ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Monday, April 29, 2013

ሆሣዕና በአርያም …!!!


ፀሐፊ ፡- ፍቅር ለይኩን፡፡
READ IN PDF


         ‹‹ሆሣዕና›› ቃሉ የዕብራይስጥ ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹አሁን አድን›› ማለት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ከፋሲካ በፊት ያለው እሁድ የሆሣዕና እሁድ በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ ዕለትም በቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው መዝሙር፣ ማኅሌቱ፣ ቅዳሴውና ማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት ዕለቱ በታላቅና እጅግ ደማቅ በሆነ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት የሚዘከርበት ነው፡፡ ይህ በዓል እጅግ በደማቅና ልብን በሚመስጥ መንፈሳዊ ሥርዓትና ድምቀት ከሚከበርባቸው ቅዱሳን ገዳማትና መካናት መካከል የአክሱሟ ርዕሰ አድባራት ጽዮን ማርያም እና በዚህ በአዲስ አበባችን ደግሞ የእንጦጦ ማርያም በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ሆሣዕና የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ወደ ኢሩሳሌም በታላቅ ድል የገባበት ዕለት ነው፡፡ አስቀድሞ በመጽሐፍ ቅዱስ በነቢዩ ዘካርያስ፡‹‹ለጽዮን ልጅ፡- እነሆ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያቱ ግልገል በውርንጭላይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት፡፡›› ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ፡፡ ጌታ፣ አምላክና መድኃኒት የሆነው ኢየሱስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ / ሊቃውንት በብሉይ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሔር ነቢያት መልካም የሆነ ትንቢትን ከፈጣሪ ዘንድ ይዘው ሲመጡና መጪው ጊዜ ሰላምና ብልጽግና የሞላበት መሆኑን ለመግለጽ በአህያ ላይ ሆነው ነበር እየዞሩ ትንቢት የሚናገሩት፡፡ ዘመኑ የጦርነት፣ የራብ የግዞት ዘመን ከሆነ ደግሞ በፈረስ ላይ ሆነው ይናገሩ እንደነበረ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በመጥቀስ፣ እግዚእነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ የሰላም አለቃ ለኢየሩሳሌምና ለዓለም ሁሉ ሰላምንና ፍቅርን ያውጅ ዘንድ በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገብቷል ሲሉ ያመሰጥራሉ፡፡

የዋህና ትሑት ሆኖ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ በታላቅ ድልና ክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባው የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ለታላቅ ክብሩና ማዳኑ ሰዎች ሁሉ ኢየሱስ በሚያልፍበት መንገድ ልብሳቸውንና የዛፍ ቅርንጫፎችን በማንጠፍና በመጎዝጎዝ ለክብር ጌታ ክብርን፣ ምስጋናንና ውዳሴን አቀረቡለት፡፡

በመቅደስም ሳለ ሕፃናቱ፡‹‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሣዕና በአርያም!›› እያሉ በታላቅ ድምጽ እየጮኹ አመሰገኑት፡፡ አስቀድሞም ነቢይ ወካህን በሆነው በንጉሥ ዳዊት አፍ እንደተነገረው፡‹‹ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋን ለራስህ አዘጋጀህ፡፡›› የሚለው ትንቢትም ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ፡፡ የቤተክርስቲያን አባትና ሊቅ የሆነው አባ ጎርጎሪዮስም በቅዳሴው፡-

የካህናት አለቃ ወደ መጋረጃ ውስጥ በገባ ጊዜ በጸሎት ቤት የተደረገውን ድንቅ ነገር ታዩ ዘንድ ኑ፡፡ ሁሉም መለኮትን የምትሸሽግ ኅሊናትንም የምትሰውር ናት ይሏታል፡፡ የአጋዕዝትና የመናፍስት ጌታ በተዋረደ አህያ ውርንጫ ተቀምጦ ወደርስዋ ገባ፡፡ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ብሩክ ነው፡፡ አንተም የአማልክት አምላክ የእስራኤልም ንጉሥ እግዚአብሔር ብሩክ ነህ እያሉ ለሚያመሰግኑ ሕፃናት ሁሉ ጌትነቱን አሳየ፡፡ከመድኃኒትነቱ የተነሳ ከቤቱ መሠረት ሳይናወጥ ከልዑል መንበሩ ወርዶ ጸጋንና ኃይልን አሳየ፡፡ ሆሣዕና በአርያም፣ ሆሣዕና በአርያም፣ ሆሣዕና በአርያም፡፡ ብሎ እንዳመሰገነ፡፡

የክብርን ጌታ፣ የሕይወትን ራስ ‹‹ሆሣዕናሆሣዕናሆሣዕና በአርያም፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ብሩክ ነው!›› እያሉ በእናታቸው ጀርባና እቅፍ ያሉ ሕፃናትና የቢታንያ ድንጋዮች ሁሉ ሳይቀሩ በታላቅ ደስታና ሐሴት ሆነው መድኃኒት፣ አደኝና ቤዛ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ድምፅ በንጹሕ አንደበት ዘምሩለት፡፡ ምድርምና ሞላዋ፣ ውቅያኖሶች፣ ባሕሮችና ተራሮች፣ ሰማይ፣ ሰማየ ሰማያት፣ ከሰማይም በላይ ያለ ሰማይ፣ የእግዚአብሔር ፍጥረታት ሁሉ በዚህ ልዩ የሕፃናት የምስጋና ጥዑም ዜማ ተሞሉ፣ በደስታም እንደ እንቦሳ ዘለሉ፡፡

በዚህ ልዩ ሰማያዊ ቅኔ የሰማይ ሠራዊት፡- መላእክት፣ ሊቃናት፣ አጋእዝትና መናብርት ሁሉ በአንድነት ታደሙ፣ በዚህ ታላቅ የምስጋና ዜማ ምድርን በሐሴትና በደስታ ተናወጠች፣ መሠረቶቿም ተነቃነቁ፣ የፍቅር አምላክ፣ የሰማይና የምድር ሁሉ ፈጣሪ ራሱን ባዶ አድርጎ፣ የዋህና ትሑት ሆኖ በአህያ ውርንጫ ላይ ሆኖ በግልጽ መጥቷልና፡፡

ወንጌላዊው ማቴዎስ በወንጌሉ እንደጻፈልን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በቀረበ ጊዜ መላው ከተማ ይህ ማነው ብሎ ተናወጠ ይለናል፡፡ ዛሬም ይህ ማነው ለሚሉ፡በእውነት እርሱ፡- በጽኑ ፍቅሩ ጨለማውን ኃይላትን፣ የሞትን መውጊያ፣ የሲኦልን ሥልጣን፣ የኃጢአትን ኃይልና ብርታት ሁሉ የሻረ፣ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ፣ ወልደ አብ ወልደ ማርያም፣ ድንቅ፣ መካር፣ ኃያል አምላክ፤ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው!!!

በዕለት ሆሣዕና ሐዋርያት፣ ሕፃናት፣ ሕዝቡና የተከተሉት ሁሉ ቃላት በማይገልጸው ደስታና ሐሴት ውስጥ ሆነው ሲዘምሩና ሲያመሰግኑ ክርስቶስ ኢየሱስ ግን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌም በበደሏና በኃጢአቷ ምክንያት ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀጠረላትን የመዓት፣ የጥፋትና የመፍረስ ቀን አሻግሮ አይቶ ሩኅሩኁ ጌታችን እምባውን አፈሰሰላት፤ በሐዘን መንፈስ እያያትም አለቀሰላት እንዲህ ሲል ይለናል ሐኪሙና ታሪክ ጸሐፊው፣ ወንጌላዊው ሉቃስ፡‹‹ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ብታውቂ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል...፡፡››

የሰላሟን አምላክ፣ የሕይወትን ራስ የገፋችው፣ አሳልፋ በመስጠትም የሰቀለችው ኢየሩሳሌም ጌታችን እንደተናገረ ቅጥሮቿ ፈርሰው፣ ሕዝቧ እርስ በርሱ ተራርዶ፣ ልጆቿም ያለ እናት ተበትነው፣ እንዲያ የሚኮሩበትና የሚኮፈሱበት መቅደሳቸውም በአሕዛብ ተርግጦና ተዋርዶ ድንጋይ በድንጋይ ሳይቀር በፈራረሰበት፣ ሕዝቦቿም በታላቅ ሀፍረትና ውርደት ተሸማቀው፣ በዓለም ሁሉ ዙሪያ እንደ ጨው ዘር ተበትነው፣ 1800 ዓመት በላይ እስራኤል የምትባል ሀገር ከምድረ ገጽና ከካርታ ላይ ከጠፋች በኋላ ነበር እንደ ገና እንደ አዲስ ሙሽራ ጎጆ በመውጣት .. 1948 . ዳግም ዓለም ሁሉ እንደ ሀገር የተቀበላት፡፡

ይሁን እንጂ ያቺ ምድር ዛሬም ቢሆን መሽቶ በነጋ ቁጥር የጥይት ባሩድና የሮኬት አረር ጭስን የምትታጠን፣ ፍጹም ሰላምና መረጋጋት የራቃት የዓለም ሁሉ ዜና መክፈቻና መነጋገሪያ እንደሆነች አለች፡፡ የእርሷ ሰላም ማጣት የዓለም ሀገራት ሁሉ የሚታወኩበትና የሚጨነቁበት የሌት ተቀን ጉዳያቸው እንደሆነ በየቀኑ እየታዘብን ነው፡፡

የእስራኤልና የዐረቡ ዓለም ፍጥጫ፣ የፍልስጤማውያን የልዑላዊነትና የነጻነት ጥያቄ፣ የመካከለኛው ምስራቅ የነዳጅ ዘይት፣ የአካባቢው ሀገራት የሚገኙ የሀማስና የሂዝቦላ ጽንፈኞች ታጣቂ ኃይላት፣ የኢራን የኑክሌየር፣ የጅምላ ጨራሽ ኬሚካልና ባይሎጂካል መሳሪያዎች የማምረት ሽር ጉድ በአሜሪካና በምዕራባውያኑ ሀገራት መካከል ያነገሰው ውጥረትና ጥርጣሬ፣ ለእስራኤል ታላቅ ስጋት ነው በሚል አሜሪካና የምዕራቡ ዓለም ከኢራን ጋር የገቡበት ውዝግብና ክስ፣ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከኤዥያ እስከ አውስትራሊያ፣ ከአውሮፓ እስከ ሩሲያ፣ ከቻይና እስከ ፓሲፊክ ሀገራት ድረስ የተዘረጋ ትልቅ የዓላማችን የመነጋገሪያ አጀንዳ ነው፡፡

ግና በእውነትም የኢየሩሳሌም ሰላም ያለው በገፋችው በሰላሟ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እጅ ነውና ወደ እርሱ ፊቷን እስካላዞረች ድረስ እንደታወከች፣ እንደተናወጸች ለዓለም ሁሉ ጭንቅትና ውጥረት እንደሆነች ትዘልቃለች፡፡

በዘመናችንም ሰላም የሁሉም ሰው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ ሰላም በቤተሰብ፣ ሰላም በሀገራት፣ ሰላም በመንግሥታት፣ ሰላም በባልና ሚስት፣ ሰላም በአብያተ ክርስቲያናት እና በሃይማኖት ተቋማት፣ ብቻ ሰላም በሁሉም ስፍራ በሁሉ ዘንድ በመብራት የምትፈለግ እንቁ ሆናለች፡፡ ስለሆነም ሀገራት ሁሉ ከፍተኛ ወጪ የሚመድቡት ለውስጥ ሰላማቸው፣ ጸጥታና የደህንነት ጉዳያቸው ነው፡፡ ስለ ሰላም ዓለማችን የዘንባባ ዝንጣፊን በማወዛወዝ ዘምራለች፣ ስለ ሰላምም ሲባል ነጫጭ ርግቦችን በሰማይ ላይ ለቃለች፡፡

ይሁን እንጂ ዓለማችን የተመኘችው ሰላም ዛሬም የሰማይ ያህል እንደራቃትና እንደሸሻት ነው፡፡ በውስጣቸው ሰይፍ፣ ሰልፍና ጠብ ያለባቸው ሀገራትና ሰዎች በአፋቸው ሰላም ሰላም በማለት ቢሰብኩም የሰላሙ አለቃ ኢየሱስ ከልባቸው ዙፋን ተሰዷልና ሰላምን ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች ሊያረጋግጡ አልቻሉም፡፡

የጥበብና የሕይወት ምንጭ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ለምድራችን፣ ለዓለም፣ ለሀገራትና ለሰዎች ሁሉ ሰላም መፍትሔው የሰላም አለቃ የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ኢየሱስም በወንጌል፡‹‹ሰላምን እተውላችኋለሁ፣ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም፡፡›› በማለት ለደቀመዛሙርቱ የሰላምን የዘላለም ዋስትና ሕያው የሆነ ተስፋን ሰጥቷቸዋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለኤፌሶን ክርስቲያን በፃፈላቸው መልእክቱ፡‹‹እርሱ ሰላማችን ነውና!›› እንዳለ፡፡

በዓለ ሆሣዕና ክርስቶስ የጽድቅ የትሕትና እና የድኅነት ንጉሥ እንደሆነ በአደባባይ የተገለጠበት ነው፡፡ ሕዝብና አሕዛብን አንድ ለማድረግ እንደመጣ በምሥጢር የገለጠበት ዕለት ነው፡፡ በዚህች ቅድስት የሆሣዕና በዓል ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ዘንድ ለተቀበልነው ሰላማችን ማብሰሪያ ምልክት ይሆነን ዘንድ በግንባራችንና በጣቶቻችን ከምናስረው ዘንባባ ባሻገር ለልባችን፣ ለቤታችን፣ ለትዳራችን፣ ለቤተሰባችን፣ ለኑሮአችንና ለሀገራችንና ለዓለም ሁሉ ሰላም የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰላምና ፍቅር በተግባር የምናሳይበትና የምናውጅበት በዓል ይሁንልን!



ለሕዝበ ክርስቲያን ሁሉ መልካም የሆሣዕና በዓል!
ሰላም! ሻሎም!

No comments:

Post a Comment