የፍቅር ኃያልነት፣ የይቅርታ ታላቅነት፣
የነጻነት ክብር... የተገለጸበት
ፀሐፊ፡ በፍቅር ለይኩን፡፡
[fikirbefikir@gmail.com/befikir12@yahoo.com]
[fikirbefikir@gmail.com/befikir12@yahoo.com]
‹‹…Winn my love as
it drifted slowly away with you, I felt all alone in the world and the books
that fill my cell, which have kept me company all these years, seemed mute and
unresponsive.›› -ማንዴላ
ለውድ ባለቤታቸው ለዊኒ ከጻፉት የፍቅር ደብዳቤ የተወሰደ፡፡
ውድ ፍቅሬ ዊኒ… የቀዝቃዛውን የአትላንቲክ ውቅያኖስን ተጎራብቶ በሮቢን
ደሴት በተገነባውና እድሜዎቻቸው እንደ ባቢሎን ግንብ በረዘሙ ቅጥሮች እስር ቤት ተጥዬ፣ አውሬ በሚመስሉ አስፈሪ ውሾችና በአፓርታይድ ነጭ ፖሊሶች እንደ ነፍሰ ገዳይ በዓይነ ቁራኛ በምጠበቅበት
በዛች ጠባቧ እስር ቤት ውስጥ ከማንም ጋር እንዳልገናኝ ባለተፈቀደበትና ከአንቺ ከውድ ባለቤቴና ፍቅሬ ጋር እንኳን በየስድስት
ወሩ ለ30 ደቂቃ ብቻ እንድትጠይቂኝ በዘረኛው የአፓርታይድ መንግሥት ተፈርዶብን፤ ለአንቺ የምልከው የናፍቆት ደብዳቤዬ
እንኳን ሳይቀር በፖሊሶች እየተመረመረ፣ እየተቆራረጠና እየተደለዘ ለአንቺ ለፍቅሬ በሚደርስበት በአሰቃቂው በዛ የመከራና ጨለማ
ዘመን በመጣሽ ቁጥር ሳንጠጋገብ ተለያይተን ስትሄጂ የጫጉላነት ዘመናችን ውብ የፍቅር አጭር ጊዜያት ትዝ ይለኝና በሐዘን
እዋጣለሁ፡፡ የፍቅራችን ትዝታ በአእምሮዬ እየተደቀነ ልቤ በሐዘን ባሕር ይዋኛል፣ ነፍሴ በሐዘን ትቃትታለች፡፡
ውዴ ሆይ፡- በፈጣሪ
ድንቅ ጥበብ የተዋበው ውብ፣ ለስላሳው ገላሽና ሁሌም ምሽት ላይ በሲልክ በተሰራው ሮዝ የሌሊት ልብስሽ ሆነሽ በቤታችን እልፍኝ
ጉድ ጉድ ስትይ በዓይነ ኅሊናዬ እየታሽኝ ውብ ሰውነትሽን፣ ውብ ጠረንሽንና ጣፋጭ መዓዛሽን እናፈቀዋለሁ፡፡ የእኔ ጣፋጭ…
ከናፍቆትሽ ራብ የተነሳም ዓይኔን እንባ ይሞላዋል፡፡ ዊኒ ፍቅሬ:- ከሮቢን ደሴየት የእስር ቤት የአፍታ ያህል ቆይታሽ በኋላ
ወደመጣሽበት የምትወስድሽን መርከብ ሞተር ድምጽ ባሻገር ሲሰማኝ ነፍሴ ትሸበራለች፣ ልቤ የአትላንቲክ ውቅያኖሱን ተሻግሮ ውቧን
የደቡብ አፍሪካ እናት ከተማና የታሪክ እምብርት ኬፕታውንንና ለእናት ምድሬ ግርማ ሞገስ የሆነውን የቴብል ተራራን በሐሳብ
ሰንጠቆ ከአንቺው ጋር ይጓዛል፡፡ የእኔ ጣፋጭ ከሐሳቤ ባንኜ ከአንቺ ተለይቼ ወደ ጠባቧ የእስር ቤት ክፍል ስገባ በሰፊው ዓለም
ውስጥ ብቻዬን ያለሁ፣ ብቻዬን የተረሳሁ፣ ብቻዬን የተጣልኩ ሆኖ ይሰማኛል፣ ለዓመታት ብቸኝነቴን ያስረሱኝና የሚያነጋግሩኝ
መጽሐፍቶቼ በዝምታ የተዋጡ ድምፅ የለሽ መስለው ያፈጡብኛል…››
(ኔልሰን ማንዴላ ለባለቤታቸው ለዊኒ ማንዴላ ከጻፉት የፍቅር
ደብዳቤ የተወሰደ -እ.ኤ.አ 1970ዓ.ም)፡፡
በአንድ ወቅት የለንደኑ ዘጋርዲያን
ጋዜጣ ይህን ኔልሰን ማንዴላ ለቀድሞ ባለቤታቸውና ለትግል አጋራቸው ለዊኒ የጻፉትን የፍቅር ደብዳቤዎች፡- ‹‹ማንዴላ ለዓለም ሕዝብ የፍቅርን ብርታትና ኃይል የገለጹበትና ለመጽሐፋቸው የፍቅርን፣ የሕይወትንና
የውበትን እስትንፋስ እፍ ያሉ ደብዳቤዎች ናቸው በእርግጥም አንዳንዶቹ ለዊኒ የተላኩት ደብዳቤዎች some of his letters from
the prison to the then-wife Winnie are really heartbreaking…በማለት ነበር በሐዘን ስሜት የገለጸው ዘጋርዲያን፡፡
ወይ ፍቅር… ምን ቋንቋ፣ ምን ቅኔ፣ ምን ጥበብ… ፍቅርን በምልዓት ሊገልጸው ይችል ይሆን…? በ27 ዓመታት የማንዴላ የግዞት ሕይወታቸውና የነጻነት ትግላቸው ጉዞ ውስጥ፡- በእርግጥም ፍቅር ብርታታቸው፣
ፍቅር ጉልበታቸው፣ ፍቅር ጽናታቸው፣ ፍቅር ተስፋቸው፣ ፍቅር ራእያቸው ነበር፣ ነውም! ስል ለመደምደም ወደድሁ፡፡ ይህን እውነት
የሚያስተባብል፣ የዚህን የፍቅር ጽናት፣ ኃይልና ብርታት ሊቋቋም የሚችል የትኛው በደል፣ የትኛውስ የክፋት ኃይል ነው. . .?
ፍቅር በነጻነት፣
ነጻነት በፍቅር መስዋእትነት ውል በተገመዱባት በዛ የአፍሪካ ምድር ባፈራችው እንቁ ማንዴላ/ማዲባ ልብ ውስጥ ዛሬም የፍቅር፣ የነፃነት፣
የፍትህና የይቅርታ መልእክት ባሕሮችን፣ ውቅያኖሶችን፣ ተራሮችን እና አድማሳትን ሁሉ ዘልቆ ይሰማል፡፡ የዘረኝነት ቅጥሩን ጥሶ፣
ድንበሩን አፈራርሶ ፍ…ቅ…ር… ብርቱ፣ ፍ…ቅ…ር… ኃያል፣ ፍ…ቅ…ር… ዘላለማዊ…!!!
አነሳሴ የማንዴላን ‹‹ከራስ ጋር ወግ/ጭውውት››
መጽሐፍን ለማሐየስ አይደለም ግና በሰሞኑ በዚህ መጽሐፍ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ የስነ ጹሑፍ ባለሙያዎችና ሐያስያን
ያበረከቷቸውን ሥራዎቻቸውን ሳነብ ነበር፡፡ እናም ማንዴላ በሕይወታቸው ደጋግሞ ለደረሰባቸው ቃላት ሊገልጸው ከሚችለው በላይ
ለሆነው የሰው ልጆች ክፋት፣ አመጻና በደል ያሳዩት የፍቅርና የይቅርታ መንፈስ እንዲሁም በመጨረሻ በጠላቶቻቸው ላይ የተጎናጸፉት
የመንፈስ ድልንና ልእልናን በተመስጦ እያሰላሰልኩ ለብቻዬ በሐሳብ ለደቂቃዎች ተመሰጥኩ፤ እናም በእኚህ ሰው ታላቅ ስብእና
የተሰማኝን ልዩ ስሜት ለሌሎች ጭምር ለማጋራትና ሁሌም ብናወራው፣ ብንጽፍለት፣ ቅኔ ብንቀኝለት፣ ብንዘምርለትና ብናሰላስለው
ፈጽሞ ስለማይሰለቸው ፍቅርና የፍቅር ዋንኛ ባሕርይ ስለሆነው ይቅርታ በማንዴላ በራሳቸው ብዕር በተተረከው የሕይወት ታሪክ
መጻሕፋቸውን ዋቢ በማድረግ ያለፉበትን እልህ አስጨራሽ የትግል ሕይወታቸውንና በእዚህም ረጅም የትግል ጉዞአቸው ያለፉበትንና
በሌሎች የደረሰባቸውን ግፍና መከራ በይቅርታ መንፈስ ያለፉበትን ድንቅና ለዓለም ሁሉ መነጋገሪያ የሆነውን የእርቅና የሰላም ተምሳሌት
ተደርገው በተወሰዱበት ታላቅ ሰብእናቸው ዙሪያ ጥቂቱ ነገሮች ለማለት ወደድሁ፡፡
‹‹Conversation with Myself›› በሚል እ.ኤ.አ በ2011ዓ.ም ለህትመት የበቃው የኔልሰን
ማንዴላ የሕይወት ታሪክ እስከ ዛሬ ድረስ ራሳቸው ማንዴላም ሆኑ ሌሎች ጸሐፍት ከጻፏቸው በእርሳቸው ሕይወት ታሪክ ዙሪያ ከተጻፉ
መጽሐፍቶች ልዩ የሚያደርገው የማንዴላን በጣም የግልና ምስጢራዊ የተባሉ የግል ሕይወታቸውን፣ የትዳራቸውንና የጓዳቸው ምስጢር፣
በእስር ቤት ሆነው ከቤተሰባቸው፣ ከትግል አጋራቸውና ውድ ባለቤታቸው ከዊኒ ማንዴላ ጋር የተጻጻፏቸውን የፍቅር ደብዳቤዎች፣
ምስጢራዊና ድብቅ የሆኑ (very confidential letters) ከፓርቲያቸው ከANC ጋር የተለዋወጧቸውን ፖለቲካዊ ደብዳቤዎች፤ ሰው በመሆን ውስጥ ያለፉበትን የመውደቅና
የመነሳት ውጣ ውረድና እልህ አስጨራሽ የሆነውን የሕይወትን ብርቱ ትግልና ሠልፍ በግልጽ ለዓለም ሕዝብ ይፋ ያወጡበት በመሆኑ
ልዩ ትኩረትና አድናቆት የተቸረው መጽሐፍ ለመሆን በቅቷል፡፡
ለዚህ መጽሐፍ መቅድም የጻፉት የልዕለ ኃያላኗ የሀገረ አሜሪካ የመጀመሪያ ጥቁር ፕሬዝዳንት የሆኑት
ባራክ ኦባማ ስለዚህ ድንቅ መጽሐፍና ማንዴላ ሲናገሩ፡-
‹‹… የእኚህ
ታላቅ አፍሪካዊ ፖለቲከኛና የነጻነት ታጋይ የሕይወት ታሪክን ማንበብ ለእኔ እጅግ መሳጭና ልዩ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ በማንዴላ ልብ
ውስጥ ሞልቶ የፈሰሰውን ዓይነት ታላቅ ሰብአዊነት፣ ርኅራኄ፣ ፍቅርና ይቅርታ ለመስጠት የሚችል ለጋስ የሆነ ልብ ይኖረኛል ብዬ ለማለት
አልደፍርም፣ ከእናንተስ ማን ይሆን እንዲህ ዓይነቱ ልብ የሚኖረው… ይህ በምንም መከራ ያልተበገረ የማንዴላ የመንፈስ ጽናትና ብርታት
ለእኚህ ታላቅ ሰው የጥንካሬያቸው ምንጭ ሆኖ ዘልቋል ዛሬም ጭምር በእርግጥም ትሑት ሃይማኖተኛ ሰው ናቸው ማንዴላ...!!!››
ኔልሰን ማንዴላ ይህን መጽሐፋቸውን በዓለም ዋንጫ መክፈቻ ዕለት በድንገተኛ የመኪና አደጋ በሞት ለተለያቸው
የልጅ ልጃቸው መታሰቢያ ያደረጉት መሆናቸውን ገልጸውታል፡፡ አፍሪካውያን በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለምን ዋንጫ ለማዘጋጀት በደቡብ
አፍሪካ አማካኝነት ዕድል በማግኘቷ መላው አፍሪካዊ እንባ በተራጩበት ብዙዎችም አፍሪካውያን ለዚህ ወግና ማእረግ ገና አልደረሱም
የሚል ሟርታቸውን በሚያሟርቱበት ወቅት አፍሪካ ዳግም በተሞሸረችብትና በሚልዮን የሚቆጠሩ የዓለማችን ሕዝቦች በቴሌቪዥን መስኮት ዓይኖቹን
ወደ ደቡብ አፍሪካ ባደረጉበት በዛ ወርኃ ክረምት በዚህ ታሪካዊ የዓለም ዋንጫ መክፈቻ ቀን ይገኛሉ ተብለው የታሰቡትና በታላቅ ጉጉት
የተጠበቁት ኔልሰን ማንዴላ በልጅ ልጃቸው ሞት ሐዘን ምክንያት ለመገኘት አለመቻላቸው አሳዛኝና አስደንጋጭ ክስተት ሆኖ ነበር ያለፈው፡፡
በዛ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ጥቁርና ነጭ ሕዝብ በአንድነት በታደሙባት በስዌቶው የሶከር ሲቲ ስታዲዮም
ለመገኘትና ከዓመታት በፊት በዛች የጥቁሮች ከተማ ስዌቶ ገና ምንም የማያውቁ ጨቅላ ሕጻናት እኩል የሆነ የትምህርት እድል ይከበርልን
ብለው ሰልፍ በመውጣታቸው በእነዚህ ንጹኃን ላይ የጥይት ውርጅብኝ ላዘነቡባቸውና በአፓርታይድ ነጭ ፖሊሶች ጥይት አረር በጠራራ ጸሐይ
ግንባራቸውን እየተመቱ ደማቸው የውሻ ደም ሆኖ በፈሰሰባት በስዌቶ[i] ማንዴላ በአካል ተገኝተው የእነዛ ንጹኃን ሕጻናትና የምስኪን እናቶቻቸው ደምና እንባ የታበሰበትንና
ያ ዘግናኝ የደቡብ አፍሪካውያን የጨለማ ዘመን ታሪክ የተዘጋበትን የታሪክ ምእራፍ ዳግም ለዓለም ለማብሰር ማንዴላ በዛች ታሪካዊ
ቀን መገኘት አለመቻላቸው ትልቅ ቁጭትንና ሐዘንን ፈጥሮ ነበር በወቅቱ፡፡
ለ27 ዓመታት በተጋዙባት፣ በገዛ ምድራቸው ሰብአዊ መብታቸው እና የመኖር መብታቸው በነጮች ስልጣን በሚወሰንበት በደቡብ አፍሪካ ማንዴላ በዚሁ ‹‹Conversation with Myself›› መጽሐፋቸው በጥልቅ ሐዘን እና ትዝታ ውስጥ ሆነው እንደገለጹት ዘጠኝ ወር በማሕጸናቸው ተሸክመው፣ ወልደው፣ አሳድገውና አስተምረው፣ ለዛሬ ሰብእናቸው ታላቅ መሠረት የጣሉላቸውን፣ ባለውለታቸውንና የዘጠኝ ወር ቤታቸውን ውድ እናታቸውን ለመቀብርና በእንባ ለመሰናበትና ጥልቅ ሐዘናቸውን ለመግለጽ በመቃብራቸው ላይ እንኳን እንዳይገኙ በአፓርታይድ መንግሥት ፈቃድን ተነፍገው ነበር፡፡
ለመሆኑ ይህን
ጥልቅ ሐዘን ሊቀበልና ሊሸከም የሚችል የማንኛችን ልብ ነው…!? ቤተሰባዊ ቁርኝትና አንድነት ልዩ ትርጉም በሚሰጥባትና ‹እናት›
በአፍሪካ ምድር የሕይወት ምንጭና የፍቅር አውራና ተምሳሌት ተደርጋ በምትሳልበት አህጉርና ማኅበረሰብ የዘጠኝ ወር ልዩና ውብ ዓለማችንን፣
የፍቅርና የሕይወት ሲሳያችንን የእናታችንን ሞት በመቃብሯ ተገኝተን በእንባችን ለመሰናበት ዕድል ቢነፈገን በውስጣችን የሚፈጠረውን
ቅጥ የለሽ ሐዘን ምን ቋንቋ ሊገልጸው፣ የትኛውስ ጠንካራ ልብ ይህን መራር ሐዘን ሊሸከመውና የትኛውስ ብርቱ ኅሊና ይህን ስብራት
ሊያስታምመው ይችል ይሆን…?
ይህን ነፍስን በሐዘን ሰይፍ የሚመትር ሰው የመሆንን ክብርንና ልእልናን በትልቅ ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ
ከባድ ሐዘንና ፈተና ውስጥ ቅስማቸው የተሰበረው ማንዴላ ዳግመኛ በእዛው በእስር ቤት እያሉ መርዶው የመጣላቸውን የአብራካቸውን ክፋይ
የበኩር ልጃቸውንም ወደ መቃብር ለመሸኘትና ሐዘናቸውን ከቤተሰባቸውና ከወዳጅ ዘመድ ጋር መካፈል እንዳይችሉ የሰዓታት ዕድሜ እንኳን
ተንፍጓቸውና በጠባቂዎቻቸው ጥብቅ የሆነ እገዳ ተጥሎባቸው በጠባቧ ወህኒ ቤታቸው በብርቱና ልብን በሐዘን ጦር በሚወጋ የብቸኝነት
ቆፈን ብርድ እየተንዘፈዘፉና ልባቸው በሐዘን ሠይፍ እየደማ፣ እየቆሰለና እያመረቀዘ እንዲቆዩ ፍጹም ኢሰብአዊነት በጎደለው ሁናቴ
ነበር በዘረኛው የአፓርታይድ መንግስት ይህን ዘግናኝ ውሳኔ ያስተላለፈባቸው በኔልሰን ማንዴላ ላይ፡፡ ያን ጊዜ ሲያስታውሱት ማንዴላ
‹‹… ያ ጊዜ በእውነትም ከባድና
እጅግ መራር ነበር…›› በማለት ገልጸውታል በዚሁ መጽሐፋቸው ውስጥ፡፡
ይህን ጭካኔ፣ ይህን ዘግናኝ ኢ-ሰብአዊነት፣ ይህን ርኅራኄ የጎደለውን፣ ፍትሕ የራቀውን የአፓርታይድ
ዘረኛ ሥርዓት የትኛው ቋንቋ ሊገልጸው ብርታትና ኃይል ይኖረዋል፡፡ በዚህ ሁሉ የመከራ ውርጅብኝ መንፈሳቸውን ያላሸነፈው ማንዴላ በተፈቱ ማግስት ምሕርትንና ይቅርታን በማወጅ፣
ዓለሙ ሁሉና ጠላቶቻቸው ጭምር ሊያምኑት ያልቻሉትንና ሊሸከሙት አቅማቸውን የተፈታተነውን፣ በእንባና በእፍረት በርከክ ያሉለትን የፍቅርን
የይቅርታን ልዝብ ቀንበር ከፍ በማድረግ እነሆ አሉ እኚያ ታላቅ የጥቁር ምድር እንቁ ማንዴላ/ማዲባ፤ ዓለም በእንባ ተራጨ፣ ደቡብ
አፍሪካውያን እንባና ሲቃ ብቻ ቋንቋቸው እስኪመስል በታላቅ ዝምታና በአግራሞት ተዋጡ፣ የአፍሪካውያን ቋንቋ፣ የአፍሪካውያን ምላሽ…
እንባና ሲቃ ብቻ ሆነ… ዓለም ይህን ፍቅር፣ ይህን ይቅርታ ለመግለጽ ቋንቋ ጠፋው… ቃላትም ቸገረው… ፍቅር የተግባር ቋንቋ ሆኖ
በአካል ገዝፎ ደምቆና ከፍ ብሎ በአፍሪካ ምድር ለሁሉ ታየ…፡፡
ይህን ታላቅ የሆነ የማንዴላን
ስብእና፣ የይቅርታ ልብ፣ የመንፈስ ድልና ልእልና ክብር በእጅጉ የተደመሙበት ባራክ ኦባማ፡- ‹‹…Well, I'm pretty sure that I'm not capable of that generosity
of human spirit and I doubt if you are either. The puzzlement still remains as
to the source of this strength. He is religious, yes, but not in the same
Praise the Lord and Pass the Legislation sense of most U.S. Senators…›› እንዲህ ዓይነቱ እጅግ ሰብአዊነት የተሞላው ሩኅሩኅ መንፈስ ይኖረኝ ይሆን ብዬ እጠራጠራለሁ
ከእናንተስ ይህን ጽኑ መንፈስ የታደለ ይኖር ይሆን… በማለት በኔልሰን ማንዴላ Conversation
with Myself መጽሐፍ መቅደም ላይ ባሰፈሩት አስተያየታቸው በመገረም የጠየቁት የአሜሪካው ርእሰ ብሔር፡፡
ያን እንደ መርግ የከበደ የራሳቸውንና የሕዝባቸውን ሰቆቃና መከራ በታላቅ
ጽናትና ትእግስት የተቀበሉ ማንዴላ እናታቸውንና የበኩር ልጃቸውን እንኳን ለመቅበርና በእንባቸው ለመሰናበት የደቂቃ እድሜን
የተነፈጉት ማንዴላ የመከራቸውን ጥልቀትና ክብደት ሊወዳደር በማይችል ፍቅር ሁሉን በይቅርታ የዘጉት ማንዴላ በትክክልም መጽሐፍ
ቅዱስ እንደሚያስተምረን እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ የዓለሙን ሁሉ በደልና ኃጢአት ይቅር እንዳለና እርስ በርሳችንም በዚህ
መንፈስ በፍጹም ይቅርታ መቀባበል እንዳለብን ጌታችን ኢየሱስ ያስተማርውን ታላቅና ዘላለማዊ እውነት በተግባር የገለጹ የፍቅርና የይቅርታ ተምሳሌት መሆናቸውን ለዓለም
ለማስመስከር የቻሉ መንፈሰ ጽኑ ታላቅ ሰው መሆናቸውን ብዙዎች ያለማንገራገር ይመሰክሩላቸዋል፡፡
በዚህ ሁሉ ሰቆቃና መከራ ውስጥ
ያለፉትን ይቅር ባዩንና የሰላም ተምሳሌት የሆኑትን ማንዴላን በአንድ ወቅት ከሞትዎ በኋላ ምናልባትም ዓለም፣ አፍሪካውያንና
ሕዝብዎ በአንድ ድምፅ ቅዱስ የሚል ማእረግ ሊሰጥዎ እንደሚችል በብዙዎች ዘንድ ጥርጣሬ አለ እርስዎ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ
ተብለው በጋዜጠኞች የተጠየቁት ማንዴላ በዚሁ ‹‹ከራስ ጋር ወግ›› በሚል መጽሐፋቸው ውስጥ እንደገለጹት፡- ‹‹…ይህ ለእኔ አይገባም… ግን
በእኔ እሳቤ ቅዱስ ማለት የማይሳሳት ሳይሆን ለመቀደስ ወይም ቅዱስ ለመሆን አብዝቶ የሚሞከርና የሚጥር ኃጢአተኛ ማለት ይመስለኛል አሉ…፡፡›› ትህትና ፍቅር በሚንጸባረቅበት
ፈገግታ በተሞላ ቅላጼ… "Even on the basis of an earthly definition of a saint as
a sinner who keeps on trying".
Conversation with Myself- ‹‹ከራስ ጋር ወግ/ጭውውት›› የተባለው የኔልሰን ማንዴላን ድንቅ መጽሐፍ በመመርኮዝ የእኚህን
ታላቅ አፍሪካዊ የሰላምና የእርቅ ሰው አስደናቂ ሰብእና በጨረፍታ ለመዳሰስ የሞከርኩበትን መጣጥፌን እንዲህ ዓይነቱን በይቅርታና
በፍቅር የመቀባበል ታላቅ እውነትንና ሕይወትን የሚሰብኩ የሃይማኖት አባቶች፣ ባለ ራእይና የእርቅ ልብ ያላቸው የፖለቲካ መሪዎች
እንዲበዙልንና ደግሞም እንዲህ ዓይነቱ ባለ ድል የእርቅና የመቀባበል መንፈስ በእናት ምድራችን ኢትዮጵያ፣ በመሪዎቻችን፣
በፓርቲዎቻችን፣ በፖለቲከኞቻችንና በሕዝባችን መካከል ይሰፍን ዘንድ በአንድነት ልባዊ ምኞታችንን ብንገልጽስ…! በማለት የዛሬውን
መጣጥፌን ላጠቃልል ወደድሁ!!
ሰላም! ሻሎም!
[i]በጹሑፉ ውስጥ የተካተተው ምስል እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ በደቡብ አፍሪካዊቱ የጥቁሮች መንደር በስዌቶ እኩል የሆነ የትምህርት
እድል ይሰጠን ብለው በወጡ ታዳጊ ሕፃናት ላይ ዘረኛው የአፓርታይድ መንግሥት የተኩስ እሩምታ በመክፈቱና በዚህ አመጽ በተቀላለቀለበት
ሰልፍ ከሞቱ ከአምስት መቶ በላይ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን መካከል የ12 ዓመቱ ታዳጊ ሄክተር ፒተረሰን ይገኝበታል፣ በምስሉ ላይ
የሚታየው ሄክተር በጥይት ተመትቶ ነፍሱ ካለፈች በኋላ አንድ በሰልፉ ላይ የነበረ ወጣት ምስኪኑን ሄክተር በእቅፉ ይዞት ይታያል፡፡
በአጠገቡ እየጮኸች የምትታየው ደግሞ የሄክተር እህት ናት፡፡ በዚህች የሕጻናት ነፍስ ደም እንደ ውሻ ደም በፈሰሰባት ሰዌቶ ነው
ታሪክ ተለውጦ ነጮችን ጥቁሮች በአንድነት የዓለም ዋንጫ መክፈቻን ለመመልከት የታደሙት፡፡
It's a great article. I hope I read "Conversation with Myself" one day. We solute you Nelson Mandela.
ReplyDeleteThank you for sharing Bsrat
des yilal konjo tsihuf new
ReplyDeleteTiru Aterarek Ebakeh atakumew . FIKREN YASTEMERALNA .
ReplyDeleteThanks u for sharing .Nelson Mandela is father of peace
ReplyDeletewow what a story!!!!
ReplyDeleteWow very nice person
ReplyDelete"Even on the basis of an earthly definition of a saint as a sinner who keeps on trying".
ReplyDelete