ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Tuesday, August 16, 2011

ቡሄ - « ደብረታቦር »


    በዋዜማው. . .
በዋዜማው የሠፈር ልጆች በየቤቱ እየዞሩ ሆያ ሆዬ! አሲዮ ቤሌማ እያሉ ይጨፍራሉ።
ቡሄ በሉ፣ ልጆች ሁሉ
ቡሄ መጣ፤ መላጣ
ቅቤ ቀቡት፣ እንዳይነጣ
ክፈትልን በሩን
የጌታዬን
እዚያ ማዶ ነጭ ሻሽ
እዚህ ማዶ ጥቁር ሻሽ
የእኔማ ጌታ ነጭ ለባሽ።
የወንዜው ነብር የወንዜው ነብር
የኛማ ጌታ ሊሰጡን ነበር።
ሆይ ሾህዬ ሎሚታ
ልምጣ ወይ ወደማታ።
ለብሩ ነወይ ነወይ ሽጉዱ
በአባትህ ጊዜ ሰንጋ ነው ልምዱ፡፡
                                                                                                              

ነሐሴ ፲፫
በቤተ ክርስቲያን ዘንድ  «ደብረታቦር» እየተባለ ይጠራል፡፡
«…መጣና መጣና
ደጅ   ልንጠና………
መጣና በአመቱ 
አረ እንደምን ሰነበቱ
ክፈቱልን  በሩን
የጌታዪን ! »

ቡሄ

ቡሄ! በመላው ሀገራችን በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን የሚከበር በዓል ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ዓቢይ (ዋና) በዓላት አንዱ ይሄ 'ደብረ ታቦር' የምትለው የቡሄ በዓል ነው።
ቡሄ ማለት ብራ፣ ብርሃን፣ ደማቅ  ገላጣ፣ የተገለጠ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት በዓል የሚዘከርበት እና ለበዓሉም ችቦ ስለሚበራ የብርሃን በዓል በማለት የቡሄ በዓል እንላለን፡፡
በሌላ በኩል ቡሄ ሲመጣ የክረምቱ ጨለማነት አልፎ ወደ ብርሃን፣ ወደ ጥቢ የሚያመራበት፣ ወደ መፀው የሚዘለቅበት ወገግታ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበትና የሚሸጋገርበት እንዲሁም  የሚታይበት ወቅት በመሆኑ እና ከቡሄ በኋላ የጠነከረ ክረምት ስለማይኖርም           
"ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፣
ከጮኸ የለም ሌሊት"እየተባለም ይነገራል፡፡ ላው "ሙልሙል" የሚታደልበት በዓል በመሆኑም ቡሄ ተብሏል፡፡      
‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹፡፡››››››››››››
"መጣና ባመቱ
አረ እንደምን ሰነበቱ
ክፈትልኝ በሩን የጌታዬን
ሆያ-ሆዬ-"
እያሉ ልጆች በዜማ እያወረዱ፣ በየመንደሩ እየተሽከረከሩ የሚጫወቱት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረ፣ አሁንም እየቀጠለ ያለ ትውፊት ነው፡፡
ቡሄ በሉ ! !
ቡሄ በሉ ! !
ያዳም ልጅ ሁሉ`! !
የኛማ ጌታ የአለም ፈጣሪ
የሰላም አምላክ፣ ትሁት መካሪ
ድምጽህን ሰማና በብሩህ ደመና
የቡሄው ብርሃን ለኛ መጣና
ያዕቆብ ዮሃንስ ! እንዲሁም ጴጥሮስ
አምላክን አዩት ! ሙሴ ኤልያስ
አባቱም አለ ! ልጄን ስሙት
ቃሌ ነውና ! የወለለድኩት
ድምጽህን ሰማና በብሩህ ደመና
የቡሄው ብርሃን ለኛ መጣና።
የዚህ በዓል መሠረት የክርስቲያን እምነት ሲሆን፣ የታቦር ተራራ የሚገኘው አሁን ፍልስጥኤም ተብሎ በሚጠራው ሀገር ነው፡፡ ደብረ ታቦር ወይንም የታቦር ተራራ ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት ደቀመዛሙርቱን ይዞ ወደ ተራራው የወጣበትና ፊቱ እንደ ፀሐይ የበራበት ልብሱም እንደብርሃን ነጭ የሆነበት ቦታ ነው፡፡ ይህ ቦታ ጌታ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ተራራ ነው።
ስለ ደብረታቦር  ረጅሙ ተራራ
          ይህ ተራራ ማን ነው? ወንጌላዊው ማቴዎስ "ረዥሙ ተራራ" በማለት የጠራውና ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ "ቅዱስ ተራራ" በማለት ጠርቶታል፡፡ ሥርዓተ ሐዋርያትን የያዘው ሲኖዶስ የተሰኘው መጽሐፍም በስሙ "ታቦር" በማለት ጠርቶታል፡፡ ከዚህ በመነሳት ረዥሙ እና ቅዱሱ ተራራ በማለት ቅዱስ መጽሐፍ የገለጠው ደብረ ታቦር / የታቦር ተራራ/ ነው ማለት ነው፡፡

የታቦር ተራራ ትንቢት የተነገረለት ምሳሌ የተመሰለለት ደብር ነው፡፡ ትንቢት "ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል" በማለት ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ተናግሮአል፡፡ ምስጢረ ብርሃንን /መለኮትን አይተዋልና፡፡

በነቢይነትና በምስፍና ሕዝበ እግዚብሔርን ያገለገሉትዲቦራ’ ናባርቅ’ ጠላታቸውሲሳራን’ ድል ያደረጉት በዚህ ተራራ ነው፡፡ የእስራኤል ጠላት ክፉ ሰውሲሳራ’ በዚህ ተራራ ድል እንደሆነ በልበ ሐዋርያት ይፈታተን እና በክፉ አሳብ ያጠራጥራቸው የነበረ ክፉ ጠላት ሰይጣንም በዚህ ተራራ ድል ተነሥቷል፡፡ ምሳሌው ተፈጸመ፡፡ ሌላው ደብረ ታቦር በግዕዝ ቋንቋ ሲሆን የታቦር ተራራ ማለት ነው፡፡ ማቴ 07÷1-8::
ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ለምን?

...ሙሴና ኤልያስ ኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ...
      የማቴ.17፤1-5 " ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ።
እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስንጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ።” እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው። “……በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።"
 ዮሐንስ፣ ያዕቆብና ጴጥሮስ ለምን ተመረጡ?
      እግዚአብሔር በልዩ ልዩ ምክንያት ይመርጣል፡፡ ለአገልግሎት ይለያል፣ ምስጢር ይገልጣል ወዘተ ሦስቱን ደቀ መዛሙርት የመረጠበት ምክንያት አይታወቅም፡፡ ሙሴ ለምን መስፍን እንደሆነ አይታወቅም፤ አሮን ለምን ካህን እንደሆነ አይታወቅም "ሰው ፊት ያያል እግዚአብሔርን ግን ልብን ያያል" ዳዊትን ሊቀባ የሄደውን ሳሙኤል የእሴይን ልጆች እያየ ሲያሳልፍ የዐይኑን አምሮት ይሄ ይሆንን ይል ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን ወንድሞቹን እያሳለፈ ብላቴናው ዳዊትን ለመንግሥት የመረጠበት ምክንያት አይታወቅም፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሦስቱ ደቀ መዛሙርት የተመረጡበትን ምክንያት ሲያትቱ የዳሰሷቸውን ጥቂት ነጥቦች እንመልከት፡-
ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ሹመት፣ሽልማት፣ ክብር ፈላጊዎች ነበሩ፡፡ ከዚህ ሃሳብ እንዲወጡ ከብልየታቸው እንዲታደሱ ለይቶ አውጥቷቸዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ለድኀነተ ዓለም የመጣው በሕማማቱ በሞቱ ቤዛ የሚሆነን አምላክ "ልሰቀል ነው" ባላቸው ጊዜ "አይሁንብህ" ብሎት ነበር፡፡ እንዲህ ያለው ሃሳብ የጠላት እንጂ የሰው ልጆች ሊሆን አይችልም ከሞቱ በቀር ድኀነት ሊያስገኝልን የሚችል የለምና፡፡ ደቀ መዝሙሩ ግን ከሞተ ክብሬ ምንድን ነው ብሏልና "አይሁንብህ" አለ፡፡ /ማቴ. 16/ በሌላም ስፍራ እንዲሁ "ሁሉን ትተን ተከተልንህ እንግዲስ ምን እናገኝ ይሆን?" በማለት ይጠይቃል፡፡ /ማቴ.19/፡፡ ጌታ ግን ዋጋችሁ ሰማያዊ ክብራችሁ ዘላለማዊ ነው ሲል እስከ ፍጹማን መዓርግ ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ አድርሶ ብርሃነ መለኮትን ገልጦ ተስፋውን ነገራቸው፡፡

ሁለቱ ወንድማማች ደቀ መዛሙርትም እናታቸውን ልከው ሹመት ሽልማት መዓረግ ለምነዋል፡፡ ስለዚህም ጌታችን በደብረ ታቦር "በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው ነገር" ስለሞቱ እንዲነጋገሩ አደረገ፡፡ ሞቱ እርግጥ ሆነ ማለት ነው፡፡ አባቱም "ኦሆበልዎ ለክርስቶስ" እሺ በሉት እርሱን ስሙት፡፡ ሞቱ እርግጥ በመሆኑ ከልባቸው እንዲጠፋ መርጦ ወደ ቅዱስ ተራራ ይዟቸው ወጥቷል፡፡                                                                            ‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹፡፡››››››››››››

                   
መጣና መጣና ደጅ ልንጥና
መጣና ባመቱ እንዴት ሰነበቱ፣
ክፈት በለዉ በሩን የጌታዪን
ክፈት በለዉ ተነሳ ያንን አንበሳ፣
መጣሁኝ በዝና ተዉ ስጠኝ ምዘዝና
የኔማ ጌታ የገደለበት
ስፍራዉ ጎድጉዶ ዉሃ ሞላበት
እንኳን ሰዉና ወፍ አይዞርበት
ያሞራ ባልቴት ዉሃ ትቅዳበት።
የኔማ ጌታ የሰጠኝ ካራ
ከዚህ ብመዘዉ ጎንደር አበራ፣
የኔማ ጌታ የሰጠኝ ስንዴ
ገና ሳልበላዉ አበጠ ክንዴ።
ወይ የኔ ጌታ የሰጠኝ ሙክት
እግንባሩ ላይ አለዉ ምልክት፣
መስከረም ጠባ እሱን ሳነክት
ሆያ ሆዪ፣
ሆያ ሆዪ
ወይ የኔ ጌታ
ዋርካ ነህ ዋርካ
ቢጠለሉብህ የማታስነካ
ለእማ ወራ
የኔማ እመቤት፣ እሜት እሜት
ሎሚ ተረከዝ ትርንጎ ባት
የኔ እማ እመቤት የፈተለችዉ
የሸረሪት ድር አስመሰለችዉ
ሸማኔ ጠፍት ማርያም ሰራችዉ
ለዝያች ለማርያም እዘኑላት
አመት ከመንፈቅ ወሰደባት
የኔማ እመቤት መጣንልሽ
የቤት ባልትና ልናይልሽ።
የኔማ እመቤት ብትሰራ ዶሮ
ሽታዉ ይጣራል ገመገም ዞሮ
የኔማ እመቤት የጋገረችዉ
የንብ እንጀራ አስመሰለችዉ።
       በገጠርም ሆነ በየከተማው ልጆች ጅራፋቸውን ገምደው ሲያጮሁ (ሲያኖጉ) ይሰነብታሉ። እናቶችም ለበዓሉ ዝግጅት ስንዴ ሲለቅሙ፣ ሲፈትጉ፣ ሲፈጩ ይሰነብታሉ።  በተለይ ነባሩን ትውፊት ይዞ የሚገኘው በገጠር አካባቢ ፡፡ ቡሄኞቹ ልጆች ለበዓሉ አስቀድመው ይዘጋጃሉ፡፡በዚህ ጊዜ እናቶች ካዘጋጁት ዳቦ ይሰጧቸውና እየገመጡ ጅራፋቸውን ሲያጮሁ ያመሻሉ። የቡሄ ዕለት ለእያንዳንዱ የቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ ልጅ አንዳንድ ሙልሙል ዳቦ በልጆቹ ልክ ይሰጣል። በቆሎ ተማሪዎች ዘንድ ደግሞ ደብረ ታቦርየተማሪዎች በዓልነው። ተማሪዎቹ ቀደም ብለውስለ ደብረ ታቦር" እያሉ እህሉንም፣ ብቅሉንም፣ ጌሾውንም ይለምኑና ጠላውን ጠምቀው፣ ዳቦውን ጋግረው፣ ቆሎውን ቆልተው ለደብረ ታቦር ዕለት ሊያስቀድሱ የመጡትን ምዕመናን ሁሉ ይጋብዛሉ።
እስቲ የሙልሙልን ትርጉም እንይ
   ጌታችን ብርሃነ መለኮቱ በገለጠበት ዕለት ጊዜው ምሽት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እረኞች ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር፡፡ የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጡ፡፡  አሁን ታዲያ «ቡሄ» ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና ችቦ በማብራት በዓሉን የምናከብረውም ከዚህ በመነሣት ነው፡፡ስጦታው ቤተሰባዊነትን፣ ፍቅርንና መተሳሰብን መግለጫ ነው፡፡ ወደ ቤታችን "ቡሄ" እያሉ ለሚመጡ አዳጊዎችም ዘምረው እንዳበቁ የሚሰጥ "ሙልሙል" ዳቦ አለ፡፡ ለምሳሌ ሐዋርያት ምስራች ሊነግሩን፣ ወንጌል ሊሰብኩን በደጃፋችን ቆመው "ቡሄ በሉ" የሚሉንን አዳጊዎች የሚበሉትን መስጠታችን ምሳሌያዊ /መጽሐፋዊ/ ነው፡፡ ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ባስተማራችሁበት፣ በደረሳችሁበት ተመገቡ ብሏቸዋል፡፡ /ማቴ 10÷12/ ሕፃናቱም ሊዘምሩ ሲመጡ ዳቦ መስጠት ልማዳዊ ብቻ አይደለም፡፡ ሕፃናቱ የደቀመዛሙርት ምሳሌ ናቸው፡፡ መዝሙራቸው ደግሞ ሐዋርያት "የምስራች" ይዘው የመምጣታቸው ምሳሌ ነው፡፡
ሐዋርያት በገቡበት አገር አስተምረው አጥምቀው የጸጋ ልጅነትን አሰጥተው በረከት አድለው እንደሚሔዱም፣ ልጆችም ዘምረው፣ አመስግነው፣ መርቀው "ውለዱ ክበዱ፣ ሀብት አግኙ፣ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ያድርጋችሁ ...." ይላሉ፡፡
የቡሄ በዓል እንዲህ ያለ መንፈሳዊና ባህላዊ ሁኔታዎችን ያጣመረ ቢሆንም በተለይ በከተሞች አካባቢ የሚታዩ አንዳንድ ችግሮች የበዓሉን ታሪክ፣ ባህልና፣ የአከባበር ሥርዓት እያጠፉት ቢገኙም በከተማዋ ዳርቻ የሚኖሩ ጎረምሶችም በኦሮምኛ የቡሄ ጭፈራቸውን፣ ቄጠማ እያበረከቱ የሚያስኬዱበት ሥርዓት አላቸው፡፡
‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹፡፡››››››››››››
ዜማ
ይሄ የንጋት ወጋገን ሲፈናጠቅ በጠዋት ውርጭ የሚዘመር ሲሆን በከባድ ድምጽና በጅራፍ ጩኸት የሚታጀብ፣ ስራዬ ተብሎ በገደላገደል ስር እንዲያስተጋባ ተደርጎ ብዛት ባላቸው ህጻናት በከፍተኛ ድምጽ የሚዘመር ነው። ሙሉ ዜማው ብዙ ቢሆንም በጥቂቱ እንዲህ ይላል
ቡሄ ! ቡሄ
ቡሄ ! ቡሄ
አበባ ማለት ያደርሳል ካመት (ጅራፍ ጥንጅት ድምጽ)
ኦሆ!
ቡሄ ቡሄ !
ቡሄ ቡሄ !
ቡሄ ! ቡሄ!( የጥንጅትና የጅራፍ ድምጽ )
ቡሄ ! ቡሄ!
ጅራፍ
 በገጠርም ሆነ በከተማ ጅራፍ የሚያጮኹ ሰዎች አይታችሁ ይሆናል፡፡ የጅራፉ ድምፅ ምሳሌ የባሕርይ አባቱን የአብን ምሰክርነት ቃል፣ማለትም «የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡ እርሱን ስሙት» ብሎ ሲናገር የነበረው  ነጎድጓዳማ ድምጽ ለማሰብ ነው፡፡ በወቅቱ ሙሴና ኤልያስ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብ ደንግጠው ነበር፡፡ ያን ለማሰብ በሀገራችን ጅራፍ ማጮህ የተለመደ ሆኗል፡፡ሌላው ጅራፍ መገመድ እና ጀራፍ ማጮኸ ሁለት ዓይነት ምስጢር ይዞ የሚከወን ትውፊታዊ ተግባር ነው፡፡ የመጀመሪያው ግርፊቱን እና ሞቱን እናስብበታለን፡፡
የጅራፍ ትውፊታዊነት /ውርስ/ መጽሐፋዊ ትምህርትና ምስጢር ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ጨዋታውን በተራራማ አካባቢ፣ ከመኖሪያ ቤት ርቆና፣ በሜዳ ማድረጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ጅራፍን በርችት መቀየር የሚያመጣውን የምስጢር ተፋልሶ ብቻ መመልከት ከማኀበራዊ ጎጂ ገጽታው በላይ እንድናስወግደው ያስገድደናል፡፡            ‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹፡፡››››››››››››
ከማጠናቀቄ በፊት ጥቂት የቡሄ ዜማዎችን ልጋብዛችሁ
በአገራችን ቡሄን ተከትሎ፣ የፍልሰታ፣ በአል በደማቅ ይከበራለ፣ በተለይ ወደ ሰሜኑ የኢትዮጽያ ክፍል አሸንዳ ወይም ሻደይ የሚል መጠርያ ያለዉ በአል በልጃገረዶች ዘንድ ተወዳጅ እንደሆነም ይነገርለታል። በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የቡሄን በአል አከባበር እና ትርጉሙን እንዲሁም የፍልሰታ ማለት የአሸንዳን በአል አከባበርን  እንቃኛለን

   ቡሄ በሉ
ልጆች ሁሉ
ቡሄ መጣ
ያመላጣ 
 ቅቤ ቀቡት  ጸጉር ያዉጣ
ቡሄ መጣ ተኳኩሎ 
ሳይወጣብን እንጨፍር ቶሎ 
 ‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹-1-››››››››››››
   መጣና መጣና 
 ደጅ ልንጥና
መጣና ባመቱ 
 እንዴት ሰነበቱ፣ 
 ክፈት በለዉ በሩን
የጌታዪን
ክፈት በለዉ ተነሳ
ያንን አንበሳ፣
መጣሁኝ በዝና
                                    ተዉ
ስጠኝ ምዘዝና                                                                                           ‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹-2-››››››››››››
በወሎ አካባቢ የቡሄ አከባበር እንዴት ይሆን?
የኔማ እመቤት፣
እሜት እሜት 
 ሎሚ ተረከዝ ትርንጎ ባት
የኔ እማ እመቤት የፈተለችዉ
የሸረሪት ድር አስመሰለችዉ
ሸማኔ ጠፍት ማርያም ሰራችዉ
ለዝያች ለማርያም እዘኑላትአመት 
ከመንፈቅ ወሰደባት
እያሉ ልጆች ወይዛዝርትን በሞያቸዉ ያወድሳሉ።
‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹-3-››››››››››››
የኔማ ጌታ የገደለበት
ስፍራዉ ጎድጉዶ ዉሃ ሞላበት
እንኳን ሰዉና ወፍ አይዞርበት
ያሞራ ባልቴት ዉሃ ትቅዳበት።
የኔማ ጌታ የሰጠኝ ካራ
ከዚህ ብመዘዉ ጎንደር አበራ፣
የኔማ ጌታ የሰጠኝ ስንዴ
ገና ሳልበላዉ አበጠ ክንዴ።
እያሉ ልጆች አባወራን እያወድሱ ጅራፍ እያጮሁ ይጨፍራሉ
‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹-4-››››››››››››
ተዉ ስጠኝና ልሂድልህ
እንዳሮጌ ጅብ አልጩህብህ 
 ኸረ በቃ በቃ
ጉሮሮአችን ነቃ 
 ኸረ በስላሴ
ልትወጣ ነፍሴ 
 ብትሰጠኝ ስጥኝ ባትሰጠኝ እንዳሻህ
ከነገሌ ሁሉ አነሰ ወይ ጋሻህ
እያሉ መልስ አልሰጥ ያለን አባወራን ያሳለቃሉ፡፡
‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹-5-››››››››››››
ወይ የኔ ጌታ የሰጠኝ ሙክት
እግንባሩ ላይ አለዉ ምልክት፣
መስከረም ጠባ እሱን ሳነክት፣
የኔማ እመቤት መጣንልሽ
የቤት ባልትና ልናይልሽ። 
የኔማ እመቤት ብትሰራ ዶሮ
ሽታዉ ይጣራል ገመገም ዞሮ
የኔማ እመቤት የጋገረችዉ 
                                                  የንብ እንጀራ አስመሰለችዉ።   እያሉ ልጆች እማወራን እያወደሱ ይጨፍራሉ።
ሆያ ሆዪ፣
ሆያ ሆዪ
ወይ የኔ ጌታ ዋርካ ነህ ዋርካ
ቢጠለሉብህ የማታስነካ
እየተባለ የሚጨፈርበት የቡሄ ጨዋታ ወደ ከተማዉ አካባቢ በአንዳንድ ቦታ መልኩን መቀየሩ ሊያሳስበን እንደሚገባበአሁኑ ጊዜ፣ በተለይ አዲስ አበባ ይሄንን መንፈሳዊና ባህላዊ መሠረት በመልቀቅ ለሕሙማን፣ አዛውንት እንዲሁም ለእንስሳት ድንጋጤ የሚፈጥረውንና ለእሳት አደጋ የሚያጋልጠውን ባእዳዊ ርችት በመተኮስ ሆኗል የሚከበረው።
በመጨረሻ
    በዓለ ደብረ ታቦር ከነዚህ ምስክር ካላቸው ትምህርቶቹ፣ ምስጢር ከሚራቀቅባቸው ትርጓሜያቱና ከትውልድ ትውልድ በቅብብል በተላለፈው ቅዱስ ትውፊት ጋር ሃይማኖታዊ ባሕል ሆኖ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን አዳጊዎች ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ይዘው እንዲያድጉ ጥቆማ በመስጠት፣ ግጥም በመግጠምና ምስጢሩን በማብራራት የመጀመሪያዎቹ ባለድርሻዎች ወላጆች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሚሰሙ ግጥሞች ስድብ፣ ፌዝና ሥላቅ የተቀላቀለባቸው ይሆናሉ፡፡ ሕፃናቱም ዝማሬውን ሲጀምሩ "ከሰጡን እንነሣ ከነሱን እናርዳ" ብለው ይጀምሩታል፡፡ ከሰጡን እንመርቃለን ካልሰጡን እንራገማለን በማለት፡፡ አሳሳቢው ነገር ደግሞ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ወደ ገንዘብ ማግኛነት የቀየሩ ሁኔታዎች መታየታቸው ነው፡፡ ዳቦ /ሙልሙል/ ትምህርቱንም፣ ምስጢሩንም፣ ትውፊቱንም በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ቤተክርስቲያን የምስጢር ግምጃ ቤት ናት የምታከናውነውን ሁሉ ከበቂ መረጃ ጋር ነው ተግባራዊ የምታደርገው፡፡ በተለይ ወጣቱ ክፍል ይህንን አውቀን ተረድተን ለቀሪው ትውልድ ማስተላለፋ እንችል ዘንድ ከክፉ ጠላት ከሰይጣን ፈተና፣ በሽታ ከመሳሰሉት ችግሮች ለመዳን ወደ ተራራዋ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሸሽ ከክፉ ነገሮች ሁሉ ማምለጥ ይቻላል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር የሚጠለሉ ሁሉ ዕድሜያቸው ይረዝማል፡፡ አስተዋዮችም ይሆናሉ ሁሉን ማየትና የሚጠቅማቸውን መምረጥ ይችላሉ በሥነ-ምግባር የታነፁ አገርንና ወገንን የሚጠቅሙ ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን በመጠጋት ከክፉ ሁሉ የሚያመልጡ ይሆናሉ ለዚህም የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
አውዳዓመት ለአመት፣
ድገምና አመት . . ድገምና፣
የእማምዬን ቤት . . ድገምና አመት. . . ድገምና፣
ወርቅ ይፍሠስበት. . ድገምና አመት. . . ድገምና፣
እንዲህ  እንዳላችሁ አይለያችሁ፣
እንዲሁ እንዳለን አይለየን፡፡
አማኑኤል በቀኙ ያቁመን. . . .
የቅዱሳን መላዕክት . . . 
ፃድቃን ሠማዕታት. . . .
ረድዔት በረከት  . . . ይግባ በሁሉም ቤት. . . 
በሁሉም ቤት. . . በሁሉም ቤት
.ይግባ በረከት !፡፡
የዓመት ሠው ይበለን!!

የአምላካችን ቸርነት አይለየን፡፡



ምስጋና
·                ማህበረ ቅዱሳን  መካነ
·                መንግስተአብ አራንሺቸቨ

6 comments:

  1. Oh my I like it please keep it up God bless you

    ReplyDelete
  2. Berta! Betam arif aqerarebna yizet alew. gitimochume lijineten asitwosegn. Bizu yemitisera lij endahonk tasitawikaleh. Berta! Betam arif aqerarebna yizet alew. gitimochume lijineten asitwosegn. Bizu yemitisera lij endahonk tasitawikaleh.

    ReplyDelete
  3. Betam des yemel new yalwekuten endawek seladerek yebel yemyseg sera new letenshem seat behun Ageren asetawesekeg gerafu mulemulu hulunem dasehal bereta egziyabher ke anet gera yehun

    ReplyDelete
  4. wendeme egziabehere yestelign yagelgelot zemenehen yabzalih sew yalfal neger gin endezih yalu yebetekerestianachenen serat leteweled lemastelalef betshuf melk maskemet telek neger new

    ReplyDelete
  5. እግዚአብሔር ነብይ ያስነሳል ምክንያቱ ደሞ ብዙ ነው.
    1.መልክቱን ለሰው ለማስተላለፍ
    2.ሰውን በምሳሌ ለማስተማር
    3.ባህልና ቱፊቱን ለማውረስ

    ReplyDelete