ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Wednesday, July 11, 2018

ማነው ገንጣዩ?

          የዚህ ፅሑፍ መነሻ አንድ የማከብረው ወዳጄ 'ትግራይ' ብትገነጠል ምንም አናጣም... የትግራይ ሠው ማለት እንደዚህ ነው... ትግሬ ማለት እንደዚህ ነው... እያለ የወረደ እና የሚያበሳጭ ፍሬአልባ ፅሑፍ ፅፎ ማየቴ ነው። የገረመኝ 'ተደምሬያለሁ' የሚል ቲሸርት ለብሶ ፈገግ ኮራ ብሎ የተነሳውን ፎቶ ጨምሮበታል። እርግጥ ነው በሒሳብ ስሌት 'መደመር' ገደብ የለውም። ከማንም ጋር ከምንም ጋር መደማመር ይቻላል። ውጤቱም እንደተደማሪው ዓይነት ፣ ይዘት ይወሰናል። እንግዲህ ከማን ጋር እንደተደመረ እሱ ይወቀው።
ሠሞነኛው ሙቀት መሠለኝ አሁን አሁን በተጠናከረ ሁኔታ ስለ ትግሬ እና ትግራይ መልካም ነገር እየተነገረ አይደለም። ምንም እንኳን ጥቂቶች በተቃውሞ ቢሟገቱም!

    "ስታጠፋ ምላስ እንጂ አቋም አያስፈልግም" እንደሚባለው አንዳንዶች ጥላቻን ለማስፋፋት ፈለገው ፣ አንዳንዶች በአለማወቅ ፣ በአስተሳሰብ ጥበት ፣ ሌሎች 'ትገንጠል አታስፈልግም' በማለታቸው የሚበላ ትርፍራፊ እንጀራ በማግኘት  ይኖራሉ። ሁሉም ግን አይረቡም። 
እንደዚህ የወረደ ፣ ታጥቦ የማይጸዳ ፣ የመነቸከ ስብዕና ተሸክመው የሚኖሩ እነሱንም በመደገፍም በማራገብም ከጎናቸው የሆኑ ሁሉ 'ትግራይ' ሳትሆን እራሳችሁ ከህዝቡ ከማህበረሰቡ ብትገነጠሉ ለኢትዮጵያ ትልቅ አስተዋጽዖ እና ዘላቂ ጥቅም ነው። ችግሩ ተገንጠሉም ብትባሉም ይህን የሚያስደርግ ወኔም ድፍረትም የሌላችሁ መሆኑ ነው። እንደመርዘኛ እባብ ተሸሽጎ የጥላቻ የመከፋፈል ቃላትን መወርወር ካልሆነ።

                 ባለፉት 27 ዓመታት መገነጣጠል መከፋፈል ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። ያለንን ደም መጦ ጨርሶ በአጥንታችን አስቀርቶ ተፈታትኖናል ፤ ጥንካሬያችንን ሰብሮ ህብረታችንን በትኖ ፍቅራችንን አጠልሽቶ ክብር አልባ ሀገር አልባ ወገን አልባ ዕምነት አልባ ሊያደርገን ሞክሯል።
ስለመገንጠል ስለመጠላላት ስለዘረኝነት የሚያስብ ላይ ይቅር መባባል መደራደር ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። ማንም እየተነሳ ስለሌላው ህዝብ እንዲያወራ መፈቀድም አለበት ብዬ አላምንም። ቀልድ ጨዋታ መፎጋገር የትም ዓለም አለ። አንዱ በአንዱ መተራረብ በአኗኗር መንገድ ውስጥ የሚታይን እውነታ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አንዱ በአንዱ ጥላቻን ቂምን መዝራት ግን አንገት ማስቆረጥ አለበት ብዬ አምናለሁ።

         እኔ የትግራይ ተወላጅ አይደለሁም ነገር ግን ስለ ትግራይ ሕዝብ መልካምነት እስከጥግ ልናገር ፣ እስከጥግ ልሟገት እችላለሁ። ኢትዮጵያን እንደቅርጫ አከፋፍለህ ለኢትዮጵያ የሚጠቅሟትን የሚያስፈልጓትን ክልሎች አስቀር ብባል ከማስቀራቸው ክልሎች አንዷ ነች። ይህ ማለት ሌሎቹ አያስፈልጉም ሳይሆን በባህል በታሪክ በዕምነት በሌሎችም ብዙ ምክንያቶች ትልቅ ቦታ ስላላት ነው።
ስለሌሎቹ ታውቃለህ ወይ ብትሉኝ መልሱ አዎ ነው። ኢትዮጵያን ከእግር እስከ እራሷ አውቃታለሁ ነው መልሴ!!! በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ዞሬያለሁ ፣ ከርሜያለሁ ፣ ኖሬያለሁ ሰንብቻለሁ። ባለጌውንም ሌባውንም ግብዙንም ቅኑንም ደጉንም ታሪክ ሳይኖረው እዚህ ግባ የማይባል ወሬ ይዞም ታሪኬን አክብሩልኝ ብሎ ዘራፍ የሚለውንም ለይቼ አውቃለሁ።

የፍቅር ከተማ ነን ፣ የባህል ማዕከል ነን ፣ ትንሿ ኢትዮጵያ ነን ፣ የሃይማኖት መቻቻል ማሳያ ነን... ሌላም ሌላም እያሉ እራሳቸውን በራሳቸው ሾመው እራሳቸውን እያወደሱ ስራቸው ምግባራቸው ግን የላሸቀ ምንም ከሚሉት ጋር የማይገናኙ ክልሎችን ቦታዎችን ህዝቦችን አውቃለሁ።

በኢትዮጵያዊነታችን ተመሣሣይነታችን ብዙ እንደሆነ ሁሉ ምንም ኢትዮጵያዊነት ምንም የማይታይባቸው ሆዳም ለሆዳቸው የሚያድሩ ሠውን የማያከብሩ ፣ እንግዳ ሲመጣ አሳቀውና አስጨንቀው ምን ዓይነት ህዝቦች ናቸው እነዚህ የሚያስብሉ ሠውን የማያከብሩ ፣ እንግዳ ሲመጣ አሳቀውና አስጨንቀው ምን ዓይነት ህዝቦች ናቸው እነዚህ የሚያስብሉ ሠውን እንደከበት እያረዱ የሚደሠቱ፣ሠው ሲሞት የሚስቁ ፣ አውሬ ከአውሬ የባሱትንም ዘርዝሬ ልናገር እችላለሁ። እድፍ ጉድፋችንን ሸፍነን ስለሌሎች ለምን እንደምናወራ አይገባኝም።

በተለይ በዚህ ወቅት ዝቅ ብሎ እግር የማያጥብ ሁሉ ስለኢትዮጵያዊነት ህብረት ለማውራት ሲዳዳው ስመለከት አፍራለሁ። እነእንትና አይጠቅሙም ፣ እነእንትና ልሙጡን ባንዲራ ለምን ያዙ? እነእንትና እኮ እንዲህ ናቸው... ብላብላ መጀመሪያ እራሳችንን እንፈትሽ!! ለኢትዮጵያዊነት የሚያበቃ ኢትዮጵያዊ የሚያደርግ ማንነት ስብዕና የተወለወለ ታሪክ አለን ወይይ እንበል። እኛ ለማንታመንለት ኢትዮጵያዊነት ሌሎችን ማጥላላት ዋጋ የለውም።
"ግም ለግም አብረ አዝግም" ለሀገር አይሰራም።

            የኢትዮጵያን ታሪክ እና መገለጫዎች የያዘውን እና ተጨፍልቆ የሚኖረውን የሌሎች መጠቀሚያ ከሆነው የትግራይ ነዋሪ ይልቅ ከአስቸጋሪነታቸው የተነሳ መግባባትን የማይመርጡ ብናጠፋም ቻሉን መቻቻል ግድ ነው ብለው የሚሰብኩ ሰብዓዊነት የሚባል ነገር ያልፈጠረባቸው ሠው ሠው የማይሸቱ የወረዱ ህዝቦች ነዋሪዎች ተወላጆች ቢገነጠሉ ምርጫዬ ነው። ይሄንን ሃሳቤን ሀገርን የሚዞሩ ሠዎች ያውቁታል ይረዱኛልም ብዬ አስባለሁ። እውነታን እየሸፈኑ ታሪክን እየደበቁ እስከመቼ እንደምንዘልቅ አልገባህ ብሎኛል።

ከተማ እየኖረ የበሰለ እየበላ ንጹህ ውሃ እየጠጣ ያማረውን እየለበሰ ነገር ግን ስለማያውቀው ህዝብ ፣ የህዝብ አኗኗር ፣ ስለማያውቀው ባህል ፣ ስለማያውቀው ታሪክ ፣ ስለማያውቀው ነገር... የሚያወራ ሠው እንዴት እንደሚሰማ እንዴት እንደሚደመጥ እንዴት ዝም እንደሚባል ግራ ይገባኛል። የአጨብጫቢውስ መብዛት? ያስደንቀኛል።
"ደሃ ተበድሎ ይቅር በሉኝ ይላል" አለ የሀገሬ ሠው።

እዚህ ላይ ለሆዳቸው ያደሩ አዲስ አበባ ላይ እና ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ የስርዓቱ ደጋፊዎች እና ፍርፍር ጠባቂ ለቃሚዎች ይኖራሉ። ቆሻሻ ሕይወት እየኖሩ በችግሮቻችን የሚስቁ አሽቃባጭ አቃጣሪዎች ሞልተዋል። ሲያበሳጩን ሲያስገድሉን ሲያስመቱን ሲያሳስሩን የኖሩ አሉ። ከእነሱም ጋር ተደምረው ህዝብን ሲያስለቅሱ የነበሩ ያሉ የሌላ ብሔር ተወላጆችም እንዳሉ ማለት ነው! ታዲያ ይሄን ለይተን ውቧን ኢትዮጵያ መፍጠር እንዴት ያቅተናል? ዘለዓለም መበላላት?

            የሚጻፉልን የተጣመሙ መጻሕፍት የሚነገሩን የውሸት ታሪኮች የምንመለከታቸው የፈጠራ ፊልሞች ገንዘብ አፍቃሪነታችን አጣመውን ሊሆን ይችላል። ቢሆንም ስለኢትዮጵያዊነት ስናወራ ምክንያታዊነት እንጂ ተደማጭነት ስላለን ፣ ዩኒቨርስቲ ምሩቅ ምዑር ስለሆን ፣ ታዋቂ ስለሆን ፣ መጻፍ ስለምንችን ፣ ወሬኛነት ስለሚያጠቃን መሆን የለበትም። ምንም ይጻፍ! አይነበብ አልልም ግን በኃላፊነት ስሜት በሚመለከተው አካል ማረጋገጥ ፣ ተገቢ ቦታ ሄዶ ማጥናት ፣ አባቶችን አዋቂዎችን መጠየቅ ፣ ሀገሬን ልወቅ ብሎ መነሳት ታሪካዊ ስህተት እንዳንሰራ ይረዳናል።

           የኢትዮጵያ ፤ የሀገሬ ታሪክ እንደተረት ተረት 'ከዕለታት አንድ ቀን'... ተብሮ ተጀምሮ 'አፌን በዳቦ አብሱ' ተብሎ የሚያቆም አፍ መፍቻ የመላምት መለማመጃ የፈጠራ ውጤት አይደለም። ስለኢትዮጵያ ለማወቅ ፣ ስለቆመችበት ምሰሶ ለመመስከር አርቆ ማሰብ ጠልቆ መመርመር ያስፈልጋል። ለሕጻን ልጅ የማይመጥን የማያሳምን አንደበት ይዘን ስለሀገር መዋቅር ፣ ስለህዝብ ቅንነት ስለግለሰቦች ስብዕና አኗኗር ለመተንተን መድፈር ንቀት ካልሆነ አዋቂነት አይመስለኝም። እንደመር ከሆነ አርፈን እንደመር!!

            ጊዜው የእርቅ የፍቅር የመተባበር ነው በሚባልበት ወቅት ይህን የሚገልጸውን ባንዲራ አንግበን እየታየን ስለመከፋፈል ስለጥላቻ ስለፀብ የምናወራ ከሆነ ባንዲራውን ሀገራቸውን ለሚወዱ አስረክበን ስለፍቅር ምንነት ፣ ስለባህል ምንነት ፣ ስለአብሮነት ፣ ስለታሪክ ፣ ስለእምነት... በአጭሩ "ስለኢትዮጵያዊነት" ቁጭ ብሎ መማር ሳያስፈልግ አይቀርም።

አመሠግናለሁ!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

No comments:

Post a Comment