ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡
Showing posts with label ከፀሐፊዎቹ. Show all posts
Showing posts with label ከፀሐፊዎቹ. Show all posts

Monday, September 9, 2013

አንተ ነህ መስከረም

                                                            በገብረክርስቶስ ደስታ

ማለቂያ በሌለው ደማቅ ሰማያዊ፣
ከሩቅ ያለው ጋራ ተነክሮ ሐምራዊ፡፡
በዚያ ላይ ደመናው እንደ ጥጥ ተነድፎ፣
እየተራራቀ ሲያንጃብብ ተቃቅፎ፡፡
አንተ ነህ መስከረም፣
የሐምሌን ጨለማ የነሐሴን ዝናም፣
የሻርከው አንተ ነህ፣
በብርሃን ውበትህ፡፡
በክረምቱ ወራት ሰማዩን ያስጌጠው፣
የማርያም መቀነት በቀለም ያበደው፡፡
ጤዛው አርሶታል መሬቱ ላይ ለቆ፣
በቀይና ብጫ መስኩ ተለቅልቆ፡፡
ወንዝና ጅረቱ ድንጋይና አፈሩ፣
ሀገሩ ውብ ሆኗል ሜዳው ሸንተረሩ፡፡
ዕንቁጣጣሽ አንተ ስጦታህ የበዛ፣
ለሰው መታሰቢያ ውበት የምትገዛ፡፡

Monday, April 29, 2013

ሆሣዕና በአርያም …!!!


ፀሐፊ ፡- ፍቅር ለይኩን፡፡
READ IN PDF


         ‹‹ሆሣዕና›› ቃሉ የዕብራይስጥ ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹አሁን አድን›› ማለት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ከፋሲካ በፊት ያለው እሁድ የሆሣዕና እሁድ በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ ዕለትም በቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው መዝሙር፣ ማኅሌቱ፣ ቅዳሴውና ማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት ዕለቱ በታላቅና እጅግ ደማቅ በሆነ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት የሚዘከርበት ነው፡፡ ይህ በዓል እጅግ በደማቅና ልብን በሚመስጥ መንፈሳዊ ሥርዓትና ድምቀት ከሚከበርባቸው ቅዱሳን ገዳማትና መካናት መካከል የአክሱሟ ርዕሰ አድባራት ጽዮን ማርያም እና በዚህ በአዲስ አበባችን ደግሞ የእንጦጦ ማርያም በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ሆሣዕና የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ወደ ኢሩሳሌም በታላቅ ድል የገባበት ዕለት ነው፡፡ አስቀድሞ በመጽሐፍ ቅዱስ በነቢዩ ዘካርያስ፡‹‹ለጽዮን ልጅ፡- እነሆ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያቱ ግልገል በውርንጭላይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት፡፡›› ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ፡፡ ጌታ፣ አምላክና መድኃኒት የሆነው ኢየሱስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡

Saturday, April 27, 2013

ፋሲካ፦ “ሥጋዊ ወመንፈሳዊ”


ፀሐፊ፡ ኤፍሬም እሸቴ  
  

(ኤፍሬም እሸቴ - ኢትዮጵያዊ)

         በኢትዮጵያውያን ዘንድ በታላቅ ሁኔታ ከሚከበሩት በዓላት መካከል ትንሣኤ ወይም ፋሲካ አንዱና ዋነኛው ነው። ሃይማኖታዊ ትርጓሜው እና ምንነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ባህላዊ አከባበሩ እና ምንነቱም ከኢትዮጵያውያን ባህላዊ ማንነት ጋር በጥልቅ የተያያዘ ነው። እንኳን በአገር ቤት ያለው በሰው አገር ያለነውም እንኳን ብንሆን እንደ አቅሚቲ የአገር ቤቱን መንፈስ በያዘ ሁኔታ እናከብራለን። ስለዚህ ፋሲካው መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን ሥጋዊ/ ባህላዊ አንድምታው ከፍ ያለ ነው ማለት ነው።
አለቃ ዘነብ የተባለው የአጼ ቴዎድሮስ ታሪክ ፀሐፊ አንባቢውን እያዋዛ የመከረበትንመጽሐፈ ጨዋታየተሰኘውን መጽሐፉንሥጋዊ ወመንፈሳዊ” (ሥጋዊ እና መንፈሳዊ) እንዳለው ስለ ፋሲካ ያለችኝን ወግ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ ብዬ ብከፍላት ኋላ ለሚከተለው ሐሳብ ጥሩ ገላጭ ይሆናል። ዘነብ ኢትዮጵያዊ ሲል ራሱን እንደገለጸ ኩረጃዬን ሙሉ ለማድረግ ኤፍሬም ኢትዮጵያዊ ብያለሁ፣ ቢያንስ ለዚህ ጽሑፍ። ኢትዮጵያዊነታችንን ከፍ አድርገን በክብር ልናሳይ የሚገባበት ዘመንም ስለሆነ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይሆንልኛል።
በጥንተ ታሪኩ ፋሲካ የሚጀምረው ከእስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነጻ የመውጣት ታሪክ ታሪክ ጋር ተያይዞ ነው። ሕዝበ እስራኤል ለረዥም ዘመን በግብጽ አገር በባርነት ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ በቤተ መንግሥቱ ያደገው ሙሴ መሪ ሆኗቸው ወደ አገራቸው ለመመለስ የጀመሩትን ጉዞ መሠረት ያደረገ በዓል ነው። ግብጻዊው ገዢ የሚያየውን ተአምራት ተቀብሎ ሕዝቡን ሊለቅ እና ነጻነታቸውን ሊመልስላቸው ባለመፍቀዱ ከተከሰተው ከባዱ ቅጣት ማለትም የግብጻውያኑ የበኩር ልጆች መቅሰፍታዊ ሞት ጋር ይገናኛል።

Wednesday, April 24, 2013

አገርን ፍለጋ

ፀሐፊ፡- ዮሴፍ ይልማ
yilmajoseph_1978@yahoo.com
የጨርቋን ጫፍ ጥለት፣
በአቧራ ነትቦ ባንዲራ ያለበት፡፡
ጭምድ አርጎ ይዞ ህፃኑ ጠየቀ
ግራ ቀኝ እያየ እየተሳቀቀ
አገራችሁ ሂዱሰዎቹ የሚሉን
የት ነው አገራችን?
ጥለትሽ ላይ ያለው ያገርሽ መለያ
የት ናት ኢትዮጵያ?
የት ጋር ተጀምራ የት ጋር ነውምታልቀው?
አፈርና ወንዙ ባህል ሐይማኖቱ የት ጋር ነውሚለየው?
እዚህ አይደለችም? ወደምንሄድበት እዚያ ናት ኢትዮጵያ?
ወጥተን ነበር እንዴ ከናታቻን ጉያ?
ውስጥ ሆነን ውጭ ነበርን?
እንደዚ ጨክነው አጣድፈዉሚገፉን
ወዴት ነው ምንሄደው?
ወዴት ናት አገሬ?

Thursday, April 4, 2013

ደብረ ዘይት ፡- የዓለማችን ታሪክ ፍፃሜ ቅዱስ ተራራ


ፀሐፊ፡- በፍቅር ለይኩን

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ቀኖና መሠረት የዓብይ ጾም ወይም የሑዳዴ ጾም አምስተኛ ሳምንት ‹‹ደብረ ዘይት›› በመባል ይጠራል፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት አስተምህሮ የዓብይ ጾም ሳምንታት በሙሉ ከክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ታሪክ ጋር የተያያዘ የራሳቸው የሆነ ስያሜ አላቸው፡፡
የዚህ ስያሜ አመንጪም የ6ኛው መቶ ክ/ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቅና የዜማ ደራሲ የሆነው ቅዱስ ያሬድ እንደሆነ ነው የታሪክ ድርሳናት የሚመሰክሩት፡፡ ገና አውሮፓና እስያ በከፊል፣ አሜሪካና እንዲሁም የተቀረው የዓለማችን ክፍል በሙሉ ባልነበሩበትና ወንጌልን ባልሰሙበት በዛ የጥንት ዘመን ኢትዮጵያውያን ታላላቅ የሆኑና ዓለምን ዕፁብ ድንቅ ያሰኙ የሥነ ሕንጻ ጥበብና ክህሎት የተንጸባረቀባቸው ቤተ መቅደሶችን ገንብተው፣ መጽሐፍትን መርምረው፣ ዜማ ደርሰው፣ ቅኔ ፈጥረው ልዩ በሆነ መንፈሳዊ ሥርዓት ለረዥም ዘመናት አምላካቸውን ሲያመልኩ ቆይተዋል፡፡

አውሮፓ የሙዚቃ ኖታ ለመፍጠር አይደደለም ገና እንኳን ለማሰብ ባልደፈሩበት በጥንቱ ዘመን ቅዱስ ያሬድ ከሺሕ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ዜማ ከነምልክቱ ወይም ኖታው በቀመር ዛሬ ዓለም የሚደነቅበትን ሰማያዊና መንፈሳዊ ምሥጢር ያለበትን የቤተ ክርስቲያኒቱን አምልኮተ ሥርዓት መሠረት ለመጣል ችሏል፡፡

Thursday, August 2, 2012

Conversation with Myself:- ድንቅ መጽሐፍ፡፡


የፍቅር ኃያልነት፣ የይቅርታ ታላቅነት፣ የነጻነት ክብር... የተገለጸበት                   
ፀሐፊ፡ በፍቅር ለይኩን፡፡
[
fikirbefikir@gmail.com/befikir12@yahoo.com]

‹‹Winn my love as it drifted slowly away with you, I felt all alone in the world and the books that fill my cell, which have kept me company all these years, seemed mute and unresponsive.›› -ማንዴላ ለውድ ባለቤታቸው ለዊኒ ከጻፉት የፍቅር ደብዳቤ የተወሰደ፡፡
   ውድ ፍቅሬ ዊኒ… የቀዝቃዛውን የአትላንቲክ ውቅያኖስን ተጎራብቶ በሮቢን ደሴት በተገነባውና እድሜዎቻቸው እንደ ባቢሎን ግንብ በረዘሙ ቅጥሮች እስር ቤት ተጥዬ፣ አውሬ በሚመስሉ አስፈሪ ውሾችና  በአፓርታይድ ነጭ ፖሊሶች እንደ ነፍሰ ገዳይ በዓይነ ቁራኛ በምጠበቅበት በዛች ጠባቧ እስር ቤት ውስጥ ከማንም ጋር እንዳልገናኝ ባለተፈቀደበትና ከአንቺ ከውድ ባለቤቴና ፍቅሬ ጋር እንኳን በየስድስት ወሩ ለ30 ደቂቃ ብቻ እንድትጠይቂኝ በዘረኛው የአፓርታይድ መንግሥት ተፈርዶብን፤ ለአንቺ የምልከው የናፍቆት ደብዳቤዬ

Tuesday, July 24, 2012

‹‹ ኦፒየም ›› በየዓይነቱ በኢትዮጵያ።


ምድርን ሁሉ ካሰከረች የወርቅ ፅዋ መጎንጨት ይብቃ፡፡
ከመልካሙ መንገድ እንዳይወጣ ቅዱሳን መጻሕፍት ለኢትዮጵያዊው ያቆዩለት ማስጠንቀቂያ ፥

የእግዚአብሔርን መንገድ ብትተው፥ 

  •    የማታውቀው ጠላት የምድርህንና የድካምህን አዝመራ ይበላል:: [']
  •    በሬህ በፊትህ ይታረዳል፥ ከእርሱም አትበላም፤ አህያህ ከእጅህ በግድ ይወሰዳል፥ ወደ አንተም አይመለስም፤ በግህ ለጠላቶችህ ትሰጣለች፥ የሚረዳህም አታገኝም።[']
ተመክሮ፥ ምእራባውያን እና ኦፒየም በቻይና።

     አንድ የማውቀው የእስያ ሰው ሆንግ ኮንግ ዘመዶቹን ጠይቆ እንደተመለሰ አገኘሁትና ስንጨዋወት "አንተ የምን አገር ሰው ነው የምትባለው?" ብየ ጠየቅሁት። እሱም "የቻይና" አለኝ። አከታትሎም ስለ ሆንግ ኮንግ ታሪክ አጫወተኝ። በምእራባውያን የተጻፈ ታሪክ በማንበብ ስለ ቻይና የተወሰነ እውቀት ቢኖረኝም፡ ስለ ሆንግ ኮንግ ልዩ አስተዳደርና፣ እንዴት  ከቻይና ተነጥላ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛትነት እንደኖረች ሲያጫውተኝ፡ የሆንግ ኮንግን እና የቻይናን ታሪክ ከቻይና ሰው በመስማቴ ተመስጨ በጥሞና አዳመጥኩት። እንዲህም አለኝ፥

Tuesday, July 3, 2012

ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል፡፡

የስዊድን ስቶክሆልም ካህን ለፃፉት ፅሑፍ የተሠጠ ምላሽ
ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል፡፡

ፀሐፊ፡ ብርሃነ ስላሴ

       ይህን ፅሑፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ በደጀ ሰላም ድረ-ገፅ ላይ በወጣው ሽምጥጥ ያለ ውሸት በመፃፉ ነው፡፡ ውሸት በቅዱስ መፅሐፍ ‹‹ አቡሀ ለሐሰት›› የሐሰት አባቷ ሰይጣን ነው ይላል ( የሐ.8፡44 ፤ የሐ.ሥራ 5፡3 ፤1ኛ ጢሞ. 4፡1 ፤ራእ. 12፡9)፡፡ እውነትን ማጣመም ፣ሐቅን መደበቅ ፣ያልተደረገ ታሪክን ተደረገ ብሎ ሽምጥጥ አድርጎ ፈጥሮ መፃፍና ማውራት፤ሐቅን መካድና በተጨማሪም መንፈሳዊና ማኀበራዊ ኑሮን ማደናቀፍና እንዲፈራርሱ ማድረግ በተለይም የተለይም የተደራጀውን ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰላትን ቤተክርስቲያን  (ምህመናንን) ለማፍረስ መነሳት፤ የሐሰት አባት የተባለው የሚያሰራው ነው፡፡ከሁሉ በላይ ደግሞ ፍርሃትና በራስ አለመተማመን ለውሸት ዋና መንገዶች ናቸው፡፡ እንደዚህ ሆኖ የኖረ ሰው ሁሉን ጠርጣሪ በመሆኑ ኑሮው በሙሉ ሰውን ሳያምን እሱም ሳይታመን ይኖራል፡፡ ይህ ባህሪይ ያለበት ሰው መንፈሳዊ በመሆን፣በመፀለይ፣ ቅዱስ መፅሐፍን በመማርና በማጥናት ሊለወጥ ይችላል፡፡ (ሐሰት ግዕዙ ሲሆን ውሸት አማርኛ ነው፡፡)
በሚያዝያ 27 ቀን 2004 ዓ.ም. በደጀ ሰላም ድረ-ገፅ የወጣው የግለሰቡ ፅሑፍ ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ ለዚህ የሐሰት መልስ ለመስጠት አርዕስቱን ‹‹ ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል›› በማለት በመገረምና በማዘን ለመፃፍ ተገደድኩ፡፡ ከዚህ በውሸት ከጎደፈው ፅሑፍ ውስጥ በተለይ እንዲህ የሚል ቃል አገኘሁ፡፡
   ‹‹ በቧገታ( ለማኞች ማለት ነው) ወይም በሸመታ ካህናት ከለንደንና ከአንዳንድ ሀገሮች ነጋዴና አትራፊ ካህናት ጋር ግንኙነት በመፍጠር. . . . . . . ›› ይላል፡፡
ውሸት እውነት ሆኖ በታሪክነት እንዳይቀር እውነቱን በዳኝነት መፃፍ አለብኝ ብዬም ከህሊናዬ ጋር ተሟገትኩ፡፡

Sunday, July 1, 2012

ዘረኝነት ኢ-ክርስቲያናዊ የሆነ ተዛማችና ክፉ ወረርሽኝ ነው፡፡


ፀሐፊ፡ ፍቅር ለይኩን፡፡

         ለዚህ ጹሑፍ መነሻ የሆነኝ በደጀ ብርሃን ብሎግ ላይ የተስተናገደው ናኦድ ቤተ-ሥላሴ በዘረኝነት/በጎጠኝነት ዙሪያ ያስነበበው ምሬት የተቀላቀለበት አጭር መጣጥፍ ነው፡፡ የ1997ቱን ድኅረ ምርጫን ተከትሎ በሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ደም አፋሳሽ ግጭትና ቀውስ ምክንያት እስከ አሁን ድረስ ምክንያቱ ባልገባኝና ምላሽ በላገኘሁበት በወቅቱ በነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከኢትዮጵያውያን የረጅም ዘመን የማኅበራዊ ኑሮና የአብሮነት እሴቶችና ዋጋዎች በተቃረነ መልኩ «ከትግራውያን ጋር ለቅሶ አትደራረሱ እሳትም አትጫጫሩ…» እስከሚል የዘለቀ መመሪያ መሰል አዋጅ ተላልፎ ነበር፡፡
እናም በዚሁ አዋጅ ጦስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለን የክፍል ጓደኛዬ የሆነች ከአክሱም የመጣች ወጣት ሴት ለሦስት ዓመታት በቆየችበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማደሪያ ክፍሏ ያሉ ከሌሎች ክልሎች የመጡ ጓደኞቿ እንዳገለሏትና ሰላምታ እንኳን እንደነፈጓት የነገረችኝ እንባዋ በሁለቱ ጉንጮቿ እየወረዱ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንድ እና ግልጽ ነው የትግራይ ልጅ በመሆኗ ነበር፡፡ ዘረኝነት ባለ ብዙ መልክ ነው መገለጫውም የዛኑ ያህል ደግሞ ውስብስብና ባለ ብዙ ኅብር ነው፡፡
በዘረኝነት ዙሪያ ብዙ አከራካሪ የሆኑ መጽሐፍቶችና የምርምር ጥናት ጹሑፎች ለንባብ በቅተዋል፡፡ የሰው ልጆችን አመጣጥና ታሪክ በሚያጠኑ ሰዎች መካከልም ይኸው የዘር ጉዳይ ብዙ አወዛጋቢ ክርክሮችንና አለመግባባቶችን ያስነሳ ጉዳይ ነው፡፡ ወደዛ ሰፊ ክርክርና ሙግት ለመግባት አልሻም፡፡ ይሁንና ለበርካታ መቶ ዓመታት በዚሁ ዘረኝነት ጠንቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካንና አፍሪካውያንን ላይ ታሪክ በጥቁር መዝገቡ የከተበው ዘግናኝና አሳፋሪ ስደት፣ ሞትና እልቂት በአፍሪካውያን ሕዝቦች ላይ ደርሷል፣ አሁንም በምድራችን የዚሁ የዘረኝነት ጦስ ደፋው ገና ተከፍሎ ያበቃ አይመስልም፡፡

Tuesday, June 19, 2012

ይድረስ በአባቶቻችን ላይ የስደብና የማዋረድ ዘመቻ ለከፈታችሁ ብሎጎች፡-

‹‹ደፋሮችና ኩሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም፣ ዳሩ ግን መላእክት በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ በጌታ ፊት በእነርሱ ዘንድ የስድብን ፍርድ አያመጡም…፡፡›› ፪ጴጥ ፪፣፲፩፡፡

ፀሐፊ፡ ፍቅር ለይኩን፡፡
********************************************************************

       አባቶችን ማዋረድ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር ማዋረድ ህልውናዋንስ መዳፈር እንደሆነ አታውቁምን…?!

መንፈሳዊ ድባብ ያላቸው የሚመስሉና ግን መንፈሳዊ ወዝና ሽታን የተራቆቱ በቤተ ክርስቲያን ስም በተከፈቱ መጦመሪያ መድረኮችና ድረ-ገጾች ዛሬ በእኛ ዘመን በአባቶች ላይ እየወረደው ያለው ስድብና እርግማን፣ እየተገለጸ ያለው ገመና ጆሮን ጭው የሚያደርግ ነው፡፡ እንዲህ የቤተ ክርስቲያኒቱን ገበና ለአደባባይ በማብቃትስ የሚገኘው ትርፍና ጥቅም ምንድን ነው? እባካችሁ ቆም ብለን እናስብ፣ እናስተውል እንጂ ወገን፡፡ ምን ዓይነት ድፍረት ምን ዓይነት ዝቅጠት ነው ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የተባሉትን ሊቀ ጳጳስ- የአንተ ያለህ…! ‹‹ቀውስ እና ጦስ›› ናቸው ብሎ መጻፍና ማዋረድ፤ ሰውን ያህል ክቡር ፍጥረት ብፁዕ አቡነ አብርሃምን ‹‹የጉድ ሙዳይ›› በማለት የመንፈሳዊነቱ ክብር ቢቀር ከሰብአዊ ክብር ማውረድ፣ ይህ በምንም ዓይነት መለኪያ፣ በምንም ዓይነት መንገድ ክርስቲያናዊነት ሊባል ይችላል፣ በምንስ መስፈርት ሞራላዊና ግብረ ገብነት ሊሆን ይችላል???

ታዲያ እኔ ምንድር ነኝ? ማነኝ?

ፀሐፊ፡ በ ኢትዮጵያዊው ፍቅረ መድኅን 

አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ጠየቀ፡-
 ምንድር ነኝ? ማነኝ? መለሰም፡-
አንደኛ - የሥላሴ ፍጡር ፣ ሰው ነኝ፡፡
ሁለተኛ - ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡
ሦስተኛ፣ አራተኛ… እያለ ወደላይም ወደታችም፣ወደፊትም ወደኋላም፣ወደግራም ወደቀኝም ሊሳብ እና ሊቀጥል ይችላል፡፡ቁም ነገሩ ወደፊት ማራመዱ ፣ሰውን ኹሉ በሰውነት አንድነቱ መቀበሉ ነው፡፡እኔ ደግሞ እንደ ሰውነቴ በአገሬ ሆኜ ምንድር ነኝ? ማነኝ? ስል ጠየቅኹ፡፡ስለዛም ‘ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡’ አልኩ፡፡
 ቋንቋዬ ያ ወይንም ይሄ ሊኾን ይችላል፡፡

አባቴ፣እናቱ አባታቸው ኦሮሞ እናታቸው ደግሞ አማራ እንደኾኑ ይናገሩ እንደነበር ይናገራል፡፡አባቱ ደግሞ አባታቸው ትግሬ እናታቸው ሳሆ እንደነበሩ ሰምቷል፡፡
 እናቴ፣አባቷ በአባቱ ጉራጌ በእናቱ ደግሞ የሸዋ ኦሮሞ እንደኾነ ነግሯታል፡፡ እናቷ ደግሞ አባቷ አማራ እናቷ አገው እንደኾኑ ነግራታለች፡፡ኸረ ለኛም ለልጅ ልጆቿ ነግራናለች፡፡አዎ አስታውሳለሁ፡፡ነፍሱን ይማርና ያባቴንም አባት እንዲሁ፡፡ 

Sunday, May 27, 2012

ይድረስ ለኢትዮጵያውያንና ለኤርትራውያን!

CLICK HERE FOR PDF

     አደይ ኢትዮጵያ… ል አስመራ


 …መች ነው የምንገናኝ ከምወዳት እህቴ

አልቆልኝ የማየው የአምሳ ዓመት ናፍቆቴ፡፡        

                                               [ክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል 1937 ዓ.ም]
                                                          በፍቅር ለይኩን፡፡

                                                                                
       ለዚህ መጣጥፍ መነሻ የሆነኝ ከዛሬ ሰባ ዓመት ገደማ በፊት በ1937 ዓ.ም ክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ‹‹የሐማሴን ድምፅ›› በኋላም ‹‹የኤርትራ ድምፅ›› በተባለው ጋዜጣ ላይ ያወጧት ግጥም ናት፡፡ ይህች ጋዜጣ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ አንድነት የሚታገሉ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ድምፃቸውን የሚያሰሙባት መድረክ ነበረች፡፡ በአጋጣሚ ለታሪክ ምርምርና ጥናት ሥራዬ በእጄ የገባችው ይህች ጋዜጣ ስለ ትናትናዎቹ ሁለቱ ሀገራት ወደኋሊት በታሪክ ሰረገላ ተጉዤ በጥልቅ እንዳስብ አስገደደኝ፡፡ ይህን በኅሊናዬ እያወጣሁ እያወረድኩ ሳለሁም በቴዲ አፍሮ የተዜሙት ሁለቱ ዜማዎች ‹‹ዳህላክና ፊዮሪና›› በአእምሮዬ መመላለስ ያዙ፤ እናም በዚሁ መንፈስ የክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ግጥም፣ የቴዲ አፍሮ ፊዮሪና ዜማና የትናንት ታሪካችን እውነት በውስጤ ያጫረው ስሜት ይህን አጭር መጣጥፍ ሊወልድ ቻለ፡፡ በቅድሚያ ግን በከፊል በዚህ ጹሑፍ ውስጥ ያካተትሁትን የዶ/ር ከበደ ሚካኤልን ግጥም እነሆ ልበል፡-


እንደነ ኡጋዴን ደግሞ እንደነ ባሌ
ሐማሴን ደሜ ነች ሥጋዬን አካሌ
ይህን ጉልህ ነገር ማነው የሚል አሌ፡፡
የእሷና የእኔ ቤት ምሰሶው አንድ ነው
አትተዋወቁም የሚለው ሰው ማነው፡፡
ዘላለም ምን ጊዜም ከዱሮ ከጥንት
በሁለተናችን የለም ልዩነት፡፡
አንድ አካል መሆኑን የእኔም የእስዋም ገላ
ዶጋሊ ላይ መልካም መስክሯል አሉላ፡፡
መች ነው የምንገናኝ ከምወዳት እህቴ
አልቆልኝ የማየው የአምሳ ዓመት ናፍቆቴ፡፡