለሰ… ከሐልዩ ከነቢብ… ከገቢር የነፃች እናትነትን ከድንግልና አስተባብራ የተገኘች የደናግል መመኪያ ናት።


    « ልጄ ሆይ ስሚ… ምክሬን አድምጪ ንጉስ (ክርስቶስ) ማደሪያው ልትሆኚ ደም ግባትሽን (ቅድስናሽን) ወዶአልና ዘመድሽን እርሺ» (መዝ, 44: 10) ተብሎ በነቢይ እንደተነገረ ለእናትና አባቷ የብፅዕት ልጅ የሆነችው ድንግል ማርያም ሆዷ ዘመድ ሳይወድ… አፏ እህል ሳይለምድ ከእናቷ እቅፍ ተወስዳ ስላሴን እንደአባት … እንደ እናት መላዕክትንእንደእህት እንደወንድም አድርጋ በቤተመቅደስ ያደገች «እህተ መላዕክት» ናት።

ልጆችን ለቤተ እግዚአብሔር መስጠት… በቤተመቅደስ እግዚአብሔርን እያገለገሉ እንዲያድጉ ማድረግ የልጅ በረከት ለማግኘት የሚናፍቁና እግዚአብሔርን ደጅ የሚጠኑ አማንያን እምነትና ልማድ ነው። እነ ሳሙኤልን የመሳሰሉ ነቢያት ሁሉ በቤተመቅደስ ያደጉ ናቸው።
እመቤታችን ድንግል ማርያም ከሶስተኛ ዕድሜዋ ጀምሮ ከግብር አምላካዊ ከሰማይ የተገኘ ሕብስትን እየተመገበች… ከሰማይ መጠጥን እየጠጣች…ሐርና ወርቅ እያስማማች እየፈተለች በመላዕክት ሞግዚትነት በቤተ መቅደስ ያደገች… በንፅህና በቅድስና የተሸለመች የሰማይና የምድር ማደሪያ (ታቦት) ናት። ንፅሕተ ንፁሐን ድንግል ማርያም እንደዓለም ሴቶች ልጆች በሳቅና ስላቅ … በቧልትና ጨዋታ ያደገች አይደለችም።


      ቤተመቅደስ የገባችበትና መልዓኩ ፋኑኤል በአንድ ክንፉ ህብስትና ፅዋዕ አቅርቦ አንድ ክንፉን ጋርዶ በመመገብ ቤተመቅደስ ቆይታዋ በእግዚአብሔር ፍቃድ መሆኑ የተረጋገጠበት በመሆኑ ታኅሳስ 3 ቀን በየዓመቱ በቤተክርስቲያናችን በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።

በዔሊ ልጆች ኃጥያትና በደል በምርኮ ቆይታ በኃይል ፅዮን ወደ ቤተመቅደስ
እንደተመለሰች ሁሉ አማናዊት ታቦት ቅድስት እመቤታችንም በእናትና አባቷ ቤት ሶስት ዓመት ከኖረች በኋላ ወደ ቤተመቅደስ ገብታለች። « በአታ ለማርያም» ማለት ይኸው ነው ። የማርያም ቤተመቅደስ መግባት ማለት ነው።
እንኳን አደረሳችሁ።

1 comment:

  1. What does the word በኣታ literary mean on itself?

    ReplyDelete