ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Saturday, April 27, 2013

ፋሲካ፦ “ሥጋዊ ወመንፈሳዊ”


ፀሐፊ፡ ኤፍሬም እሸቴ  
  

(ኤፍሬም እሸቴ - ኢትዮጵያዊ)

         በኢትዮጵያውያን ዘንድ በታላቅ ሁኔታ ከሚከበሩት በዓላት መካከል ትንሣኤ ወይም ፋሲካ አንዱና ዋነኛው ነው። ሃይማኖታዊ ትርጓሜው እና ምንነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ባህላዊ አከባበሩ እና ምንነቱም ከኢትዮጵያውያን ባህላዊ ማንነት ጋር በጥልቅ የተያያዘ ነው። እንኳን በአገር ቤት ያለው በሰው አገር ያለነውም እንኳን ብንሆን እንደ አቅሚቲ የአገር ቤቱን መንፈስ በያዘ ሁኔታ እናከብራለን። ስለዚህ ፋሲካው መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን ሥጋዊ/ ባህላዊ አንድምታው ከፍ ያለ ነው ማለት ነው።
አለቃ ዘነብ የተባለው የአጼ ቴዎድሮስ ታሪክ ፀሐፊ አንባቢውን እያዋዛ የመከረበትንመጽሐፈ ጨዋታየተሰኘውን መጽሐፉንሥጋዊ ወመንፈሳዊ” (ሥጋዊ እና መንፈሳዊ) እንዳለው ስለ ፋሲካ ያለችኝን ወግ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ ብዬ ብከፍላት ኋላ ለሚከተለው ሐሳብ ጥሩ ገላጭ ይሆናል። ዘነብ ኢትዮጵያዊ ሲል ራሱን እንደገለጸ ኩረጃዬን ሙሉ ለማድረግ ኤፍሬም ኢትዮጵያዊ ብያለሁ፣ ቢያንስ ለዚህ ጽሑፍ። ኢትዮጵያዊነታችንን ከፍ አድርገን በክብር ልናሳይ የሚገባበት ዘመንም ስለሆነ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይሆንልኛል።
በጥንተ ታሪኩ ፋሲካ የሚጀምረው ከእስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነጻ የመውጣት ታሪክ ታሪክ ጋር ተያይዞ ነው። ሕዝበ እስራኤል ለረዥም ዘመን በግብጽ አገር በባርነት ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ በቤተ መንግሥቱ ያደገው ሙሴ መሪ ሆኗቸው ወደ አገራቸው ለመመለስ የጀመሩትን ጉዞ መሠረት ያደረገ በዓል ነው። ግብጻዊው ገዢ የሚያየውን ተአምራት ተቀብሎ ሕዝቡን ሊለቅ እና ነጻነታቸውን ሊመልስላቸው ባለመፍቀዱ ከተከሰተው ከባዱ ቅጣት ማለትም የግብጻውያኑ የበኩር ልጆች መቅሰፍታዊ ሞት ጋር ይገናኛል።

ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ሞተ በኩር በመጣ ጊዜ ቀሳፊው መልአክ እስራኤላውያን ልጆችን እንዳይቀስፍ እነዚህ ተገዢዎች በየበሮቻቸው መቃን ላይ የበግ ደም ቀብተው፣ መልአከ ሞትም ደሙ የተቀባበትን በር በማለፉና ግብጻውያንን  በመምታቱ በዓሉም ከማለፍ ጋር ተገናኘ እና ማለፍን፣ መሻገርንና መሸጋገርን የተመለከተ ሊሆን ቻለ። በዕብራይስጡፓሳህማለት ማለፍ ማለት ነውና። ሁለተኛው ማለትም የክርስቲያኖች ፋሲካ ወይንም ትንሣኤ ደግሞ ክርስቶስ እውነተኛው በግና መስዋዕት ሆኖ ሰዎችን ከጥፋት ወደ ድኅነት ያሻገረበትን ይመለከታል። ለምን ፋሲካሥጋዊ ወመንፈሳዊእንዳልኩት ለመረዳት የቀድሞውን የእስራኤል ፋሲካ ከኋላው ከክርስቲያኖች ፋሲካ ጋር ማነጻጸር ነው።
በቀድሞው በእስራኤል ፋሲካም ሆነ በኋለኛው የክርስቲያኖች ፋሲካ፣ፋሲካአማናዊ ትርጉሙ ከባርነት ነጻ ከመውጣት (ከነጻነት) ጋር የተገናኘ ነው። ይህ ከሆነ ታዲያ ነጻነት ያላት ሥፍራ ምን ያህል ክቡር መሆኑን ያስረዳናል። እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት፣ ከምድራዊ ገዢዎች አስከፊ ተገዢነት ነጻ እንደወጡት ሁሉ በክርስትናው ደግሞ ክርስቶስ የፋሲካው አማናዊ በግ ሆኖ በመሰዋቱ የሰው ልጆች ከሰይጣን ባርነት ነጻ እንደ ወጡ ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች። ባርነት፦ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ።
ከፍ ብዬ በጠቀስዃቸው ታሪኮች ቅደም ተከተል ከሄድን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ከሰይጣን ባርነት ነጻ ከማውጣቱ በፊት የሚቀድመው የሕዝበ እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነጻ መውጣት ነው። ከነፍስ ነጻ መውጣት የሥጋ ነጻ መውጣት ቀድሟል ማለት ነው። ነገር ግን የእስራኤልንም ነጻነት ቢሆን ጠልቀን ብንመለከተው ከምድራዊ ገዢዎቻቸው ነጻ ከመውጣታቸው አስቀድሞ የነፍስ ነጻነት ማለትም የኅሊና ነጻነት ማግኘታቸውን እንረዳለን፤ ነጻነታቸውን በተግባር ከማግኘታቸው አስቀድሞ ራሳቸው ለራሳቸው ነጻነትን ሰጥተዋል። ይህንን ነው የኅሊና ነጻነት ያልኩት።
ማንኛውም ሰው ነጻነትን ከማግኘቱ አስቀድሞ ነጻነት እንደሚያስፈልገው ማወቅ፣ ማመን እና ከማንም ሰጪ ወገን እንዲቸረው ሳይጠብቅ ነጻነትን ለራሱ በራሱ መስጠት/ ማጎናጸፍ እንዳለበት ይሰማኛል። ለራሱ ነጻነት ያልሰጠ ሰው ሰዎች ቢሰጡትም ለመቀበል አይችልም። ማንነቱ ነጻነትን ለማስተናገድ ይሳነዋል። ነገር ግን ነጻነትን ለራሱ የሰጠ ሰው ሰዎችነጻነትህን ወስደንብሃልቢሉት እንኳን ነጻነትን ለራሱ ሊከለክልና ባሪያ ሊሆን አይቻለውም። አንድ ምሳሌ ልጥቀስ።
ሰውየው ለረዥም ዘመን በእስር ቤት የኖረ ነው አሉ። የዕድሜውን ግማሽ በላይ ያህል በእስር ቤት በመኖሩ እያንዳንዱ ርምጃው በእስር ቤቱ ኃላፊዎች ፕሮግራም ሲቀረጽለት የኖረ። የሚበላበት፣ የሚጠጣበት፣ የሚተኛበት፣ ሰውነቱን የሚታጠብበት፣ ሥራ የሚሔድበትና የሚመለስበት ጊዜ የተሰፈረና የተቆጠረ። ለእርሱ የምግብም ሆነ የመኝታ ሰዓት የሚወስኑት ሌሎች ሰዎች/ እስር ቤቱ ጠባቂዎች ናቸው። ይህንን ኑሮ ለረዥም ዘመን የተለማመደ ሰው አንድ ቀንነጻ ነህ፤ ወደ ቤትህ ሒድተባለና ከወኅኒው ተለቀቀ።
ነገር ግን ሰውየው እስረኝነትን እንጂ ነጻነትን፣ በሰው ሰዓት መኖርን እንጂ በራሱ ሰዓት መሔድን አልለመደምና ነጻነቱ ባርነት ሆነበት። እስር ቤቱን ናፈቀ። የዕለት ኑሮውን ለማሸነፍ የተቀጠረበት ቦታ ያሉ አለቆቹን ሽንት ቤት ለመሔድ ያስፈቅድ ጀመር። ጥያቄው ግር የሚላቸው አለቆቹታዲያ ሽንት ቤት ብትሔድ ባትሔድ እኛ ምን ቸገረን? ከገለግኽ ሒድ፣ ካልፈለግህ ቅርይሉታል። እርሱ ግን ሳያስፈቅዱ፣ ሌሎች ቡራኬ ሳይቸሩት የሚደረግ ኑሮን አያውቀው ኖሮ ነጻነት ከመርግ ከበደው። ባርነትን የተሸከመ ጫንቃው ነጻነትን ለመኖር ከበደው። (በግብጽ የባርነት ኑሮ መኖርን እንጂ ከፈርኦኖች አገዛዝ ውጪ ያለች አገር አልታይህ አለው።) ለካስ ሥጋው ነጻ ይሁን እንጂ ኅሊናውና ነፍሱ ገና እስረኞች ናቸው። የነፍስ ነጻነት ሳይኖር የሥጋ ነጻነት አይኖርም ያልኩትን ለማስረገጥ ፈልጌ ነው።
የቀደመውን ፋሲካ ያከበሩት ሕዝበ እስራኤል በሙሴ መሪነት ከግብጽ ባርነት እንዲወጡ ብዙ ተአምራት ቢደረግላቸውም አዲሱን ነጻነት ለመቀበል ግን ሁሉም ዝግጁዎች አልነበሩም - ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን። የነጻነታቸውን ፈር ቀዳጅ ሙሴን አንዴም ሲቀበሉት ሌላም ጊዜ ሲያሙት፣ አንዴ ሲያጸድቁት ሌላ ጊዜም ሲያዋርዱት ሲወጡ ሲወርዱ እንመለከታለን። በነጻነት ከሚያገኙት መና ይልቅ በባርነት የሚሰጣቸውን የግብጽ ምግብ (ቅዱስ መጽሐፍ ዓሣ፥ ዱባ፥ በጢኽ፥ ኩራት፥ ቀይ ሽንኩርት፥ ነጭ ሽንኩርት” ይለዋል) ይናፍቁ ነበር (ኦሪት ዘኍልቍ 115) ችግሩ ግን ነጻነትን ያለማወቅ ዕዳ ነው።
በታሪኩ ቅደም ተከተል መሠረት ከሔድን እስራኤል 430 ዘመን በግብጽ ኖረዋል። ነጻነቱ በታወጀበት ወቅት የነበሩት በሙሉ በባርነት አገዛዝ ሥር የተወለዱ ናቸው ማለት ነው። የሚያውቁት ባርነትን እንጂ ነጻነትን አይደለም። ሙሴ ከእስራኤላውያን የተወለደ ነገር ግን በጉዲፈቻ በፈርዖኖቹ ቤት መስፍን ሆኖ ያደገ ነጻነትን ያወቀ ሰው በመሆኑ የወገኖቹ ባርነት በቅጡ ይቆጨው ነበር። ኅሊናውና ነፍሱ  ነጻ ነበሩ።
ሌላው እስራኤላዊ ግን የዚህ ተቃራኒ ነበር።የማያውቁት አገር አይናፍቅምእንዲባል ነጻነትን የማያውቅ ሰው ባርነቱ ለምን እንዳልከበደው መጠየቅኤሊ በላይዋ ያለው ድንጋይ እንዴት አይከብዳትም?” እንደማለት ነው። የማያውቀው ነጻነት በየት በኩል ይናፍቀዋል? በሚያየው በዚያው ተወስኖ ከመ-እንስሳ ይኖራል፤ የዕለት ጉርሱን የዓመት ልብሱን ብቻ እያሰበ። ሙሴ ግን ከፈርዖኖቹ ቤተ መንግሥት ይልቅ ከወገኖቹ ጋር ያለውን መረጠ፣ ነጻነቱን ብቻውን ላለመኖር፣ የነጻነትን አየር ብቻውን ላለመተንፈስ የድሎት ሕይወቱን ለወገኖቹ ነጻነት ለመለወጥ እና የፋሲካው ምክንያት ለመሆን አላንገራገረም። የነጻነትን ጣዕም ለማካፈል ጓጉቷልና።
የሰው ልጅ ትልቁ ሀብቱ ነጻነቱ ነው። የማንም እጅ እየገባ የማይበጠብጠው ድንበሩ ነጻነቱ ነው። ነጻነቱ የተገፈፈ ሰው ምን ሀብት ቢኖረው ሰብዓዊ ማንነቱ ጎዶሎ ነው። ኅሊናውና ነፍሱ በማይታይ ሰንሰለት እግር ተወርች ታስረዋል ማለት ነው።
ጀርመን አገር በነበርኩበት ወቅት ይገርመኝ የነበረ አንድ ታሪክ ላካፍል። በአገሪቱ ሕግ መሠረት ጥገኝነት የሚጠይቁ ወይም ሕጋዊ መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የውጪ አገር ሰዎች በሙሉ ፈቃድ ካላገኙ በስተቀር እንዲኖሩ ከተመደቡበት ከተማ እና አካባቢ ተነሥተው እንደፈቀዱ ወደ ሌሎች ከተሞች መጓዝ አይችሉም። ለምሳሌ ጥገኝነት ጠያቂው ሙኒክ አካባቢ እንዲኖር ከተመደበ በራሱ ጊዜ ተነሥቶ ወደ በርሊን ወይም ፍራንክፈርት መሔድ አይችልም። እንደዚያ ቢያደርግ እና መንገድ ላይ መታወቂያ የሚጠይቁት ፖሊሶች ቢያገኙት ቅጣቱ ከባድ ነው። በትምህርት ምክንያት የሚሄዱ እኔን የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያን በቀለማችን ምክንያት በየመንገዱ ፖሊስ ስንት ጊዜ መታወቂያ ይጠይቀን እንደነበር ሳስታውስ ይገርመኛል። ፖሊስ በየመንገዱ መታወቂያ የማይጠይቀው እኖርበት በነበረው በበርሊን ከተማ ያለው ብቻ ሳይሆን አይቀርም። በተለይ ሙኒክጥቁር ሰው ለምን አይቼየምትል ትመስላለች። በየኮርነሩ በፖሊስ መታወቂያ መጠየቅ የተለመደ ነው። አናዳጆች።
ያንን አይቼ አሜሪካ ስገባ የገጠመኝ የዚያ ተቃራኒ ሆኖ ጠበቀኝ። ማንም ዞሮ የሚያየኝ የለም፣ከየት አገር መጣህ?” የሚል የለም። ሁሉም በነጻነት ይሄዳል። ጥገኝነት ጠያቂ ሆነ ሳይንቲስት ማንም መንገድ ላይ አያስቆመውም። ወንጀል እስካልሠራ ድረስ። ፖሊስ ሰውየውን ለማስቆም ምክንያት የሚያገኘው ከወንጀል ጋር በተገናኘ የሚያስጠረጥር ነገር ሲኖር ሆኖ አገኙት። ወደድኩት። ነጻነት እንዴት ደስ ይላል። ከእኔ የበለጠ ደግሞ ሌሎች ባዕዳን አገሮች ረግጠው፣ ትንሽ ኩርኩም ቀምሰው የመጡ ኢትዮጵያውያን በነጻ መኖር ማለት ያለውን ትልቅ ትርጉም እያነሱ ሲናገሩ ሰማኹና አሜሪካንን አመሰገንኩ። ታዲያ ነጻነት መታወቂያ ካለመጠየቅ/ ከመጠየቅ ጋር ብቻ እንደይያያዝብኝ። ምሳሌ ዘይሐጽጽ እንዲሉ አበውምሳሌ መግለጽ የፈለገውን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ለመግለጽ ጉልበት ያንሰዋል ሆኖ ነው።
ኢትዮጵያውያን ለብዙ ዘመናት በነጻነት የኖርን መሆናችን እሙን ቢሆንም ነጻነትን በቅጡ እናውቀዋለን፣ ወይም ነጻነትን በቅጡ ኖረነዋል ለማለት ይከብደኛል። ነጻነትን የማናውቅ ነጻ ሕዝቦች ማለት እኛ ነን። ዛሬም ድምጻችንን ከፍ አድርገን ለመናገር የምንፈራቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ሁለት ሦስቴ ዞር-ዞር ብለን ተገላምጠን፣ ድምጻችንን …… አድርገን የምናወራቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ለራሱ ነጻነት ሰጥቶ የሚያስበውን ፊት ለፊት የሚናገር ቢገኝ እንኳንዕብድና ሰካራም የፈለገውን ይናገራልብለን ሰውየውን እንዲሰክር አሊያም እንዲያብድ እናበረታታዋለን። ወይም በደፈናውጉዱ ካሳአድርገን ከባርነት ነጻ ወጥቶ በብቸነት ቀንበር ተረፈ-ዘመኑን እንዲገፋ እናደርገዋለን። ጸጋዬ /መድኅን - ነፍሱን ይማረውና - “ሕብረት ፈራን፣ ፍቅር ፈራንአለ እንጂ እኛስ የፈራነውነጻነትንነው።ነጻነት ፈራንተብሎ ይስተካከልልኝ።  
ፋሲካ ሥጋዊ እና መንፈሳዊ ማለት ይኸው ይመስለኛል። እኛስ ብዙ ፋሲካ አያስፈልገንም? አንዱ ያንሰናል። ፋሲካዎች፣ ሙሴዎች ያስፈልጉናል። ሙሴውም ቢመጣ ግን ለራሳችን ነጻነት ሳናውጅ ከቆየነው ትርጉም አይኖረውምና በነጻነት መኖርን እንለማመድ። የፋሲካው ሥጋዊ ወመንፈሳዊ ትርጉም ይረዳን። ለራሳችን ሕይወት ራሳችን ወሳኝ የምንሆንበት፣ ድምጻችንን ዝቅ አድርገን በመሳቀቅ የማናወራበት ድኅረ-ፋሲካ ይኖረን ዘንድ። ይሁን ይሁን፣ ይደረግ ይደረግ እንዲል መጽሐፍ። 
         

© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ . የተወሰነ የግ. በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::  

No comments:

Post a Comment