ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Friday, November 11, 2011

ጉዞ ወደ ዝቋላ አቦ - ልዩ የጉዞ ማስታወሻ 1


ጉዞ ወደ ዝቋላ አቦ
ክፍል አንድ
   ከአስር ዓመት በፊት       
     የዩኒቨርስቲው ጊቢ በተማሪዎች ተሞልቷል፡፡ በሁሉም ተማሪዎች ላይ ፍርሃት፣ ውጥረት ይነበባል፡፡ ዕለቱ የአመቱ ልፋታቸውን ፍሬ የሚያዩበት ከመሆኑም በላይ ወደ ዩኒቨርስቲ ወይም ኮሌጅ መግቢያ ነጥብ ማግኘት አለማግኘታቸውን የሚያረጋግጡበት የመጨረሻው ሰዓት ላይ ናቸው፡፡ የተሳካላቸው የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ፊታቸው ብርሃን ሆኗል፤ ያልተሳካላቸውም ጥግ ስር ሆነው ግራ በተጋባ ስሜት፤ተስፋ በመቁረጥ ውዥብር ውስጥ  ሰምጠዋል፡፡ 

     “አንተማ ትሠቅለዋለህ ” አሉት ጓደኞቹ፡፡ በትምህርቱ ምን ያህል ጎበዝና ታታሪ መሆኑን ስለሚያውቁ፡፡ ልበ ሙሉ ቢሆንም “እግዚሐብኤር ያውቃል’’ ነበር መልሱ፡፡ የተፈራው ደረሰና ውጤቱን ተመለከተ፡፡ የዩኒቨርስቲ መግቢያ እንደተገመተው ሆነለት፡፡ ይገባካል. . . .፤ ትችላለህ ተባለ፤ደስታና ሳቅ ነገሰ ፈንጠዝያ ሆነ፤ ቤተሰብ፣ጓደኞች አካባቢው ሁሉም ደስ አላቸው፡፡ የልፋቱን ውጤት እንዳገኘ ወዳጅ ዘመድ ሁሉም መሰከሩለት፡፡ ይህ ሁላ ሆይ ሆይታና በርታ አይዞህ መባሉ ትልቅ ኃላፊነት እንደገና ሊጣልበት መሆኑን አላጣውም፡፡ ሁሉም አልፎ ክረምቱ ሲያልቅ አዲስ ዓመት ሲጣባ ወደ ተመደበበት ዩኒቨርስቲ ተቀላቀለ፡፡ እሱም የዋዛ አላነበረምና ወደኋላ አላለም ጠንክሮ መማሩንና ማጥናቱን ተያያዘው፡፡ የራሱን፣የቤተሰቡን፣የሀገሩን ህልምና ምኞት ሊያሳካ፡፡ አንድ ዓመት. . . ሁለት ዓመት. . . .ጊዜው እልም አለ፡፡ በዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ እንዴት ያለ ልጅ ነው፣በባህሪው፣በጉብዝናው. . . . . .ጥንካሬውን መሰከሩለት፡፡
መመረቂያው ጊዜው እየደረሰ ሲመጣ ወዳጅ ዘመድ ይህን ልጅ የበለጠ ሊያስደስቱት ሽር ጉዱ  በይፋ ተጀመረ፡፡. . . . .ሁለት ዓመት ከስምንት ወር ሆነው. . . .ጥቂት ወራት ቀሩ ሊመረቅ፡፡ በዚህ መሀል ግን ይህ ተስፋ የተጣለበት ልጅ ድንገት ደብዛው ጠፋ፡፡ ድንጋጤ ተፈጠረ፡፡ አብረውት የሚማሩት ተደናገጡ፡፡ ቢፈለግ ቢጠየቅ አየሁት የሚል ጠፋ ፤የገባበትም  ሊገኝ አልቻለም፡፡  ሁሉም ነገር ጨለመ፤ ያ የቤተሰብ ደስታና ፌሽወደ ሀዘን ተለወጠ . . . ይገኝበታል ተብሎ የሚታሰበበበተ ቦታ ሁሉ ታሰሰ ለሚመለከተውም አካል ተነገረ፡፡ አረ! ልጃችንን . . . . . ማን ያግኝላቸው. . . . ፍለጋው ቀጠለ. . .


ከዓመታት በኋላ ተስፋ በተቆረጠበት ሠዓት አንድ ወሬ ተገኘ. . . በድንገት. . . .
    
     የጉዞ ዝግጅት
              ሊነጋ ሲል ይጨልማል እንደሚባለው ለሊቱ እየተጋመሠ ቢመጣም ሊነጋልኝ አልቻለም፡፡ ታሪካዊውን ጉዞ ለማየት. . . “ ያን ዳገት!. . . ያን ዳገት ማን ይወጣዋል. . . . ” የተባለውን የዝቋላ ተራራ ማየት፣መድከም . . . ፈለኩ. . . ጓጓሁኝ፡፡ የማላውቀውም ተራራ፣ብዥ የሚል ተራራ በውስጤ እየሳልኩ መንጋቱን በጉጉት መጠበቅ ጀመርኩ፡፡ እንዴት ነው ሠዓቱ ወደኋላ ነው እንዴ የሚሄደው? ጭራሽ . . .  ሊነጋ ሲል ሠዓቱ ቆመ፡፡
ልክ ከጠዋቱ 12፡00 ሠዓት ላይ ሳልተኛ እንደተኛ ሰው ከአልጋዬ ወረድኩ፡፡ እንደው ለወጉ ያህል ሽርጉድ ማለት ጀመርኩ ምክንያቲም ጉዞውን የማደርገው ከታላቅ እህቴ ጋር ስለሆነና ሁሉም ነገር በላይና ከኔ በተሻለ መልኩ ጓዛችንን ስለምታዘጋጅ የእኔ ወከባ መፍጠር አስፈላጊ አልነበረም፡፡ ከዛ አርፌ ቁርሴን መመገብ ጀመርኩ፡፡ ደግነቱ የምንሄድበት አውቶቢስ በአቅራቢያችን ስለሆነ የሚጠብቀን እናረፍዳለን የሚል ስጋት አልነበረንም፡፡
ጉዞውን የጋበዘችኝ እህቴ ስትሆን እንደእኔ ሁለት የመስሪ
ቤት ጓደኞቿን ጋብዛቸው ነበር፡፡ ሁለቱም እንደእኔ አልነጋ ብሏቸው ነበር መሰል የአበሻ ቀጠሮን በሚያስንቅ መልኩ በሠዓታቸው ከተፍ አሉ፡፡ ቁርሳችንን ስለጉዞው እያወራን በደንብ በላን፡፡
“ያንን ተራራ ማን ይወጣዋል? ብሉ እንጂ” አለች እናቴ በእናትነት ፍቅር                                     
“አረ እንውጣ እየረፈደ እኮ ነው፡፡. . . . ” አልኩ የእናቴ የመልካም ጉዞ ምኞት ምርቃት አላልቅ ሲል፡፡ . . . . አሜን. . . አሜን. . . አሜን. . . .ይላሉ ሁሉም፡፡ አሜን አልኩ እኔም የእናቴ ምኞትና ምርቃት በሰላም እንዲመልሰን በመመኘት፡፡
“በሠላም የወሰዳችሁ አምላክ በሠላም ይመልሳችሁ፡፡ድንግል ማርያም ትጠብቃችሁ”  አሜ
 
የሸክፍነውን ቦርሳ፣ትንሽ ሻንጣ ለስላሳና ምግቦች ተሸክምን ቆሞ ወደሚጠብቀን አውቶቢስ ገባን፡፡ ጥቂት ተጓዦች ብቻ ነበር የቀደሙን፡፡ ቁጭ አልን ቦታችን ላይ፡፡ ወደ ዝቋላ ልሄድ እያልኩ ለውስጤ ነገርኩት፡፡ 
‘’እንዴ ሠዎቹ ምን ሆነዋል አይመጡም እንዴ?’’ አለ አንደኛው ተሳፋሪ ሰዓቱ እየገፋ ከሄደ ፀሐዩን እንደማንችለው በመግለፅ፡፡ ተራራ በፀሐይ. . . .  እንዴት ሊቻል ነው ብዬ እራሴን ጠየኩ፡፡ ወደ ዝቋላ አቦ ስሄድ ለመጀመሪያ ጊዜዬ በመሆኑ በጣም ጉጉት ብያለሁ፡፡
ጉዞው እስኪጀመር የሙዚቃ ማጫወቻዬን (ear phone) ሠክቼ ዜና ማዳመጥ ጀመርኩ፡፡ “የሊቢያው መሪ መሀመድ ጋዳፊ. . . .  .ተከበቡ. . . . የሊቢያን ህዝብ እንዲተባበር ጠየቁ ” ታዲያ እኔ ምን አገባኝ ብዬ ዘጋሁት፡፡ መዝሙር ከፈትኩኝ. . . እንደእድል ሆኖ
ስምሽን ለልጅ ልጅ እነግራለሁ፤
እናቴ በምልጃሽ ሰው ሆኛለሁ፤
እመቤቴ ስልሽ ነይልኝ  . . . . . .
” የምርትነሽ መዝሙር ተከፈተ፡፡ ቅልል አለኝ፡፡
ሁሉም ተጓዦች መሙላታቸው ሲረጋገጥ ለፀሎት ተነሱ ተባለ፡፡ ብድግ ብድግ. . . . ፀሎታችንን በህብረት አደረስን፡፡ ፈጣሪያችን ጉዟችንን ባርክልን. . .በሠላም መልሰን. . . . .
“አባታችን ሆይ፣
በሠማያት የምትኖር፤
ስምህ ይቀደስ፣መንግስትህ ትምፃ፣
ፍቃድህ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁም በምድር ትሁን . . . .

.
.
.  
.
አሜን

ሁላችንም በስመስላሴ አማትበን አረፍ አረፍ በሉ ሲባል ቁጭ አልን፡፡ እኔም ተመቻችቼ ተቀመጥኩ፡፡

የመጀመሪያው ክፍል ጉዞ ሊጀመር ነው. . .
ይቀጥላል ...




7 comments:

  1. you are taking me back to Zekual Abo. you have good naration skill Besrie. i was expecting your post and also the rest of the travilings specialy the felling after the completion of the mountain and getting to the door of the Church. it feels heavenly; kidus Dawit EGZIABHERN ANDIT NEGETR LEMENKUT ESUAM, BEBET ETAL ZEND YALEW KAL.

    ReplyDelete
  2. Melkam tireka new
    Ebakih ketayun kifl lemanbeb betam chekuyalehu Yaguagual.

    Egziabhere yistilign

    ReplyDelete
  3. ክፍል ሁለት የት አለ?

    ReplyDelete
  4. Gosh endih yale tireka betam tiru new. ebakih ketayun aftinew

    ReplyDelete
  5. Where is the second part .Good job.....

    ReplyDelete
  6. WHERE IS PART 2.3,,,,,

    ReplyDelete