ከ10ኛው እስከ 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (920-1253 ዓ.ም ድረስ) በላስታ ቡግና ምድር የነገሡ የላስታ ቡግና ተወላጅ የሆኑ የኢትዮጵያ ቅዱሳን ነገሥታት የንግሥናቸው መጠሪያ ‹‹የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት›› ወይም ‹‹የላስታ መንግሥት›› በመባል ይታወቃል፡፡ የላስታ ነገሥታት የዘር ሀረጋቸው ከንጉሥ ሰሎሞን ዘር ሲያያዝ የመጣ ነው፡፡ ከላስታ (ከዛጉዌ) ነገሥታት መካከል ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ገብረ ማርያም፣ ቅዱስ ላሊበላና ቅዱስ ነአኵቶለአብ እነዚህ አራቱ ነገሥታት እንደ መልከጼዴቅ (ዘፍ 14፡18) ክህነትን ከንግሥና፣ ቅድስናን ከንጽሕና ጋር አንድ አድርገው በመያዝ እግዚአብሔርንም ሰውንም በቅድስና አገልግለው አልፈዋል፡፡ በንግሥናቸው ሀገራችንን በመልካም ሥራና በቅድስና ከማስተዳደራቸው በተጨማሪ ቅዱሳን ጻድቃን ሆነው እግዚአብሔርን በብዙ ድካም በመልካም ተጋድሎአቸው ያገለገሉና አገልግሎታቸውም ሆነ ቅድስናቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ስለተመሰከረላቸው ጌታችን የሰጣቸውን ቃልኪዳን መሠረት በማድረግ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን የቅድስና ማዕረግ ሰጥታ፣ በስማቸው ቤተክርስቲያን አንጻ፣ ጽላት ቀርፃ በዓላቸውን እያከበረች መታሰቢያቸው ተጠብቆ ለዘለዓለም እንዲኖር አድርጋለች፡፡
ገድለ ቅዱስ ላሊበላ፡-
እኛ ኢትዮጵያውያን የቅዱስ ላሊበላን እጅግ ድንቅ የሆኑ ሥራዎቹን ዓለም ከሚመለከትበት የተለየ መንፈሳዊ ዐይን ሊኖረን ይገባል፡፡ ስለዚህም የቅዱስ ላሊበላን የቅድስና ሕይወትና ከእግዚአብሔር ጋር ስለነበረው ግንኙነት ገድለ ቅዱስ ላሊበላን መነሻ በማድረግ ብዙ ነገሮችን ቀጥሎ እናያለን፡-
1.1 ቅዱስ ላሊበላ ከአባቱ ዣን ስዩምና ከእናቱ ኪርወርና ጌታችን በተወለደበት ዕለት ታኅሣሥ 29 ቀን 1101 ዓ.ም በላስታ ቡግና ወረዳ ልዩ ስሟ ሮሀ በተባለችው ሥፍራ ተወለደ፡፡ የልደቱን ነገር አስቀድሞ ቅዱስ ሚካኤል ለእናቱ ነግሯት ነበርና በተወለደ ጊዜ ብዙ ነጫጭ ንቦች መጥተው በሰውነቱ ላይ አርፈው እንደ ማር እየላሱት ስለታዩ እናቱ ‹‹ልጄን ንብ ዘበኛ ሆኖ ይጠብቅልኛል›› ስትል ስሙን ‹‹ላል ይበላል›› ብላዋለች፡፡ ላል በአገውኛ ንብ ማለት ነው፡፡ በጊዜ ብዛት በተለምዶ ነው ‹‹ላሊበላ›› ተብሎ መጠራት የተጀመረው፡፡ ንቦቹ ግን ሥጋዊ ንቦች ሳይሆኑ በንብ የተመሰሉ መላእክት ናቸው፡፡ ንጉሥ መሆኑን እያመለከቱ የሃይማኖትና የምግባር ማር ከእርሱ ይቀዳል ሲሉ በንብ ሠራዊት ተመስለው ሰውነቱን ላሱት፡፡ እንደ ዮሐንስና እንደ ኤርምያስም በእናቱ ማኅፀን ሳለ ነው መንፈስ ቅዱስ የሞላበት፡፡
ከዚህ ቀጥሎ በገድሉ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ አስደናቂ ነገሮችን እናያለን፡፡
1.2. ቅዱስ ላሊበላ ያነጻቸውን አብያተ ክርስቲያናት መመልከት ያለብን:-
በቅርስነታቸውና በቱሪስት መስህብነታቸው ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ የተገኙ ብቸኛ መንፈሳዊ ሀብቶቻችን መሆናቸውን ነው፡- ስለ ቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ከማንሳታችን በፊት በመጀመሪያ እውነተኛ የሕይወት ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን መመልከት የግድ ያስፈልጋል፡፡ ቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ቀድሞ በሕገ ልቡና ከዚያም በሕገ ኦሪት እግዚአብሔርን ስታመልክ ኖራለች፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ሐዋርያቱ እንኳን ለስብከት ከኢየሩሳሌም ሳይወጡ ነው በ34 ዓ.ም በራሷ ሐዋርያ በጃንደረባው ባኮስ አማካኝነት በክርስቶስ ማመንንና ጥምቀትን ወደ ሀገሯ ያመጣችው፡፡ የዚህ ደግሞ ምስክሩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ 1ኛ ነገ 10፡1-13፣ ሐዋ 8፡26-40፡፡ በዚህ መረጃ መሠረት ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ እስከ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ወደ ኢየሩሳሌም እየሔዱ ሃይማኖታዊ ጉዞ ያድርጉ ነበር፡፡ ከ7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ግን ከኢትዮጵያ ተነስቶ በሱዳን በግብፅ አድርጎ ወደ ኢየሩሳሌም በእግርና በእንስሳት ጉዞ ለማድረግ የመንገዱ አድካሚነትና በረሃማነት የሚባክነው ጊዜ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ተሻግሮም እስከ ግብፅና ሱዳን ድረስ የእስልምና ሃይማኖት ስለተጠናከረ ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ወደ ኢየሩሳሌም ለመጓዝ አስቸጋሪ ስለሆነባቸው ለሃይማኖታዊ አምልኮና ስግደት ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርጉት ጉዞ ተቋረጠ፡፡ ይህ ሁኔታም ሲያያዝ እስከ ቅዱስ ላሊበላዘመን ደርሷል፡፡ ቅዱስ ላሊበላም የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ወደ ኢየሩሳሌም ያደርጉት የነበረው ጉዞ በመቋረጡ በእጅጉ እያዘነ ተግቶ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር፡፡ የኢየሩሳሌምንም አምሳያ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናትን በሀገሩ ለመሥራት ይመኝ ነበር፡፡ ጥቂት ነገር ሲለምኑት አብዝቶ መስጠት ለእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነውና ላሊበላ ምድራዊ ኢየሩሳሌምን በሀገሩ ለመሥራት ሲያስብ ልዑል እግዚአብሔር በጥበቡእንደ ቅዱስ ጳውሎስ (2ኛ ቆሮ 12፡1-7) ወደ ሰማይ አሳርጎት ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን አሳይቶታል፡፡ ጌታችንም ‹‹ሕዝቦቼ የመከራና የስቃዬን ቦታ ለማየት ኢየሩሳሌም በመሄድ በመንገድ እየቀሩ ስለሆነ አሁን ግን አንተ በሀገረ ሮሐ ኢየሩሳሌምን ትሠራለህ›› በማለት የቤተ መቅደሶቹን አሠራር ሁሉ በዝርዝር ነግሮታል፡፡ በሰማያዊት ኢየሩሳሌምም ምሳሌ በሀገሩ ላይ ወጥ ከሆኑ የዓለት ድንጋዮች መላእክት እየተራዱት ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን እንዲያንጽ ነግሮታል፡፡
1.3. ጠላት ለክፉ ያሰበውን እግዚአብሔር ለበጎ ያደርገዋል፡-
ወደኋላ ተመልሰን የቅዱስ ላሊበላን የልጅነት ሕይወቱን እናንሳ፡- ቅዱስ ላሊበላ እናትና አባቱ ከሞቱበት በኋላ ወደ ጎጃም በመሄድ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን፣ ብሉይና ሐዲስን በደንብ ተምሮ ከጨረሰ በኋላ ወደ ደብረ ሮሐ ተመልሶ መጥቶ ነግሦ ከነበረው ከወንድሙ ከገብረ ማርያም ዘንድ ተቀመጠ፡፡ ‹‹ከገብረ ማርያም ቀጥሎ የሚነግሠው ላሊበላ ነው›› ተብሎ ትንቢት ስለተነገረ ሊያጠፋው ምክንያት ይፈልግበት ነበር፡፡ ለዐፄ ገብረ ማርያም በእናትም በአባትም እኅት የምትሆነው ለላሊበላ ግን በአባት ብቻ እኅት የሆነችው ዮዲት ላሊበላን ለመግደል በማሰብ ቀን ከሌሊት አጋጣሚን ትጠብቅ ነበር፡፡ ቅዱስ ላሊበላም ጌታችን መራራ ሐሞት መጠጣቱንም እያሰበ ሁልጊዜ ዓርብ ዓርብ ከጾምና ጸሎት በኋላ መራራ ኮሶ ይጠጣ ነበርና ይህን አጋጣሚ በመጠቀም አንድ ቀን እንደጠማው አውቃ በጠላ ውስጥ መርዝ ጨምራ ሰጠችው፤ ቅዱስ ላሊበላም መርዝ የተቀላቀለበትን ጠላ ጠጣው፡፡ እርሱ ከመጠጣቱ በፊት ያገለግለው የነበረው ዲያቆን ቀምሶት ወዲያው ሲሞት አየ፡፡ ዲያቆኑ ያስመለሰውን የጠጣው ውሻም ወዲያው ሞተ፡፡ ቅዱስ ላሊበላም ይህን ሲመለከት በሐዘንና በፍጹም ፍቅር ሆኖ ‹‹አገልጋዬ ለእኔ የተዘጋጀውን መርዝ ጠጥቶ እንደሞተ ሁሉ እኔም መሞት ይገባኛል›› በማለት ያን መርዝ ስለወዳጁ ፍቅር ሲል ጠጥቶ ለመሞት ቆረጠና ጠጣው፡፡ ጌታችን በወንጌሉ ስለራሱ ‹‹ስለ በጐቹ ቤዛ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ የሚሠጥ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም›› (ዮሐ 15፡13) ብሎ የተናገረውን ቃል ቅዱስ ላሊበላም ስለ ወዳጁ ሞት ሲል ራሱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ፡፡ ነገር ግን መርዙ እንኳን ሊጎዳው ይቅርና በሆዱ ውስጥ ከልጅነቱ ጀምሮ የነበረበትን የሆድ ሕመም ነቅሎ አወጣለት፡፡ በዚህም ጌታችን በወንጌሉ ‹‹የሚገድል መርዝም ብትጠጡ ምንም አትሆኑም›› (ማር 16፡18) ያለው ቃል ተፈጽሞለታል፡፡ መርዙ ለበጐ ሆኖለት ከሆዱም ውስጥ የነበረው ጥፍሮች ያሉት አውሬ መሰል ፍጡር ወጣለትና የሆድ ሕማሙ ፈጽሞ ተወው፡፡ ያን ጊዜም ቅዱስ ላሊበላ በወቅቱ ለሦስት ቀንም ያህል እንደሞተ ሆኖ የቆየ ቢመስልም ቅዱስ ገብርኤል ግን በመንፈስ ወደ ሰማይ ነጥቆ ወስዶ ሰባቱ ሰማያትን ያሳየው ሲሆን በጌታችን ፊትም አቅርቦት አስባርኮታል፡፡ ጌታችንም ቅብዓ መንግሥት ቀብቶት ትልቅ ቃልኪዳን ሰጥቶታል፡፡ ጻዲቁ ንጉሥ ቅዱስ ላሊበላ ቅድስናን ከንግሥና፣ ክህነትን ከንጽሕና፣ ጥበብ መንፈሳዊን ከጥበብ ሥጋዊ ጋር አንድ አድርጐ አስተባብሮ የያዘ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ፣ ቅዱሳን መላእክትም ይራዱት እንደነበርና ጌታችንም ትልቅ ቃልኪዳን እንደሰጠው ከቅዱስ ገድሉ ላይ እናገኛለን፡፡ ከጌታችን ዘንድ የተሰጠውንም ቃልኪዳን በሦስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡በዚህም መሠረት፡-
1ኛ. መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ላሊበላን እየመራው ከላስታ ወደ አክሱም ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም አድርሶ በዚያ የሚገኙትን ቅዱሳት መካናት ሁሉንም ካሳየው በኋላ ‹‹ወደ ሀገርህ ሮሐ ተመልሰህ በእነዚህ ምሳሌ ታንጻለህ›› ብሎታል፡፡ ወደ ሀገሩም ተመልሶ በአሽተን ማርያም ተራራ ላይ ሱባኤ ይዞ በጾም ጸሎት ተወስኖ ሳለ እግዚአብሔር የሚሠራቸውን መቅደሶች በግልጽ በራእይ አሳይቶታል፡፡
2ኛ. ከላይ እንዳየነው ለሞት ተብሎ የተሰጠው መርዝ ለሕይወት ሆኖለት በመሬት ላይ ወድቆ ሳለ በነፍስ መልአክ ነጥቆት እስከ ሰባተኛው ሰማይ ጽርሐ አርያም ድረስ ደርሶ በጌታ ፊት ቀርቦ ከጌታ ዘንድ ‹‹እኔ አከበርኩህ ቃሌ አይታበይም፣ ከአንድ ቋጥኝ እነዚያን በራእይ ያሳየሁህን አብያተ ክርስቲያናት ታንጻለህ›› የሚል ቃልኪዳን ተቀብሏል፡፡
3ኛ. ከኢየሩሳሌምም ተመልሶ የንግሥናውን ዙፋን ከቅዱስ ገብረ ማርያም ከተረከበ በኋላ በተሰጠው መንፈሳዊ ሀብትና ባየው ራእይ መሠረት አብያተ ክርስቲያናቱን አንጾ ከጨረሰ በኋላ በቀኝና በግራው ዓሥር ዓሥር ኪሎ የሚመዝን የዓለት ድንጋይ ተሸክሞ ለ7 ዓመት ሲጾም ሲጸልይ ጌታችን ተገልጦለት ‹‹…ያነጽካቸውን ቤተ መቅደሶች የተሳለመውን ኢየሩሳሌምን እንደተሳለመ አድርግለታለሁ›› የሚለውን የመጨረሻውን ቃልኪዳን ሰጥቶታል፡፡ (ይህን ቃልኪዳኑን መጨረሻ ላይ በዝርዝር እናየዋለን) እነዚህን ሦስት ዋና ዋና ቃልኪዳኖቹን በቅድሚያ ማንሳት የፈለኩበት ምክንያት ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ስለ ቅዱስ ላሊበላ ድንቅ ሥራዎች ከማሰባችንም ሆነ ከመናገችን በፊት በቅድሚያ ስለ ራሱ ስለ ቅዱስ ላሊበላ የቅድስና ሕይወቱና ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ግንኙነት ማወቁ የግድ አስፈላጊ መሆኑን ለመጠቆም ነው፡፡ አሁን አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሆን ተብሎ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቶቹ በቱሪስት መስህብነታቸው ብቻ እየታዩ የቅድስና ታሪካችንም እየተጨፈለቀና መንፈሳዊ እሴቶቻችንንም ለማጥፋትም ጥረት እየተደረገ ስለሆነ እውነተኛውን ነገር በደንብ ማወቅና በእጅጉ መጠንቀቅ ስላለብን ነው ይህን የማነሳው፡፡ ስለዚህ የቅዱስ ላለበላን የቅድስና ሕይወትና ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ግንኙነት ስንረዳ እነዚያ እጅግ ድንቅ የሆኑ ሥራዎቹ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና በሰማያውያን መላእክት እርዳታ የተሠሩ መሆናቸውን እንረዳለን፤ እግዚአብሔርም ለእኛ የሰጠንን ድንቅ የምሕረትና የቃልኪዳን ስጦታዎቻችን መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ ያንጊዜም ውቅር አብያተ ክርስቲያናቶቹን ዓለም ከሚመለከትበት የተለየ መንፈሳዊ ዐይን ይኖረናል፡፡ የቃልኪዳኑም ተጠቃሚዎች ለመሆን መንፈሳችን ይነሳሳል፡፡
በዚህ ደግሞ አሁን ያለውም ሆነ ወደፊት የሚመጣው ትውልድ ታሪኩን ከማጉደፍና ከጥፋት ይጠበቃል፣ አኩሪ ታሪኩንም ጠንቅቆ ለማወቅ መንፈሳዊ ቅናትም ስለሚያድርበት ራሱንም ከውጪው የባሕል ወረራና ጥቃት ይጠብቃል፡፡ በሀገራችን ያሉትን እጅግ ጥልቅ የሆኑ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ምሥጢሮችን ጠንቅቀው የተረዱት እነ ፕሮፌሰር ፓንክረስት ‹‹ክርስቶስ ከነጮች ይልቅ ለኢትዮጵያውያን ቅርበት አለው›› በማለት ምስክርነታቸውን እየሰጡ ባለበት ወቅት የዘመኑ የሀገራችን ወጣት ማንነቱን ጠንቅቆ ቢያውቀው ኖሮ የእነርሱን (የነጮቹን) ባሕል ለመከተል ባልዳዳው ከዘመናዊ ባርነትም ራሱን በጠበቀ ነበር፡፡
1.4.መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለቅዱስ ላሊበላ ስለ ቤተመቅደሶቹ አሠራር በዝርዝር እንዳስረዳው፡-
በተራ ቁጥር ሁለት ላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በቅዱስ ገድሉ ላይ ከገጽ 117-127 ድረስ በጣም በስፋትና በዝርዝር እንደተጠቀሰው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ላሊበላን እስከ ሰባተኛው ሰማይ ድረስ በመላእክት ተነጥቆ በፊቱ እንዲቆም ካደረገው በኋላ ቤተ መቅደሶቹን እንዴት እንደሚያንጽ ቃል በቃል ነግሮታል፡፡ እግዚአብሔር ለኖህ መርከቡን እንዴት እንደሚሠራ ከነልኬቱ ጭምር በዝርዝር እንደነገረው ሁሉ ለቅዱስ ላሊበላም ዝርዝር ሁኔታዎችን ጭምር እንዲህ በማለት ትእዛዝ ሰጥቶታል፡- ‹‹መልአኩም ክብሩ ከሰማያት ሁሉ ክብር ወደሚበልጥ ወደ ሰባተኛው ሰማይ አደረሰው፣ ቅዱስ ላሊበላም ይህንን አይቶ በግንባሩ ተደፋ፣ ከኪሩቤል ዘንድ ይነሳ የሚል ቃል ተሰማና አንዱ ሱራፌል መጥቶ አነሣው፡፡ ልቡንም አጽንቶ አቆመው…እግዚአብሔርም ተናገረው፡- ‹በምድር ላይ ቤተመቅደስ ትሠራልኝ ዘንድ የማሳይህን አስተውል፤ እዝነ ልቡናህንም ግለጥ፡፡ ከሰው ጋር ስለምኖር በሰማያት የምትኖር አባታችን እያሉ ከሚጠሩኝ በሃይማኖት ከተጐናፀፈኝ ስሜን ከሚያመሰግኑ ከመረጥኳቸው ከሕዝብ አንደበት በምመሰገንበት ገንዘብ እኔ ፈጥሬያቸዋለሁና፡፡ ከመጀመሪያይቱ ድንኳን ውስጥ በተሣለው ላይ ምስላቸው የተሠራ ከሚንቀሳቀሱ ከኪሩቤል አምሳል ለሙሴ እንደተናገርኩት አይደለም፡፡ ወዳጄ ሙሴ የመጀመሪያይቱን ድንኳን አርአያ በደብረ ሲና እንዳሳየሁት ድንኳንን እንደሠራ ሁሉ እንደሁ አንተም እንዳሳየሁህ ትሠራ ዘንድ ዕወቅ፣ አስተውል፣ ተጠንቀቅም፡፡ የማሳይህ ግን ለሙሴ እንዳሳየሁት አይደለም፤ መቅደሴን የምትሠራልኝም ሙሴ እንደሠራው አይደለም፤ ሙሴስ ከተፈተለ ልብስና ከእንጨት ድንኳን ሠራ፤ አንተ ግን ለምሰሶውም ሆነ ለመቀኑ ለመድረኩ እንጨትን የምትፈልግ አይደለህም፤ ለጠፈራቸው መማገሪያ ገመድ የምትሻ አይደለህም፣ እንጨትንም ለማገር፣ ለምሰሶዋቸውም ገበታ፣ ለዙሪያቸውም ለማያያዣ ጭቃን የምትፈልግ አይደለህም፡፡ የቤተመቅደሶችን ፈቃድ ሁሉ ከአንድ ቋጥኝ ድንጋይ ትፈጽማለህና፡፡ የማሳይህ እኚህ የቤተ መቅደሶች አኗኗር ከምድር ልብ ውስጥ እስከዛሬ አለ፡፡ ከአሁን ጀምሮ በእጅህ እስኪገለጡም ድረስ በምድር ልብ ይኖራሉ፡፡ በሰው ልጅ ጥበብ ያይደለ በእኔ ሥልጣን ከምድር ልብ ውስጥ ታወጣቸው ዘንድ መረጥሁህ፡፡ ሕዝቦቼ ተወልጄ አድጌ ሞቼ ተቀብሬ ከሞትም የተነሳሁባትን ሀገር ለማየት ኢየሩሳሌም በመሄድ ግማሹም በበረሃ ይቀር ነበር አሁን ግን አንተ ኢየሩሳሌምን በሀገርህ ትሠራለህ፡፡ በማንም እጅ ዳግመኛ ሊሠሩ የማይችሉ ቤተ መቅደሶቼን እንዳሳየሁህ ትሠራለህ፡፡ አንተም እንዳሳየሁህ በልብህ ውስጥ አኑራቸው፡፡ ስትሠራቸውም እየልካቸው ይሁን፤ ከእርዝመታቸውም በላይ ቢሆን፣ ከወርዳቸውም በላይ ቢሆን፣ በመወጣጫቸውም ላይ ቢሆን አንዳች እንዳትጨምር፡፡ ያሳየሁህ እሊህ ዐሥሩ መቅደሶች ከአንዲት ቋጥኝ ድንጋይ ሲወጡ አይተሃልና….› እያለ ጌታችን ሲነግረው ጻዲቁ ንጉሥ “ይህ እንዴት ይሆናል?” በማለት ይጠይቃል፡፡ ጌታም እውነት እልሃለሁ እነዚህ ያሳየሁህ መቅደሶች በሰው ኃይል የሚሠሩ ሆነው አይደለም፤ ጀማሪያቸው ሠሪያቸውና ፈጻሚያቸው እኔ ነኝ ነገር ግን ኃይሌ በአንተ እጅ እንዲገለጽ ለምክንያት ተልከሃል፤ አንተ አነጽካቸው እየተባለ እስከ ዕለተ ምፅዓት ድረስ ስምህ ይጠራባቸዋል…›› እያለ ይቀጥላል የቅዱስ ላሊበላ ገድል፡፡ ቤተ መቅደሶቹንም ለመሥራት ቦታውን ያውቅ ዘንድ ሱባኤ ገብቶ ሳለ ዛሬ ቤተ ማርያም ካለችበት ቦታ ላይ ቅዱሳን መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ታይተውት በቦታው ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መቅደሱን መሥራት ጀመረ፡፡ ዓሥሩን ቤተ መቅደሶች ሲሠራ እርሱ አንድ ክንድ ሠርቶ እንደሆነ ሌሊቱን አድሮ በቀጣዩ ቀን አሥር ክንድ ሆኖ ያገኘው ነበር፣ ቀንም በማይታወቁ ሰዎች አምሳል እየተገለጡ መላእክት ይራዱት ነበር፡፡
1.5. አንዳንድ ነገሮች ስለ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፡-
ቅዱስ ላሊበላ ዓሥሩም ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በጣም በሚያስገርም ሁኔታ በውስጥና በውጭ ያሉት ብዙ ቅርጾች ነገረ ድኅነትን በምሳሌ እንዲወክሉ አድርጎ ነው ያነጻቸው፡፡ የክርስቶስን መከራና በእርሱም የተገኘውን ፍጹም ዘላለማዊ ድኅነት በእያንዳንዱ ቤተ መቅደስ ውስጥ እንዴት አድርጎ በምሳሌ እንዳስቀመጠው እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ በላስታ ቅዱስ ላሊበላና አካባቢው የሚገኙ ሌሎች አስደናቂ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፡- ከአሥሩ የቅዱስ ላሊበላ አስደናቂ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪ የቅዱስ ነአኵቶለአብና የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም አሸተን ማርያም በዋናነት ሕዝበ ክርስቲያኑ የሚጐበኛቸው ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡ በላሊበላና አካባቢው ግን እጅግ ጥንታዊና አስደናቂ የሆኑ በጣም በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ሣርዝና ሚካኤል፣ ብልባላ ቂርቆስ፣ ብልባላ ጊዮርጊስ፣ አርባዕቱ እንስሳ፣ ትርኩዛ ኪዳነምሕረት፣ ገነተ ማርያም፣ ቀንቀኒት ሚካኤል እነዚህ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሲሆኑ እንዲሁም ዋልድቢት ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም፣ አቡነ ዮሴፍ ገዳም፣ ገብረ ክርስቶስ ዋሻ ቤተክርስቲያን፣ ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን፣ ቀደሊት ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ እመኪና መድኃኔዓለምና እመኪና ልደታ፣ ማውሬ እስጢፋኖስ፣ የቅዱስ ገብረ ማርያም ቤተክርስቲያን፣ ማይ ማርያም ቤተክርስቲያን፣ ተከዜ ኪዳነምሕረትና መድኃኔዓለም አንድነት ገዳም ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ ከ485-536 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በዐፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት የታነጹ ናቸው፡፡ ሌሎቹንና በሰሜን ላስታ ያሉትን ደግሞ እነ ላሊበላና ይምርሃነ ክርስቶስ አንጸዋቸዋል፡፡ ቅዱስ ላሊበላ እኛ ከምናውቃቸው ከድንቅ ሥነ ሕንፃዎቹ ሥራ በተጨማሪ ከሺህ ዓመታት በፊት በሥዕል፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሃይማኖት፣ በኢኮኖሚ፣ በውጭ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙትና በመሳሰሉት ሁሉ እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ከሺህ ዓመታት በፊት አዳራሾችን፣ ፎቆችን፣ የውስጥ ለውስጥ መተላለፊያዎችን፣ የእንግዳ መቀበያዎችን፣ የሕፃናት ማሳደጊያዎችን፣ የሕሙማን መፈወሻዎችን፣ የሕንፃ መሳሪያዎችን፣ የትምህርት ማዕከሎችን፣ የመደጎሻ ቦታዎችን ያቋቋመ መሆኑን የብራና ገድሉ እንደሚናገር የደብሩ አባቶች ይገልጣሉ፡፡ ወደፊት ተርጎመው እንሚያቀርቡልን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ከዚህ በተጨማሪ የግእዝ ቋንቋን በጽሑፍ አበልፅጎ ያቆየ ባለውለታ ነው፡፡ ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ውጭ ሌሎችንም በርካታ ቤተ መቅደሶች ሠርቷል፤ ከሀገራቸንም አልፎ በሱማሌ ሞቃዲሾ ላይ መቅደሰ ማርያም የተባለች ቤተክርስቲያን ሠርቷል፡፡ ክርስትናን ከግብፅ ምድር ጨርሰው ለማጥፋት ተንባላት በተነሡ ጊዜ ዓባይን ሊያግድባቸው ሲነሣ በብዙ ምልጃና ልመና ስለማራቸው በሀገሪቱ ውስጥ ክርስትና እስካሁን እንዲቆይ የራሱን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ ቅዱስ ላሊበላ ነቢይም ሆኖ፣ ሐዋርያም፣ ጻዲቅም፣ ሰማዕትም ሆኖ ጥበብ መንፈሳዊንና ጥበብ ሥጋዊን ከእግዚአብሔር ተሰጥቶት ንግሥናንና ክህነትን፣ ቅድስናንና ንጽሕናን በሚገባ አስተባብሮ በማያዝ እግዚአብሔርንም ሰውንም በቅንነት ሲያገለግል ኖሮ ሰኔ 12 ቀን 1197 ዓ.ም ከፈጣሪው ታላቅ ቃልኪዳን ተቀብሎ በዝማሬ መላእክት፣ በመዝሙረ ዳዊት ቅድስት ነፍሱ ከሥጋው ተለይታ ሰማያዊ ክብርን ወርሷል፡፡ ክቡር ሥጋውም ራሱ ባነጸው ቤተ ሚካኤል መቅደስ ሥር በክብር ዐርፏል፡፡
1.6.መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለቅዱስ ላሊበላ የገባለት ልዩ ቃልኪዳን፡-
1.6.1. ወደ ሰማይ ነጥቆ ወስዶት በዙፋኑ ፊት የሰጠው ቃልኪዳን፡-
‹‹ዛሬ በዚህች ቀን ከአንተ ጋር እነሆ ኪዳኔን አጸናሁ፡፡ በጸሎትህ ኃይል ታምኖ በውስጣቸው የሚያመሰግን ትሠራቸው ዘንድ ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የደረሰ ሁሉ አንተን አስቦ ‹አቤቱ ፈጽመህ ይቅር በለኝ› የሚለኝ፣ ‹ይህን የሚያስደንቅ ሥራ በእጁ ስለገለጥክለት ስለ ባሪያህ ስለ ቅዱስ ላሊበላ ብለህ ይቅር በለኝ› እያለ የሚጸልየውን በዚያ ጊዜ እኔ ጸሎቱን እሰማዋለሁ፡፡ ከሕፃንነቱ ጀምሮ የሠራውን ኃጢአት ሁሉ አስተሠርይለታለሁ፤ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ እንደ እንደተወለደባት ቀን የነፃ አደርገዋለሁ፡፡ የዕዳ ደብዳቤውንም በእጅህ ትቀደው ዘንድ ለአንተ እሠጥሃለሁ፤ ዕድሜውንም በምድር ላይ አረዝምለታለሁ፤ ቤቱንና ንብረቱን ሁሉ እባርክለታለሁ፤ በተንኮል የሚከራከረው ቢኖር ድል እንዳይነሣው አሠለጥነዋለሁ፤ እግሮቹ እየተመላለሰ ወደ ቤተክርስቲያን የገሠገሠ ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት በኤዶም ገነት ውስጥ እንዲመላለስ አደርገዋለሁ፤ መባዕ የሚያገባ ሁሉ ጥቂትም ቢሆን ብዙም ቢሆን በእጅህ ከምሠራው ከቤተ መቅደሴ የሚያመጣውን መባዕ ሁሉ ቀኝ እጄን ዘርግቼ ከእጁ ፈጽሜ እቀበለዋለሁ፡፡ ከዕጣንም ወገን በየአይነቱ ያገባ ቢኖር እንደሰው ልማድ ሥጋዬን እንደቀባበት እንደ ኒቆዲሞስ ሽቱ እቀበለዋለሁ፣ በቢታንያ እንደቀባችኝ እንደ ማርያም እንተ ዕፍረት ሽቱ መዓዛውን አሸትለታለሁ፤ ስለ ማርያም እንተ ዕፍረት እስከ ዓለም ዳርቻ ሁሉ የመንግሥቴ ወንጌል በተሰበከበት ስሟን ይጠሩ ዘንድ እንዳዘዝኩ ሁሉ ትጉሃን በሚሆኑ በሰማያውያን መላእክት ከተሞች ስሙን ይጠሩት ዘንድ አዛለሁ፡፡ ለመብራት የሚሆን ዘይት ቢያገባ በይቅርታዬ ዘይትነት ራሱን አወዛዋለሁ፣ ሰውነቱ ለዘለዓለሙ አይሻክርም፣ ከፊቱም የብርሃን መብራት አይጠፋም፡፡ ወደ ሠርግ ቤት ከሚገቡ መብራታቸው ካልጠፋባቸው ከልባሞች ደናግል ጋር በመጣሁ ጊዜ በደስታ ይቀበለኛል፡፡››
1.6.2. በኢየሩሳሌም ሳለ ጌታችን የስቅለቱን መከራ በራእይ ካሳየው በኋላ የሰጠው ቃልኪዳን፡-
‹‹ለሌሎቹ ጻድቃን ከዚህ ዓለም በሞት በሚለዩበት ወቅት በፍጹም ልቡናቸው እንደሚገባ ያገለገሉኝን ዋጋቸውን ሰጠኋቸው፣ ለአንተ ግን በሞት የምትለይበት ጊዜ ሳይደርስ በሕይወትህ ሳለህ ኪዳንን ሰጠሁህ፡፡ ማደሪያህ ከጳውሎስና ከጴጥሮስ ጋር ይሆናል፡፡ አቀማመጥህ በቀኜ ነው፣ ደቀ መዛሙርቴን በ12 ወንበር ተቀምጣችሁ በ12ቱ ነገደ እስራኤል ትፈርዳላችሁ እንዳልኳቸው አንተም ወንበርህ ከወንበራቸው አያንስም፤ ብርሃንህ ከብርሃናቸው፣ ክብርህ ከክብራቸው አያንስም፤ ኪዳንህም ከሰጠኋቸው ኪዳን አያንስም፤ ርስትህ ዕድል ፈንታህ ከእነርሱ ጋር ነው፡፡ የሰጠሁህን ቃልኪዳንና ገድልህን የሚያቃልል ሁሉ ዕድል ፈንታው ከአንተ ጋር አይሁን፣ ርስት ጉልቱም ከአንተ ርስት ጉልት አይገኝም፤ የጸናሁልህን ቃልኪዳን የማያምን ያ ሰው እኔን ክርስቶስን እግዚአብሔር አይደለም እሩቅ ብእሲ ነው እንጂ እንደሚለኝ ሰው ይሁን፡፡ መጽሐፍህን ሰምቶ የተቀበለ ሁሉ የመንግሥቴን ወንጌል እንደተቀበለ ይሁን፤ አንተን ያከበረ እኔን እንዳከበረ ይሁን፡፡ ደቀ መዛሙርቴን እናንተን የሰማ እኔን የሰማ ነው፣ እናንተን የካደ እኔን የካደ ነው እንዳልኳቸው አሁንም አንተን የሰማ ቃልኪዳንህንም ያመነ እኔን ጌታህን የሰማ ነው እልሃለሁ፡፡ መከራህንና ቃልኪዳንህን የካደ ሰው ቢኖር እኔ በምድር የተቀበልኩትን መከራ እንደ ካደ ሰው ነው፡፡ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በጸሎትህ ኃይል የታመኑ ሁሉ ማደሪያቸው ከአንተ ጋር ይሁን፤ ለቤተክርስቲያኖችህ አምኃ የሰጠ ቢኖር እንደ ደሜ ፍሳሽ እንደ ሥጋዬ ቁራሽ አድርጌ እቀበለዋለሁ፡፡››
19.3.ቤተ መቅደሶቹን ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ ጌታችን የሰጠው ቃልኪዳን፡-
ቅዱስ ላሊበላ ጌታችን ባሳየውና ባዘዘው መሠረት አብያተ ክርስቲያናቱን አንጾ ከጨረሰ በኋላ በቀኝና በግራው ዓሥር ዓሥር ኪሎ የሚመዝን የዓለት ድንጋይ ተሸክሞ ለ7 ዓመት ሲጾም ሲጸልይ ከኖረ በኋላ ጌታችን ተገልጦለት በፊት የገባለትን ቃልኪዳን በዚህም ጊዜ በድጋሚ አረጋግጦለታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹…ወደ ደጅህ የመጡት ሁሉ አስራት ይሁኑልህ፣ አንተ ከገባህበትም ይግቡ፣ አንተንም ከ12ቱ ሐዋርያት ጋር በፍርድ ቀን 13ኛ አደርግሃለሁ፡፡ ያነጽካቸውን ቤተ መቅደሶች የተሳለመውን ኢየሩሳሌምን እንደተሳለመ አደርግለታለሁ፤ መታሰቢያህን ያደረገውን፣ ገድልህን የጻፈውን ያጻፈውን፣ በዚህ ቦታ ላይ መጥቶ አማልደኝ ያለውን፣ በአማላጅነትህ የተማጸነውን ሁሉ እስከ 15 ትውልድ ምሬልሃለሁ›› ብሎ የመጨረሻውን ቃልኪዳን ሰጥቶታል፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን!
እውነት ነው አሜን!
ReplyDeleteየቅዱስ ላሊበላ ምልጃ እና ጸሎት ኩሁላችን ጋር ይሁን!
ስለተመኘን ብቻ የእርሱ ንጽህና እና ቅድስና ለእኛ ተደርጎ ይቆጠርልን!
Thank you very much my brother.
ReplyDeleteይህንን post እያደረጋችሁ እግዚአብሔር ይስጥልኝ ሁላችንንም የቅዱስ ላሊበላ በረከት ይድረሰን አሜን።
ReplyDelete