ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Thursday, December 22, 2022

ደብረ ዓባይ አቡነ ሳሙኤል ገዳም - ታኅሳስ 12

         አባታችን አቡነ ሳሙኤል ደብረ ዓባይንና ዋልድባን ያቀኑ ታላቅ ጻድቅ ሲሆኑ የተወለዱት ቦታም በትግራይ ክፍለ ሀገር በርዕሰ ገዳማት ወአድባራት አክሱም ጽዮን በ 1298 ዓ.ም ከአክሱም ባላባቶች እና ካህናት እንዲሁም የአክሱም ጽዮን ገበዝ ከሚሆን ከጌዴዎን ዘር ከእስጢፋኖስና ከዓመተ ማርያም ተወለዱ።

በተወለዱም በ7 ዓመታቸው ወደ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተው በአጭር ጊዜ ትምህርታቸውን አጠናቀው በ 1314 ዓ.ም መንነው ወደ ደብረ በንኮል ገዳም ገብተው በአቡነ መድኃኒነ እግዚእ እጅ መነኮሱ። በደብረ በንኮል 3 ዓመት በርድና 9 ዓመት በምንኩስና ጠቅላላው 12 ዓመት አገለገሉ። ከዚያ በኋላ ከዚያ ወጥተው ወደ በጌምድር በመሄድ በወይና ፣ በመንዳባ ፣ በዞዝ ፣ በአዘዞና በአብጠራ ወዘተ እየተዘዋወሩ በየዋሻው ሱባዔ እየገቡ በጾም በጸሎት በስግደት በአርምሞ በተለያየ ገድል 19 ዓመት ከተቀመጡ በኋላ ወደ ሽሬ አውራጃ ተመልሰው በየቦታው እየተዘዋወሩ የገበሬዎችን ዘር እየባረኩ ሕሙማንን እየፈወሱ ሙታንን እያስነሱ ትምህርተ ወንጌልን እየሰበኩ ብዙ ሕዝብን ካሳመኑ በኋላ በ1353 ዓ.ም ወደ ደብረ ዓባይ ገቡ። ገብተውም የቦታውን ጽሙናና የቦታውን ስፋት አይተው በጣም ተደስተው ሱባዔ ቢገቡ ብዙ ተአምራት ተደርጎላቸዋል። 
ከተአምራቶቹም ጥቂቶቹ ውዳሴ ማርያምን እና ቅዳሴ ማርያምን ደግመው ውሃውን ቢባርኩት ኅብስት ሆኖላቸው አርድእቶቻቸውን መግበዋል።

እስከ ዛሬ ድረስ ገዳሙ የሚገለገልበት "ማይ ምንጭ" የሚባለውን ውሃ ባርከው አፍልቀዋል። ቅዱስ ሚካኤል ወደ ሰማይ አሳርጎ የሰማይ መኖሪያቸውን አሳይቷቸዋል። እራሱ ጌታችንም ከንጽሕት እናቱና ከአእላፍ መላእክት ጋር ሰማያዊ የመድኃኔዓለም ታቦትን ይዞ መጥቶ ሰጥቷቸው ይህች ቦታ ቦታህና መካነ ርስትህ ናት ብሎ ቃል በቃል ተነጋግሯቸው ዐርጓል።
በተነጋገሩበት ቦታ የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተሰርቶበት እስከ ዛሬ ድረስ ይገኛል። ደብረ ዓባይ ሆነውም ወደ ዋልድባ ሲመለከቱ ዓምደ ብርሃን ተተክሎ ከምድር እስከ ሰማይ ደርሶ ታያቸው። ምን ይሆን እያሉ እያደነቁ ሲኖሩ ከዕለታት በአንድ ቀን ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ "ያየኸው ዓምደ ብርሃን በቦታው ልጆችህ ይኖራሉ። በዚህ ቦታ አበው ተሠውረውበታል። ገዳሙ ከአሁን በፊት በአረማውያን መሪዎች ሁለት ጊዜ ጠፍቷል ። አሁን ግን አንተ እንድታቀናው እግዚአብሔር ፈቅዶልሃል። ብርሃኑም የአንተ ፣ የስውራኑና የልጆችህ ጸሎት ነው።ስለዚህ ተነሳና ወደዚያ ሂድ " ብሎ አዘዛቸው። 
እዚያው ሄደው ባስለመዱት ገድል ሲኖሩ ዋልድባን እንደመሶብ አንስተው አስባርከዋታል።በዚሁ ቦታ በግብረ አምላክ ከሰማይ የመሥዋዕት ዕቃዎችና መሥዋዕት ወርዶላቸው የእመቤታችን ቅዳሴ ቀድሰው ሥውራኑንና ያልተሠወሩትን አቁርበዋቸዋል። እስከ ዕለተ ምጽአት የሚወለዱ ልጆቻቸውን አሳይተዋቸዋል።
 

እንዲህ እያሉ በዋልድባና በደብረ ዓባይ እየተዘዋወሩ ሲኖሩ ወደ ቅርብ በአንበሳ ወደ ሩቅ በክንፈ ብርሃንና በሠረገላ ብርሃን እየሆኑ ይሄዱ ነበር። በሕይወታቸው ሳሉ 700 ያህሉ የመንፈስ ልጆች ነበሯቸውና በዋልድባና በደብረ ዓባይ ማህበር ሠርተው እያስተዳደሩና እያስተማሩ ሲኖሩ በዚሁ ገዳም 45 ዓመት እንደተቀመጡ በ 100 ዕድሜያቸው ታኅሳስ 12 ቀን ማክሰኞ ዕለት በ1398 ዓ.ም በደብረ ዓባይ አረፉ።በተቀበሩበት በደብረ ዓባይ ገዳም በፀጋ የተሠጣቸው የመዝገብ ቅዳሴ ጉባዔ ሲወርድ ሲዋረድ እስከ ዛሬ አለ። በኢትዮጵያ ደረጃ የመዝገብ ቅዳሴ ማስመስከሪያ በዚሁ ገዳም ነው። የከብት ቆዳ በተአምራት እንደ በርሜልና እንደ ጋን ለክብረ በዓላቸው ለጠላ መጥመቂያ ያገለግላል።ያገለገለውን ሲያረጅ እየተቆረጠ ለእምነት ይሰጣል። ከተለያየ አደጋና በሽታም ያድናል።
ስለዚህ እንደ አክሱም ኅዳር ጽዮን ፣ እንደ ግሸን ማርያም እንደ ላሊበላ እንደ ዋልድባ መጋቢት 27 እና ጥር 11 በዚሁ በደብረ ዓባይ ገዳማቸው ብዙ ምእመናን በየዓመቱ ታኅሳስ 12 ቀን እየመጡ በዓሉን አክብረው ይውላሉ። ስለዚህ ከቅርብም ከሩቅም በንጹሕ ልቡና የተማፀነና የተሣለ ሁሉ የለመነውን ያገኛል። ይደረግለታልም።

አምላከ አቡነ ሳሙኤል ከቦታው ተገኝተን የጻድቁን በረከትና ረድኤት ለመሳተፍ ያብቃን ።

አሜን።

No comments:

Post a Comment