ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Sunday, April 5, 2015

ገና '42%'...? መጓተት ብርቅ የሆነባት ሀገር!!

     ሰሞኑን 4ኛ ዓመት የዓባይ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት በሚል በሬዲዮም በቴሌቪዥን ወሬው ሁሉ ስለ ዓባይ  ነው፡፡ ተያይዞም ግንባታው 42% ደርሷል የሚል ነገር ተደጋግሞ እየተነገረን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው ፡፡ ስለ ግድቡ ባህሪይ እንዲሁም ምን ምን እንደሚያስፈልግ ፣ ስራው እንዴት እንደሚሰራ እንደሙያተኛ ማውራት አልችልም ፤ ምንም ዕውቀትም የለኝም፡፡  ያም ቢሆን ግን የሰሞኑ ሁካታና ጭፈራ ግን ሠራን ከሚባለው ጋር አልሄድ አለኝና ብዕሬን  በማንሳት የሚሰማኝን ልተነፍስ  ወደድኩ፡፡ እውነት  ለማውራት ከ 42% ይልቅ ከ 60 % እስከ 70 % ቢባል ትንሽ ምቾት ይሰማኝ ነበር፡፡ ማለቴ ላንተ ምቾት ምን አገባን ካልተባልኩኝ፡፡

ስንቶቻችሁ እንደምታስታውሱ ባላውቅም የዛሬ አራት ዓመት ገደማ የዚህ ግድብ አጥኚዎችና ተወካዮች ሲናገሩ ግድቡ በ5 ዓመት ዕቅድ ውስጥ የተካተተ መሆኑን  ወይም እነሱ በሚሉት የ 5ዓመት የ'Transformation' ጊዜ ውስጥ ተካቶ የሚጠናቀቅ መሆኑን  ነበር፡፡ ግን የተባለው የሚሆን አይመስልም፡፡ ለምን ? ምክንያት ያስፈልጋል! ፖለቲካዊ እንድምታውን ለጊዜው ወደ ጎን ትቼው እንደ ባለመብት ህዝብ ለምን እስካሁን 42% ብቻ እንደሆነና በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ለምን እንዳልተጠናቀቀ ሊገለፅልን... ሊነገረን በተገባ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡

ችግሩ ገንዘብ ነው እንዳይባል የገንዘብ እንዳልሆነ ብዙ ማሳያዎች ማቅረብ ቀላል ነው፡፡ ያን ያህል አዋጡ....አዋጡ...እያስባለ የሚያስጮህ ነገር እንደሌለ በሚታዩት ነገሮች መገመትም ይቻላል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ መጥቀስ ካስፈለገ  በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በየአዳራሹና ሆቴሉ ፣ በየእስታዲየሙና መዝናኛ ጭፈራ ቦታዎች የሚባክነው እና የሚፈሰውን የገንዘብ መዓት ነው፡፡ ይህን የተመለከተ በሀገሪቱ ትልቅ ሀገራዊ የቤት ስራዎች ያሉብን ሳይሆን የደላን፣ የሞቀን እንደሆንን የሚያስበው እንዲሁም  የሚገምተው፡፡ አውነታውም የሚያሳየው በየተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መዝለላችን ለኛ የገንዘብ ችግር አሳሳቢ እና  እዚህ ግባ የሚባል ችግር አለመሆኑን ነው፡፡

 በተቃራኒው ግን ገንዘቡ እየተረጨ በተገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ አሼሼ ገዳዬ ከምንልበት ምናለበት የሕዝብን ችግር ብንፈታበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ስንቱ ቤት መብራት የለም፣ ስንቱ ቤት የሚጠጣ ውሃ ጠፍቷል?? ጥቂቶች በሚዝናኑበት ብዙዎች በሚማረሩበት አስረሽ ፍቺው አይነት ደስታ.... ሀገር አቀፍ ስራዎች ለምን ይስተጓጎላሉ ( ይጓተታሉ)? ለምንስ በታቀደላቸው ጊዜና ሰዓት እንዲፈፀሙ አናደርግበትም??
የሚዝናናው ይዝናና ቢራውም ውስኪውም ይጠጣ.. ይረጭ፤  ለምን ተረጨ ፣ መዝናናትስ ለምን አስፈለገ...አይባል ይሆናል፡፡ ግን ይህ ሲደረግ የተቀረው ህዝብ ምን እየተሠማው እንደሚመለከታቸው  ቢያውቁትና ቢረዱት እንዴት መልካም ይሆን ነበር፡፡ በዚህ መሐል ግን  ካለው ላይ እየተቆረሰ...  ከደሞዙ እየተቆረጠ...ከሚሞላው የሞባይል ካርድ የብር መጠን ላይ  ያለእውቅናው እየተዘረፈ.... በየዋህነት 8100 ሲባል ብሩን እየገበረ የሚገኘው እንደእኔ አይነቱ ምስኪንስ በምን ይጨፍር?  ምንስ እየጠጣ ይደሰት?

እንደዚህም  ሆኖ አሁንም ደኻው እየተለመነ ሀብታም እየጨፈረ አራተኛ ዓመት ገባን፡፡ ያለ ምንም ጥናት በሚመስል ሁኔታ በአምስት ዓመት ያልቃል ያሉን አሁንም በአራት ዓመቱ ገና ግማሹም ላይ አልደረሰም፡፡  ምናልባት ያዘገያቸው የአየር ፀባዩ ክብደት የዓባይ በረሃ ሙቀት ከብዷቸው ይሆን? ደግሞ ፀሐይ ሳይበግራቸው ነው የሚሰሩት ተብሏል፡፡  ምን ነካቸው ይባላል ታዲያ?
       የሁልግዜም ጥያቄዬና ሁሌም ሳስበው የሚያበሳጨኝ ለምን እንደሆነ ባላውቅም እኛ ሀገር ምንም ዓይነት ሰራ ወይም ግንባታ ሲጀመር ያለው የደሰ ደሰ አከባበር እና ሁካታ.... እንዲሁም በተቀመጠለት ጊዜና ሰዓት በጥራት መስራት አለመቻላችን ነው፡፡ ምን እንደሚይዘን ምን እንደሚያዘገየን ሳስበው ይገርመኛል፡፡ " ብስራት....መጋጥ ታውቃለህ? " ብሎኝ ነበር  አንድ ጓደኛዬ በአንድ ወቅት፡፡ ለመጋጥ እንዲመቻቸው ይሆን የሚያዘገዩት?

     የመንገድ ልማት ይባልና ስራ ይጀመራል፤ በየቦታው ይቆፈራል፡፡  ሠብስበው 'ሊቀብሩን' ይመስል በየአካባቢው ጉድጓድ በጉድጓድ ያደርጉታል፡፡ ' እህ...እንዴት ነው? ' ሲባሉ በአንድ ዓመት ውስጥ ያልቃል ብለው ይደሠኩራሉ፡፡ በአንድ ዓመት የተባለው በሶስት ዓመቱ ያልቃል፡፡ ይቅርታ የለም!

መብራት ሲያስቸግርም እንዲሁ የኤሌትሪክ ኃይል ችግሩን ደርሠንበታል በሶስት ወር ችግሩ ይፈታል ይሉንና በትንሹ አንድ ዓመት ፈጅተው አስጨብጭበዉ ያስመርቁታል፡፡

የቤት ልማት ኮንዶሚኒየም ለሕዝቡ ሠርተናል ይባልና ዕጣ ሊወጣ ነው....ዕጣ ሊወጣ ነው አስብለው ዕጣው ይወጣል፡፡ የደረሳችሁ ቅድመ ክፍያችሁን ቶሎ ጨርሱ ተብሎ አሯርጠው ያስከፍላሉ፡፡ ከዛ ቤታችንስ ሲሉ ገና አላለቀም፡፡ ቤቱ በዕጣ ደረሰ ማለት ትርጉሙ በአጭርና በተወሰነ ጊዜ ወዲያውኑ መሰጠት አለበት ነው፡፡ የሚሆነው ግን በተገላቢጦሽ ነው፡፡ ኮንዶሚኒየም ደርሶካል ተብሎ ከቀድሞ ቤቱ የተፈናቀለው ህዝብ  በሚከፍለው ክፍያ ቤቱ ይሰራለትና ከዓመት ከሁለት ዓመት በኋላ ይሰጠዋል፡፡ ለዛውም የይድረስ ይድረስ ተሠርቶ፡፡ መቼም ኮንዶሚኒየም የደረሳችሁ ታውቁታላችሁ፡፡

የባቡር ግንባታም ከተጀመረ ቆየት ብሏል፡፡ የሀገር ሀብት ሲበላሽና ሲቆሽሽ ሲወድም እየታየ በማን አለብኝነት ዝምታ ተመርጦ ቀናት ዓመታት መሆን ጀምረዋል፡፡ የባቡሩ ስራው ስንት ዓመት ሆነው? መንገዶች ፈራርሰው ቤቶች ተገማምሰው አይተን ለምደን አድረን ውለናል፡፡ ያላለቀውን አልቋል ተብሎ እስከ መመረቅ ተደርሶ በስንፍናችን ካባ ላይ ውሸትን ደርበን እያደግን ነው ....ወገን በርታ እንባባላለን፡፡ ማንን ለመሸወድ እንደሆነ ሳይገባን ቀናት ወራትን ወራቶች ዓመታትን እየወለዱ እኛ እንደ ዔሊ ጊዜው እንደ ጥንቸል እየበረረ ነው፡፡የጊዜው መሮጥ ምንም አያሳስበንም፡፡" አረ..አነተ ጊዜ ቁም ! " አይባል ነገር ...ይሩጣ...!! ነገ እናገኘው የለ ብለን ቀጠሮ ይዘንለታል፡፡

ለምን በድሃ ገንዘብ እንደሚቀለድ ሁሌም ግራ ይገባኛል፡፡ ድፍን ጥሬ መሆናችን ማብቂያው መቼ ይሆን እላለሁ፡፡ 'Transformation' የሚል ፈሊጥ ተቀምጦ በ5 ዓመት ይኼን ...ይኼን እንሠራለን ፣ እንገነባለን ይባላል፡፡ እንደ ጉድ  ይጨበጨባል፡፡ ከአፍሪካ አንደኛ ያደርገናል ፤ ወየውልሽ...መጣንብሽ...ምን ትሆን አንቺ  ዓለም ብለን ዘራፍ እንላለን፡፡ በሠላማዊ ሠልፍ ከተማውን መላ ሀገሩን ድብልቅልቅ እናደርገዋል፡፡
ግና የተባለው መሆን ሳይችል ሲቀር...ገንዘቦች ሲባክኑ የሀገር እና  የሕዝብ ሀብት ሲባክን ግለሰቦች በአንዴ ተስፈንጥረው የሃብት ማማ ላይ ሲቀመጡ..... የታለ የገባችሁት ቃል የተከበረው ? የታለ በታቀደው እና ይሰራል የተባለው በተባለውና በታቀደው ጊዜና ሰዓት ያለቀው? የታለ....የታለ.... ለምን...ብሎ የሚጠይቅ የለም፡፡ የህዝቡን ዝምታ ትቼው ከራሳቸው ይህን ዕቅድ ከሚነድፉትና ከሚያወጡት አካላትም ጥቂት 'ለምን?'  የሚሉ እንዴት እንደሌሉ ሳስብ መጨረሻችን ማየት እናፍቃለሁ፡፡  ወይስ እራሳቸውም አያምኑበትም ?? እባካችሁን የምታውቁ ካላችሁ ንገሩኝ፡፡ ሳስበው ሳስበው እነዚህ የኢትዮጵያን ህዳሴ መሪዎች .... ፊት አውራሪዎች ነን ባዮች በሚያወሩት ወሬ እራሳቸውም አያምኑበትም፡፡ ጊዜው እንዳደረጋቸው እየተገለባበጡ መዝለቅ ይመስለኛል ምርጫ ያደረጉት፡፡

የዓባይ ግድብም ነገር ይኸዉ ነው በ" 5ዓመት ውስጥ...ይጠናቀቃል" ተብሎ ተደሰኮረልን፡፡ ነገርግን በ4 ዓመቱ ገና 42% ነው ፡፡ በሚገርም ስሜት ውስጥ ሆነው በጀብደኝነት 'ገና ሌላ እንገነባለን' ይሉናል፡፡ ምነው ተኛችሁበት... አደራችሁበት እንዳይባሉ እና እንዳይወቀሱ ይሆን እንዴ ገና ሌላ እንገነባለን የሚሉን?? ቁምነገር የሚሆነው የበለጠ ታማኝትን የሚያመጣው ግን ሌላ እንገነባለን ሳይሆን ስለ እስካሁኑ የግድቡ የስራ ሂደት በዝርዝር እየተነገረ እንዴት 42% ሊሆን እንደቻለ ቢነግሩን ነው፡፡ መቼም ይሄ ፀረ ልማት አያስብልም፡፡ እኔ በግሌ ምክንያታቸውን ማወቅ መስማት እፈልጋለሁ፡፡ ምንም ይሁን አይሁን ያሳምን አያሳምን በዜግነቴ በማደርገው አስተዋጽዖ ዝርዝር መረጃዎች ሲቀርቡ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ይነገረኝ...ይነገረን!

ከጥያቄ በፀዳ መልኩ እና ከተጠያቂነት ለመራቅ ከተፈለገ ሁልጊዜም ህዝብን ባከበረ መልኩ በዕቅድና በጊዜ ስራዎችን መስራት መልመድ አለብን፡፡ መዘግየት ባህላችን እስኪመስል ደረስ ክፉ ልምድ እየለመድን መጥተናል፡፡ መንገድ ሲሰራ  ፣ ውሃ ሲዘረጋ ፣ መብራት ፣ ስልክ....የቤት ግንባታ ሁሉም ላይ በጊዜ ያለመጨረስ አባዜ ተፀናውቶናል፡፡ አንዱ አካባቢ ሁሉ ሲሟላለት ሌላኛ አካባቢ ይሰቃያል፡፡ አንዱ ሲስቅ ሌላው ያዝናል፡፡  ሕዝቡ እንዲከፋፈል ተደርጎ ዝም እንዲል ተደርጓል፡፡

ጥያቄዎች፦

የዓባይስ ጉዳይስ እየዘገየ ዓመታት ቢጨምሩ  የየትኛው አካባቢ ጉዳይ ይሆን?? ማንስ ዝም ይል ይሆን??

ቸር ሰንብቱ::

ኦ....የዘነጋሁት.....  የሚቀጥለው ዓመትስ ስንት 'ፐርሰንት' ደረሰ  ትሉን ይህን??

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!

2 comments: