ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Thursday, October 1, 2015

ይድረስ ለ ‹‹ ባላገሩ ምርጥ ››

   
የባላገሩ ምርጥ ውድድር ከተጀመረ ከዓመታት  ቆይታ በኋላ መስከረም 17 , 2008 በመስቀል በዓል ዕለት መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡ የውድድሩ መርዘምና አላልቅ ማለት የሆነ ወቅት ላይ አጀብ አሰኝቶ የነበረ ቢሆንም ወደ ማለቂያው አካባቢ ግን የብዙዎችን ቀልብ መሳብ ችሎ ነበር ፡፡ በተለይ የመጨረሻዎቹ 25 ተወዳዳሪዎች ሲቀሩ ብዙ ደስ የሚሉ ነገሮችን ማየት ችለናል፡፡  እኔም ባገኘሁት  አጋጣሚ ማየት  የጀመርኩት በዚህ ወቅት ነበር ፡፡
     'ባላገሩ ምርጥ' በሀገራችን ቀደም ብለው ከታዩ እና አሁንም እየታዩ ከሚገኙ የድምፅና የዳንስ ውድድሮች በብዙ ነገሩ የተሻለ ሲሆን ለንፅፅርም የማይበቃ በከፍተኛ በጀት የሚሰራ መሆኑ ያስታውቃል፡፡ በዚህም ምክንያት ስነውበቱን እና ኪነጥበባዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ለዓመታት መዝለቅ  ችሏል፡፡ ቢሆንም ምንያህል ልፋት እንደሚጠይቅ እንዲሁም ምን ያህል ሊያደክም እንደሚችል ማሰብ ቀላል ነው፡፡ እጅግ ብዙ  እየተለፋበት እንደሚሰራ እና አዘጋጆቹም ጠንካሮች እንደሆኑ መገንዘብ  ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ጊዜያቶች በሄዱ ቁጥር የውድድሩ ጥራት እየጨመረ እየጨመረ መሄድ መቻሉን  የሚነግረን ነገር ስላለ፡፡  አንዳንድ ጊዜ በተወሰነ መልኩ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የባለሙያ እጥረቶች እንዳሉ ቢታይም ሁልጊዜም መሻሻሎች ነበሩት፡፡ ይህም ባላገሩ ምርጥን ምርጥ ያሰኘዋል፡፡

 ኢትዮጵያዊነትን መውደድ

            ባላገሩ ምርጥን እንድመለከት ካደረጉኝ ጉዳዮች ዋነኛው ኢትዮጵያዊነት ላይ ስለሚያተኩር እና ስለሚያውጠነጥን ነው፡፡
እስከመጨረሻ ይህን ዓላማ ይዞ መዝለቅ መቻሉ ደግሞ አስደሳች ነበር ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ትልልቅ ሃሳቦችን አንግበው በቅርብ ቀን ጠብቁን ብለው ደስኩረው ትዕይንቱ ወይም ፕሮግራሙ ሲጀመር ደግሞ ምንም ዓይነት ሀገራዊ ለዛ እና ሀገራዊ ጥፍጥና የሌለው አቀራረቡም ፣ ይዘታቸውም ባህር ማዶ ናፋቂነትን ሰባኪ ሆኖ የሚቀርቡ የቴሌቪዥን 'ፕሮግራሞች በሞሉባት ሀገርእንደ ባላገሩ አይነትን ማበረታታት ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

       ባላገሩ ምርጥ ሲጀምርም ባላገሩ  'አይዶል (idol)' ብሎ ነበር፡፡ በወቅቱ አይዶል (idol)'የሚለውን ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ቃል እንዴት ‹‹ ባላገሩ ›› ከሚለው ውብ ሀገርኛ ቃል ጋር እንዴት ሊዛመድ ይችላል ብዬ ጠይቄ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ዘግይቶም ቢሆን ግን ለማስተካከል ሞክረዋል፡፡ከ ‹‹ባላገሩ አይዶል›› ወደ ‹‹ባላገሩ ምርጥ ››፡፡ በዛ ላይ ‹ አይዶል› የሚለውን ቃል ‹ ምርጥ › ወደሚል ቃል ለመለወጥእና ለመቀየር የተጠቀሙበት ዘዴ ብልሃትን ከብልጠት ጋር አዋህዶ  ውበት በታከለበት መልኩ ነበር፡፡ይህም ለዓመታት በተመልካች አዕምሮ ውስጥ ተቀምጦ የነበረውን 'አይዶል(idol) የሚለውን ቃል በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማስረሳት አስችሏል፡፡ ይሄ ዘዴም ጥበብ በተገቢው መንገድ ሲቀርብ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል እንደማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡እንደ ቀደመው ልማድ ድንገት ከመሬት ተነስቶ በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን ስማችንን ቀይረናል ተብሎ ቢነገር ኖሮ ይህን ያህል ተቀባይነት ማግኘት በከበደ ነበር፡፡ ለዚህ የበሰለ አካሄድና የአስተሳስብ ለውጣችሁ አጨብጭቤያለሁ፡፡

በተጨማሪ ባላገሩ ምርጥን ምርጥ የሚያሰኘው ዋነኛው ነጥብ ኢትዮጵያዊነትን ለማንፀባረቅ መሞከሩ ነው፡፡ እያንዳንዱ የሚጠቀሟቸውን ነገሮች የሚገልፁት በኢትዮጵያውያን መገለጫዎች ነበሩ፡፡ ዋሽንቱ፣ አካፋው፣ አልባሳቱ እንዲሁም ለውድድሩ ድጋፍ ሠጪ ለሆኑት አካላት የሚሰሩ የንግድ ማስታወቂያዎች በሙሉ ኢትዮጵያዊነት የሚናገሩ ፣ አኗኗራችን የሚያሳዩ፣ አለባበሳችንን ፣ ጀግንነታችንን የሚያጎሉ ሲሆኑ ከሁሉ በላይ እያንዳንዱ ስራ ከውድድሩ ፅንሰ-ሃሳብ ጋር አብሮ የሚሄድ፣ የማዝናናት አቅማቸው ከፍ ያለ እንዲሆኑ ተደርገው የተሰሩ ናቸው፡፡ እንደዚህ አይነት ዘዴዎች ደግሞ የማንነት ቀውስ አባዜ ለጠለፋት ፣ ህዝቦቿም ኢትዮጵያዊነት መኩሪያ ሳይሆን መታፈሪያ እየሆነባት ላለች ሀገር ጠቀሜታው ትልቅ ነው፡፡ ሀገርን፣ ባህል ስርዓትን፣ መከባበር መዋደድን፣ ቅርስና ታሪክን እንዲሁም ሃይማኖታዊ አንድምታዎቻችንን ጠብቆ ይዞ ለመሄድ ይህን መሰል አቀራረቦች በጣም ያስፈልጋሉ፡፡

ሌላው ደሞዛቸውን ባላውቅም የውድድሩ አዘጋጆችም የዚህ ዓላማደጋፊዎች መሆናቸው አንዱ መልካም ጎኑ ነው፡፡ በተለይ ዋና አዘጋጁ አብረሃም ወልዴ ለኢትዮጵያዊነቱ የሚሰጠው ቦታና ክብር ያለው ቀናይነት በጣም ደስ ይላል፡፡ ይህን አስተሳሰቡንና ስሜቱን ተጋርተው ለዚህ ዓላማ ይጠቅሙኛል ይበጁኛል ብሎ የመረጣቸውን ባለሙያዎች ብዙ እንደደከመባቸው እና ፕሮግራሙ የተሸከመውን ትልቅ ሀገራዊ ተልዕኮ ተረድተው የተረዱትንም ወደራሳቸው አምጥተው ወደ ተግባር እንዲቀይሩ የማድረጉ ነገር ከባድ እንደሆነበት አስባለሁ፡፡ ያም ቢሆን ግን በተወሰነ መልኩ የተሳካለትም ይመስለኛል፡፡
ወደፊትም የአብርሃም ችግርና ፈተና ብዬ የማስበው ሙያቸውን አክብረው በሙያቸው ብቁ የሆኑትን ባለሙያዎች ማግኘቱ ላይ ነው፡፡ምክንያቱም ሀገራችን ውስጥ ያሉ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ከስራቸው ውጪ ተናግሮ የማሳመን እንዲሁም ራሳቸውን በማንበብ ከጊዜው ጋር የለማራመድ የሚጥሩ ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ ለምሳሌ በውድድሩ ላይ የሚገኙት የዳንስም ሆነ የድምፅም ዳኞች ከቀደመ ስብዕናቸው እና ከቀደመ ስራቸው በተለየ በዚህ የማወዳደር እና የመዳኘት ስራቸው ጠንካራ ፈተና የገጠማቸው መሆኑን ማወቅ አይከብድም፡፡ እነሱ ቀለል ለማድረግ ቢፈልጉ እንኳን ዋና አዘጋጁ እንዲህ በቀላሉ የሚተዋቸው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ውድድሩን እና የውድድሩን አቀራረብ ከዚህ ቀደም ከታዩት እጅጉን የተሻለና የበለጠ ለማድረግ እንደሚፈልግ በግልፅ ስለሚታይ፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ካስፈለገ ስንት ዳኞች በውድድሩ እንደተለዋወጡ ማሰብ ቀላል ነው፡፡ ተቀይረው የመጡትስ ምን ዓይነት ናቸው ብለን ስናይ የአብርሃምን ድካም እንረዳለን፡፡ እነ ጋሽ አበራ ሞላ ፣ እነ ዳግማዊ አሊ የመሳሰሉት ጎበዝ ዳኞች እንደነበሩና ኢትዮጵያዊነትን ቅድሚያ የሚሰጡ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ከዛስ?  የተቀየሩት ዳኞች የቀድሞዎቹን ይመጥናሉ? እዚህ ላይ የተወሰነ ክፍተት እንዳለው ይሰማኛል፡፡ አሁን ካሉት ዳኞችም ባላገሩ ምርጥን የማይመጥኑ እንዳሉበት ይሰማኛል፡፡ በተለይ በዳንስና በውዝዋዜ ላይ፡፡ ትንሽ መውደድ ክብሩ ሲጨመር ተሽሎኛል፡፡ እነ እንዬም ወንበሩ ላይ ሲቀመጡ ምን ያህል የተወዳዳሩዎቹ ደስታ እንደጨመረ ማስተዋል ችያለሁ፤ የውድድሩም ግርማ ሞገስ ከፍ አድርጎታል፡፡ ተጋባዥ የድምፅ ዳኞቹም በተለይ ፒያኒስቱ ይፍራሸዋ ምን ያህል የበሰሉ እንደነበረ በደንብ ታይቷል፡፡ ቢቻል እነዚሁኑ ባለሙያዎች ይዞ መቀጠል የሚቻልበት መንገድ ቢመቻች ጥሩ ነው፡፡  እዚህ ላይ ብዙ ችግር ሊኖር ይችላል፤ የሙያተኛ እጥረትና ተባብሮ የመስራት ችግርም አብሮ እንዳለ ነው፡፡በሙያው ብቁ የሆኑትም እራሳቸውን ገለል አድርገው በሩቁ እንደሚኖሩም አውቃለሁ፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ሀገሩቷ ያፈራቻቸውን ባለሙያዎችን ለመጠቀም እየተሞከረ እንዳለ ይሰማኛል፡፡ ይህን ሃሳቤን የሚያጠናክርልኝ አብርሃም ትልልቅ የሚባሉ ባለሙያዎችን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይጋብዝ ነበር፡፡ በየክልሉ ያሉትን ተወዳዳሪዎች በራሳቸው ሀገር ተወላጆች እንዲዳኙ ለማድረግ ሲጥር ተመልክቻለሁ፡፡ ይህ ደግሞ ይበልጥ ለተወዳዳሪዎቹም ሆነ ለተመልካቾች አሰልቺ እንዳይሆን እንዳደረገው ይሰማኛል፡
፡ የዳኞቹ የዕድሜ ስብጥርም ሌላው የውድድሩ ማጣፈጫ ነበር፡፡


በዚህ መልክ የቀጠለው ውድድር በመጨረሻው ቀን ላይ ምን ተፈጠረ . . . ?

የውድድሩ ፍፃሜ

       የውድድሩ ፍፃሜ ስገመግመው መልካም የሚባሉ ነገሮች የበዙትን ያህል የዛኑ ያህል ደግሞ ስህተቶች የነበሩት ነበር፡፡ የአብርሃም ልፋት ብዙ ከመሆኑ የተነሳ እሱ እራሱ በፍፃሜው ዝግጅት እንዳልተደሰተ ያስታውቅ ነበር፡፡ ይህ ክፍተትም የተፈጠረው አብርሃም ህክምና ላይ በነበረ ሰዓት መሆኑ ይበልጥ ያበሳጫል፡፡ የልፋቱም ውጤት ሙሉ እንዳይሆን አድርጎበታል፡፡ እስቲ እኔ የታዘብኩትን ችግሮች ልዘርዝር፡-

1ኛ.  የቅንጅትችግር

       መድረክ መሪዋ ትዕግስት እራሷን ፈፅሞ ማረጋጋት ተስኗት ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር የተፈራረመቸው እሷ ነበር የምትመስለው፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ማመን ከባድ ሊሆን ቢችልም የአብርሃም በተደጋጋሚ እሷን ሊያቋርጣት መሞከሩ ግን ማነው የፕሮግራሙ መሪ አዛዥ ያስብላል፡፡ እሷ ጊዜ የለም ትላለች አብርሃም ደግሞ የአመታት ድካሙ ውጤቶች የሆኑትን ልጆች መድረክ ላይ መውጣት አለባቸው ይል ነበር፡፡  በግሌ በአብርሃም ሃሳብ እስማማሉ፡፡ ምክንያቱም ለውድድሩም ድምቀት፣ ለተወዳዳሪዎቹም ክብር፣ ለውድድሩም ፍፃሜ ማማር የሚበጀው ሁሉንም መድረክ ላይ ማየት ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ በየትኛውም ዓለም የሚደረግ የስነስርዓት አካሄድ ነው፡፡ እዚህ ላይ ከቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር የተደረገው የሰዓት ርዝማኔ ስምምነት ይጣስ እያልኩኝ ባይሆንም ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለተወዳዳሪዎቹ ልፋትና ድካም እንዲሁም ክብር ነው፡፡
ሰዓት የለንም እያለች አስሬ ከመረበሽ ቀደም ተብሎ ስራ ቢሰራ በቂ ሰዓት እንዲኖር ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ግን የቅንጅት ስራ አልነበረም፡፡ ጊዜ አጠቃቀም ላይ ደካማ ነበሩ፡፡ ዳኞች ማውራት አልቻሉም ነበር፡፡ ጭራሽ ሴቷ ተወዳዳሪ እየዘፈነች በመሀል ይቅርታ አቁሚ ተብላ ከስሜትም ከነበረችበት ተመስጥዖ ተረብሻ እንደገና እንድትጀምር ተደርጋለች፡፡ይሄ አሳፋሪ ድርጊት ነበር፡፡ መድረክ መሪዋ ሬድዮ ላይ የምታወያይ መስሏትይሆን ? ድፍረቷና ችኩልነቷ የብዙዎችን ቆሽት ያሳረረ እና የውድድሩን ክብር የማይመጥን ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ ዓመቱን ሙሉ አስተያየታቸው ሲሰማ ምስላቸው ተደጋግሞ ሲታይ የነበሩ ዳኞች የድካማቸው ውጤት እንዴት እያጣጣሙ እንዳለ ማየት አልቻልም፡፡ ምን እየሰሩ እንዳሉ፣ አስተያየታቸውን መስማት፣ ስሜታቸውን መመልከት አልተቻለም፡፡ እንዲሁም የተወዳዳሪዎቹን ደስታና ሀዘን መመልከት አልቻልንም፡፡ ይልቅ ሰዓት ቁጠባ ተብሎ ከመድረኩ ቶሎ እንዲወርዱ ነበር ሲነገራቸው የነበረው፡፡ ውድድሩ የማን ነበር? የልጆቹ አልነበረምን ? ሊገባኝ አልቻለም፡፡
ይህን ሁሉ የሚያስብለኝ በቀደመው በውድድር ጊዜያች አብርሃም ለተወዳዳሪዎቹ እና ለውድድሩ ትልቅ አክብሮት ነበረው፡፡ በተጨማሪም ይህ ነው የሚባል የጎላ ስህተት ላለመስራት ሲጥር ስለነበርነው፡፡ የውድድሩም ደረጃ ከፍ እንዳለ ለመፈፀም የነበረውን ጥንቃቄ ስለማስብ ነው፡፡ ግን በመድረክ መሪዋ ረባሽነት እና በቅንጅት ማነስ እንደታሰበው ሳይሆን ቀረ፡፡

 2ኛ. የመብራት እና የቀረፃ ችግር

       የተወዳዳሪዎቹን ስም ባላውቅም በዘመናዊ የዳንስ ውድድር ላይ ለነበሩት ልጆች በጣም የሚያናድድ ቀን እንደነበረ አስባለሁ፡፡ ሙሉ ስራቸው ከመብራት መጥፋትና ጭለማ መሆን ጋር የነበረ ቢሆንም የመብራት መጥፋትና መብራቱ እንደፈለጉት አለመሆን ድካማቸውን ዋጋ እንዳይኖረው አድርጎታል፡፡ አብርሃምም ይህን ተረድቶ ይመስለኛል ይቅርታ ሊጠይቅ የሞከረው፡፡ የሱ አለመኖር ልጆቹን ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ ቅሬታቸውንም እንደሚክስላቸው አስባለሁ፡፡ የነበራቸውን ተነሳሽነትና ፍላጎት ማሳየት የሚፈልጉትን ማሳየት ባለመቻላቸው እንደሚከፉ ግልፅ ነው፡፡ ትልቁ ነገር የአብርሃም ለተወዳዳሪዎቹ የሚሰጠው ክብር እንዲሁም ተወዳዳሪዎቹን የያዘበት መንገድ ይቅር ያስብለው ይሆናል፡፡ ሌላው ቀረፃው ከዚህ ቀደም በተለይ በብሔራዊ ቲያትር የነበረውን ዓይነት መሆን አልቻለም፡፡ ከቀድሞዎቹ ቀረፃዎች ጋር ሲነፃፀር ደካማ ነበር፡፡ ይሄ ይሄ ብል አንባቢን ግራ ማጋባት ሊሆን ስለሚችል ልዝለለው፡፡ የካሜራ እና የዳይሬክቲንግ ባለሙያዎች ግን ይህን ሃሳቤን የምትጋሩኝ ይመስለኛል፡፡

3ኛ.  የድምፅ አሠጣጥ

      አብርሃም በጣም ተሸወደ የምለው በዚህ ብቻ ነው፡፡ 60% የህዝብ ድምፅ 40% የዳኞች ብሎ መጀመሪያ በመናገሩ ተወዳዳሪዎች ላይ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ እዚህ ላይ አብርሃምን የምረዳበት ነጥብ አለ፣ በህዝብ የተመረጠ ተወዳዳሪ መፍጠር ነበር ፍላጎቱ፡፡ ይህ ደግሞ ከአንድ ኃላፊነት ከሚሰማው ህዝብን አክባሪ ከሆነ የጥበብ ሰው የሚጠበቅ ነው፡፡ነገር ግን አብሮ ተያይዞ የሚመጣው ችግር የተጠና አልመሰለኝም፡፡ በተጨማሪ የህዝብ ምርጫ ተብሎ ውጤቱ በቴሌቪዥንም ይታይ ስለነበር ለተወዳዳሪዎችና ለደጋፊዎቻቸው ተስፋ አስቆራጭ ነበር፡፡ በተለይ የአሸናፊው የዳዊት ድምፅ ከሌሎቹ ተወዳዳሪዎች ጋር የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት ነበረው፡፡ ይሄ ደግሞ የተወዳዳሪዎቹን ሞራል ያደከመው ይመስለኛል፡፡ ይህን በመገንዘብ መሰለኝ ከህዝብ ድምፅ ይልቅ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የዳኞችድምፅ መሆኑን ውድድሩ ከተጀመረ በኋላ ለማስተካከል የተሞከረው፡፡ ውሳኔው ጥሩ የነበረ ቢሆንም በጣም ዘግይቶ ነበር፡፡
ቅሬታዬ ግን መጀመሪያም ህዝብ መምረጥ አለበት ተብሎ ሲወሰን ለምን ጥንቃቄ ማድረግ አልተቻለም ነው፡፡ በግሌ የህዝቡ ድምፅ 60% ሳይሆን 10% ወይም 15% ብቻ ቢሆን በቂ ይሆናል ብዬ አስባለሁ ፡፡ ምክንያቱም አንደኛ የተወዳዳሪዎቹ የምረጡኝ ዘመቻ አለመመጣጠን ነበረበት፡፡ ለምሳሌ ዓይነስውሩ ባልከው እና አሸናፊው ዳዊት ህዝብን ምረጡኝ ብሎ ለመቀሰቀስ እኩል አቅም ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ሴቶቹም ቢሆኑ ከወንዶቹ እኩል ይሆናሉ ብሎ መገመት የዋህነት ነው፡፡ ምክንያቱም ይሄ ኢትዮጵያ እንጂ አሜሪካ ወይ አውሮፓ ስላልሆነ፡፡ በተጨማሪም የህዝቡ ንቃተ-ህሊና በራሱ ገና የሚቀረው ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ህዝብን መናቅም ሊሆን አይችልም፤ እውነታን መጋፈጥ ስላለብን ነው፡፡

                        *******                     *******

       በመጨረሻ የባላገሩ ምርጥ እስከዛሬ በኢትዮጵያ ከተካሄዱት ውድድሮች በጣም የተሻለና የብዙ ባለሙያዎች ድካምና ልፋት የነበረበት ነው፡፡ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ አይዶል በነበረበት ጊዜ የውድድሩ ሀሳብ አመንጪ እኔ ነበርኩ ዓይነት ክርክሮች በአብርሃም እና በጀማል መሀከል እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ ይህም አሁን ላይ ለአብርሃም ጥንካሬ እና የተሻለ ነገር የመስራት አቅም እንደሰጠው እገምታለሁ፡፡  በቀጣይ ዓመታትም ከቀደመው ስህተቶች በመማር የተሻለ እና ተመራጭ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ በሙያቸው አንቱ የተባሉን በማካተት ጥሩ ጥሩ ባላገሮችን ማፍራት ይቻላል፡፡ በተረፈ ለዋና አዘጋጁ አብርሃም ወልዴ ያለኝን እክብሮት መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ ጤንነቱ ወደቀድሞ ተመልሶ ያሰበውን ያሳካ ዘንድ ልባዊ ምኞቴ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡








No comments:

Post a Comment