ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Saturday, April 14, 2018

የዋልድባዎቹ መነኮሳት

              በሽብርተኝነት ተከሰው ከሁለት ዓመት በላይ ታስረውን እጅግ የበዛ መከራና ስቃይ ሲቀበሉ የነበሩት ሁለት አበው መነኮሳት ማለትም አባ ገብረኢየሱስ ኪዳነማርያም እና አባ ገብረስላሴ ወልደሃይማኖት ዛሬ ከእስር ተፈተዋል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ በፊት የአባቶቻችንን መፈታት ደጋግሞ ሲጠይቅ ለነበረው የኢትየጵያ ህዝብ የአባቶቹ መፈታት እንደመልካም ዜና እንደሚያስበው አምናለሁ፡፡ ምክያቱም በወቅቱ አባቶች ይፈቱ በሚለው ድምፅ ውስጥ ሙስሊም ማህበረሰቡም ተሳታፊ የሆነባቸው ወቅቶች ስለነበሩ፡፡

ከፍተኛው ፍርድ ቤት በቀን 03 -08 -2010 ዓ.ም የአንድ መቶ አስራ አራት (114) እስረኞችን ክስ አቋርጠናል ብለው ሲገልጹ የአባቶቻችንን ስም ተካቶ የነበረ ሲሆን በዛሬውም ዕለት በቀን አርብ 05 -08 -2010 ዓ.ም ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ ፍርድ ቤቱ የእስረኛ መፍቻ ደብዳቤ ለቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በመፃፉ ያለወንጀላቸው ሁለት ዓመት በላይ የታሰሩት እስር አባቶቻችን ሊፈቱ ችለዋል፡፡ ለዚህም የብስራት እይታ ድረገፅ አዘጋጆች የተሠማንን ደስታ መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ ይችን ቀን በመናፈቅም ስንጠብቃት ነበር፡፡

አባቶቻችን ወደበዓታቸው ተመልሰው ለእናት ሀገራችን እንደሚፀልዩ እንደሚያለቅሱ እናምናለን፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሆን ዘንድ ምኞታችን ነው፡፡

ፅሑፌን ከማብቃቴ በፊት አባቶቻችን ከእስር ከተፈቱ በኋላ ለVOA ሬዲዮ የተናገሩትን ታሪክ ተሻጋሪ ንግግር ወደፅሑፍ ቀይሬ እንድታነቡት እጋብዛለሁ፡፡ መልካም የፋሲካ በዓል እንዲሁም መልካም የዳግማ ትንሳይ በዓል ይሁንላችሁ፡፡


አባ ገብረኢየሱስ ኪዳነማርያም
ስለእስር ወቅታቸው ፣ ስለ ገጠማቸው ችግር እና ፈተና አሁን ስለሚሠማቸው ስሜት እንዲሁም ተጠይቀው ሲመልሱ ፦

" እኛ የታሰርነው ታኅሳስ 28, 2009 ዓ.ም ነው፡፡ ግን ያው የፍርድ ቤት ፣ የማዕከላዊ ፣ የቂሊንጦ ችግር በእኔ አንደበት ብቻ ተገልፆ የሚዘልቅ አይደለም፡፡ ወደፊት ብዙ የምንነጋገርበት ይሆናል፡፡ ለአሁኑ ግን እግዚአብሔር የተመሠገነ ይሁን!በእውነት የአባቶቻችንን አምላክ ከብዙ ፈተናዎች አውጥቶ ከእናንተ ጋር እንድንነጋገር አድርጎናል፡፡ በእውነት እኔ እግዚአብሔርን የማመሠግነው. . . እኛ ደካሞች ብንሆንም ፤ በሕዝባችን ጥረት ፣ በሕዝባችን ትግል ፣ በአባቶቻችንም አምላክ ፤ በአበው አምላክ ፣ ቸርነትና ኃይል የመጣብንን ፈተናና ችግር አስወግዶ አሁን ከወገናችን ፣ ከሕዝባችን ጋር እንድንቀላቀል አድርጓል፡፡"

ጥያቄ፦ "
በጣም ፈታኝ ችግር ነበር እና ዛሬ ተገላገልን የምትሉት የችግር. . . በነበረው ጊዜ (በእስር ወቅት) ከባድ ጊዜ የትኛው ነበር?  "

" አሁን ተገላግለናል ማለት አይደለም! ችግሩ ይፈታል የምንለው ሀገራችን ፣ ቤተክርስቲያናችን ከታሰሩበት ማነቆ ፣ ከተተበተበው ማነቆ ፣ ሲበጠስ እና ሲፈቱ ነው ከእስር ተፈታን ብለን የምንናገረው፡፡ አሁን ግን ታግተን ነበር ፤ ከእግት ተለቀን ወደ ማህበረሰቡ ፣ ብዙሃኑ ወደ ታሠረበት እስር ቤት ተገናኘን . . . አብረን በአንድ ላይ ተቀላቀልን ማለት እንጂ ከእስር ተፈታን ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም በብዙ ነገር ታስረን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው፡፡

እኛ ውስጥ (እስር ቤት) አካላችን ነው የታሠረው ፡፡ መንፈሳችን አልታሰረም ነበር ፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ቢሆንም ብዙ ወገኖቻችን ታስረዋል፡፡ አሁንም ! አሁንም ከአምስት ዓመት በላይ ፣ አምስት ዓመት ከሶስት ወር ድረስ ያስቆጠሩ ወንድሞቻችን እንደታሠሩ ነው፡፡

እነ አሸናፊ አካሉ ያለ ከአምስት ዓመት ከሶስት ወር ያለምንም ፍርድ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኝ ወጣት ነው፡፡ እነዚህ እስካልተፈቱ ድረስ ከእስር ተፈታን ብለን ደፍረን ልንናገር አንችልም፡፡ እኛ እነሱ እስካልተፈቱ ድረስ እኛ ተፈታን ልንል አንችልም፡፡
እኛ የምንፈታው አሁንም በእስር ውስጥ ፣ በእገታ ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችን ሲፈቱ እና በሀገሪቱ ሠላምና አንድነት ሲረጋገጥ ፤ የመናገር መብት ፣ የመፃፍ መብት ፣ በሀገሪቱ  መልካም አስተዳደር ሲሰፍን . . . ያኔ ነው ከእስር ተፈታን ብለን የምንናገረው ፡፡

ሁለተኛ የእኛን መታሠር ፣ የእኛን መደብደብ ፣ የእኛን መንገላታት ፤ በማዕከላዊም ሆነ በቂሊንጦ የደረሠብንን ግፍ በመስማትና በሬዲዮና በተለያዩ ማህበራዊ ድረገፆች ፣ ሚዲያዎች ሲተላለፍ በመስማት ፤ ተሰባስበው ከቦታው ድረስ መጥተው በመጠየቅ ሙስሊም እና  ክርስቲያኑ ሌላም የሌላ ሃይማኖቶች በአጠቃላይ ስለእኛ የተጨነቁ ፣ ያሰቡ ወንድሞቻችን ፣ እህቶቻችን ፣ ወገኖቻችን በሙሉ ፤ ኢትዮጵያዊያን በዓለም ሁሉ የሚገኙ ፣ ሕዝባችንን እጅግ ከፍተኛ አድርገን እናመሠግናለን!! በገዳሙ ስም በዋልድባ ገዳም ስም እጅግ አድርገን እናመሠግናችኋለን፡፡ ምክንያቱም እኛ ከእስር የወጣነው በሕዝባችን ጥረትና ፣ በሕዝባችን አይዟችሁ ባይነት ፣ ሞራል ሰጪነት ፣ ድጋፍ ሰጪነት . . . እኛ ዛሬ ከታገድንበት ቦታ ወጥተን ወገናችንን እንድንቀላቀል አድርገውናል ፡፡ "

የአባቶቻችንን በረከት ይደርብን!!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!

No comments:

Post a Comment