ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Friday, January 6, 2017

የገና በዓል አከባበር በላሊበላ

     በዚህ በዓል በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ምዕመናን መንፈሳዊ በዓሉን ለማክበርና በረከት ለመሳተፍ የሚጓዙ ሲሆን ሌሎቹም አብያተ ክርስቲያናቱንና መንፈሳዊ የበዓል ሥርዐቱን ለመጎብኘት ነው። ይህም በዓል ሃይማኖታዊ፣ መንፈሳዊ፣ ትውፊታዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሀገራዊ ፋይዳ አለው።ይህንንም ለማስረገጥ በየዓመቱ ያለማቋረጥ ምዕመናን ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች መምጣታቸው ነው።
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በመላው  ዓለም የሚከበር ሲሆን በሁሉም የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት፣ ሌሊቱ ማሕሌት ተቁሞ ቅዳሴ እንዳበቃ፣ የበዓል ፍጻሜ ይሆናል፡፡  በላሊበላ ግን በተጨማሪ በዕለቱ ጧት ላይ "ቤዛ ኵሉ" የተሰኘው ክብረ በዓል ከአለት ከተፈለፈሉት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በአንዱ በቤተ ማርያም ካህናቱ ጋራና መሬት ላይ ሆነው ያከብሩታል፡፡  በተጨማሪ ዕለቱ እራሱ ቅዱስ ላልይበላ(ላሊበላ) ም የተወለደበት
በ ታህሣሥ 29 ቀን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልና የገናናው ንጉሥ የቅዱስ ላልይበላ የልደት በዓል በመሆኑም ጭምር በአንድነት በድምቀትና በደስታ ማራኪ በሆነ መንገድ ይከበራል፡፡

የላሊበላው "ቤዛ ኵሉ" አከባበር ትእምርታዊ ነው፡፡ ማሜ ጋራ /ቤዛ ኩሉ ዓለም ሥነ ሥርዓት የሚካሄድበት ቦታ/ ላይ ያሉት የመላእክት ምሳሌ፣ መሬት ላይ ያሉት ደግሞ የእረኞች ምሳሌ ሆነው ዝማሬውን በሆታና በዕልልታ ያጅቡታል፡፡ የክርስቶስ ኢየሱስን መወለድ መጀመሪያ ያወቁ እረኞች በመሆናቸው በአገር ቤት ትውፊቱ እየተነገራቸው የሚያድጉት እረኞች በተለየ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡
በዓሉ በቦታው አገልጋይ በሆኑ 670 ካህናትና በአካባቢው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በሚያገለግሉ ከ500 በላይ በሚሆኑ ካህናት ታጅቦ ማህሌቱ ይካሄዳል፤ በዚህ በዓል መላው ነዋሪ ‘ካህን’ የመስሎ ሚታይበት አከባበር ነው፤ የማህሌት ሥነ ሥርዐቱ 2፡30 (ማታ) የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መሪነትና ሌሎች ብጹአን አባቶች በሚገኙበት በየዓመቱ ይከበራል።

በዓሉ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ መከበር የጀመረው ከ900 ዓመት በፊት ነው። ከታህሳስ 23(በዓለ ጊዮርጊስ) ጀምሮ እስከ ዛሬ (ታህሳስ 28) ድረስ ሁሌም 2፡00 ሰዓት ሲሆን የሥርዐተ ማህሌት ደወል ይደወልና በአገልግሎት ይታደራል።

ይህ በዋዜማው የሚካሄደው የማህሌት ሥርዐት 1፡30 አካባቢ የሚጀመር ሲሆን ልዩ የሚያደርገው የራሱ ቀለምና ዜማ ያለውና ሙሉ ሌሊቱን በወረብ ዝማሬ እየቀረበ የሚታደር መሆኑ ነው።
ማህሌት ሥነ ሥርዓቱ ሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አባታዊ መሪነትና በአስተዳዳሪው አስተባባሪነት እንዲሁም በመሪጌታው በሚመሩ ከ7 ባልበለጡ አስተናጋጆች በሥርዓት ይካሄዳል።የማህሌቱን አካሄድ ስንመለከትም አንድ ጊዜ ከ 12 ያልበለጡ ጥንግ ድርብ የለበሱ' አንድ ጊዜ ደግሞ ከ 12 ያልበለጡ  ጥቁር ካባ የለበሱ  በድምሩ 24 ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ከቀኝና ከግራ ሆነው በተራ እያሸበሸቡ ያስኬዱታል፡፡
ማህሌቱም ማዕጠንት በያዙ 4 ካህናትና ከ8 ያላነሱ ዲያቆናት ወርቅ ካባ ለብሰው፣ የወርቅ አክሊል ደፍተው፣ የወርቅ መስቀል ይዘው መለከት እየነፉ ዙሪያውን በመዞር ማህሌቱን ያጅቡታል። የዚህም ምሳሌነቱ ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ መላእክት መለከት እንደሚነፉ ለመግለጥ ሲሆን ለማህሌቱ ትልቅ ድባብ ይፈጥራል። የማዕጠንት ሥርዐቱ ካህናቱ በሊቀ ካህናቱ፤ ዲያቆናቱ በሊቀ ዲያቆኑ ይመራሉ። 
  ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ በአስራ አንዱም ቤተመቅደስ የቅዳሴ ሥርዐት ይፈጸማል። በተለይም ያሉትን ቆራብያን በተቀላጠፈ መልኩ ለማስተናገድ በቤተ ማርያምና በቤተ መድኃኒዓለም በሁለት ልዑክ ቅዳሴው ይከናወናል።
ከ12፡00 ሰዓት ጀምሮ ጥንግ ድርብ፣ ካባ እንዲሁም ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናት ከአስራ አንዱ ቤተመቅደስ ከእያንዳንዳቸው ከአስራ ሁለት ያላነሱ ካህናት ይህንን ያሬዳዊ ዜማ ለማጀብ ወደ ማሜ ጋራ /ቤዛ ኩሉ ዓለም ሥነ ሥርዓት የሚካሄድበት ቦታ/ ይወጣሉ።
ልክ አንድ ሰዓት ሲሆን ከላይና ከታች የሚሰለፉ ካህናት ቦታቸውን ይይዙና እስከ 4 ሰዓት በሚፈጅ ክንውን እየተቀባበሉ ለሀገር፣ ለወገን፣ ለምድር ሰላም በረከት የሚጸለይበት ‘ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ’ (ዛሬ የዓለም ቤዛ ተወለደ)  የተባለው የቀለም ክንውን ይካሄዳል። እንግዲህ የበዓሉን አከባበር በቅዱስ ላልይበላ ልዩ የሚያደርገው አንዱ ይህ “ቤዛ ኩሉ ዓለም” የሚባለው የቀለም ዓይነት ነው።

1 comment:

  1. Enter your comment...ቃለ ህይወት ያሰማልን ።

    ReplyDelete