ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Thursday, December 20, 2012

ለአንድ ሀገር ዕድገት የእምነት ተቋማት መኖር ግድ ነው!

                              ‹‹    የቀደመኝ ትውልድ - ባሳብ የሰከረ
                         በተራማጅ ባህል- አናቱ የዞረ
                              በኢቮልዩሽን ህግ- ጠበል እየጠጣ
                                         ፈጣሪን ለመግጠም- ወደ ትግል ወጣ፤. . .››

                                                                                          ግጥም- ስብሐት ገብረ እግዚሐብሔርREAD IN PDF

       ከአንድ ወዳጄ ጋር ሻይ ቡና እያልን በድንገት አሁን ስላለው የአገራችን ሁኔታ ማውራት ጀመርን ፡፡ በብዙ ነገሮች ላይ መግባባት ነበረንና ‹‹ አዎ. . . .›› ‹‹ ልክ ነክ ›› ‹‹ በጣም›› ‹‹ ምን ማድረግ ይቻላል›› የሚሉትን ቃላት በመደጋገም ሀሳባችን አንድ መሆኑን ራሳችንን በአወንታ እየነቀነቅን ተግባባን፡፡ ነገር ግን በስተመጨረሻ በአንዲት ጉዳይ የሀሳብ መለያያት ተፈጠረና ጨዋታችን ደመቅ አለ፡፡ይኸውም ለአንድ ሀገር ዕድገት ቅድሚያ የሚያስፈልገው ‹‹ልማት ወይስ እምነት››? የሚል ነበር፡፡ እሱ ልማት እኔ ደግሞ እምነት ፡፡ አሁን እንደቀድሞው በቀላሉ መስማማት አልቻልንም ፡፡ በመጨረሻ ባለመግባባት ተግባብተን ለመለያየት ወሰንን፡፡
ይህን ጉዳይ ሳሰላስል እና ሰሞኑን በሚዲያና የማህበረሰብ ግንኙነት በሚባሉት ዘዴዎች (በተለይ ፌስቡክ/facebook)፣ እንዲሁም በአንዳንድ ድረ-ገፆች የሚወራውና የሚናፈሰው ወሬ ስመለከት ቢጠቅምም ባይጠቅምም በዚህ ጉዳይ ላይ የግል ሀሳቤን ለመግለፅ ብዕሬን ለማንሳት ፈለኩኝ፡፡ወቅቱም ይህን የሚያስብል ይመስለኛል፡፡
በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተደጋግሞ እንደምንሰማው ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት በልማት ጎዳና ላይ ሆና በዕድገት እየተጓዘች እንዳለች ነው፡፡ እርግጥ ኢትዮጵያ በልማትና ዕድገት መስመር ውስጥ ነች? ሌላኛው ጥያቄ ነው፡፡ ይህ በራሱ አንድ የመወያያ አጀንዳ የሚያስፈልገው በመሆኑ ስለዚህ ጉዳይ የምለው የለም፡፡

ልማት/ዕድገት
     
ልማት
መነሻ ነጥብ እንጂ ማደግን  ማሳያ አይደለም፡፡


       ልማት እና እድገት ተያያዥነት ይኑራቸዋል እንጂ ፍፁም ይለያያሉ፤ ልማት ለዕድገት የሚወስደን መሰላል እንደ ማለት ነው፡፡ ሁሉን ነገር አቅሎ ምቹና የተስተካከለ ሲደረግ. . . ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነው ‹ ዕድገት› ወደሚባለው ቀጣይ ክፍል ይወስዱናል፡፡ ይህን ለማድረግ ሁሉም ሰው ህብረት ሊኖረው ይገባል፡፡ ልማት ላይ መግባባት እና ተነሳሽነት ከሁሉም ይጠበቃል፡፡ እነዚህን ማሟላት ስንችል የሚፈለገውን ግብ መምታት ይቻላል፡፡ ለዛም ነው ከላይ ልማት መነሻ ነጥብ እንጂ ማደግን ማሳያ አይደለም ብዬ የተነሳሁት፡፡ የመለወጥ ተስፋዎች፤ የማደግ ጭላንጭሎች ሲታዩ ልማቱ ውጤታማ እንደሆነ ማሰብ ይቻላል፡፡ ግልፅ ለማድረግ ያህል አንድ ሀገር ብዙ የሰው ሀይል ቢኖራት ፤ የበዛ የማዕድን ክምችት ቢኖራት፣ ለም እና ምቹ መሬት ዙሪያውን ቢከባት ይህንን አስተባብሮ በዘመንኛው አነጋገር ዘላቂነት ባለው መንገድ የህዝቡን የአስተሳሰብ ፣ የአኗኗር ዘይቤ የተሻለ በማድረግ ፣ እንዲሁም የደህንነት ጥራቱንም ከፍ በማድረግ ወደ አንድ ጥንካሬ ተሸጋግሮ እስካልተገኘ ድረስ ዕድገት አለ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡ አለ የምንለው ከላይ የተዘረዘሩት በጥቂቱም ቢሆን ሲሟሉ ብቻ ይሆናል፡፡ ይህንን ለማምጣት የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች ናቸው ልማታዊ እንቅስቃሴዎች የምንላቸው፡፡ እንግዲህ በዚህ ሂደት ውስጥ ሰው የሚያየው፣ የሚቀምሰው፣ የሚያሸተው፣ የሚያነበው፣ የሚወደው፣ የሚጨነቅለት ነገር ሊኖር ይገባል፡፡ እነዚህ ነገሮች ከተጓደሉ ለስራ የሚኖረው ተነሳሽነት ይቀንሳል፤ ለሀገር ያለው ፍቅር ይዳከማል፤ በህብረት በአንድነት ማሰብ ትቶ ግለተኝነትን ወደ መፈለግ ይኬዳል፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ ወደ አንድ ስንደምረው ያልተደራጀ እና ህብረት የሌለው ስለሚሆን በአንድም ይሁን በሌላ ግዜ ለመፍረስ፣ ለመውደቅ የተመቻቸ ነው፡፡ ዘላቂነት እንዳይኖረው ያደርጋል፡፡ እድገትንም እንደተፈለገው ሳይሆን ተናፋቂ ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም ልማት ግብዓት እንጂ ውጤት ስላልሆነ፡፡
ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ለማስወገድ ደግሞ ደህንነት፣ የሰብአዊ መብቶች ማለትም የመናገር፣ የመፃፍ፣ ከቦታ ቦታ በነፃነት እየተዘዋወሩ መኖርን ( በሰላም ወጥቶ መግባት) እና ሌሎችም ከምንም በላይ ለአንድ ሀገር ልማት እና ዕድገት መፋጠን እና ዘላቂት መኖር ዋልታዎች በመሆናቸው አትኩሮት ሊሰጣቸው ግድ ይላል፡፡ እነዚህ በጥቂቱ ሲሟሉ መኖርንም ሙሉ ማድረግ ይጀምራሉ፡፡ ለራስ ከሚባለው አስተሳሰብ አስወጥቶ ለቤተሰብ፣ ለአካባቢ፣ ለህዝብና ለሀገር እንድናስብ እንድንቆረቆር እንድንሞት ያደርጋል፡፡ እዚህ ላይም የመምረጥ ነፃነትም ሳይዘነጋ ማለት ነው፡፡
እስቲ ከዚህ ጉዳይ እንውጣና:: ዐፄ ምኒልክ የተናገሩትን ላስታውስ

   
‹‹ . . . . እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፋፍቶ አኖረኝ፡፡ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ከእንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡

አሁንም ሀገር የሚያጠፋ ሃያማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚሐብሔር የወሰነልንን የባሕር በር አልፎ መጥቷልና እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ የሰውንም መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚሐብሔር ረዳትነት ሀገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡
ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም ፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ ለሚስትህ ለሀይማኖትህ ስትል በሀዘን እርዳኝ፡፡
ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልተውህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡ ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሠው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ፡፡ ››


     ይህ የዐፄ ምኒልክ ንግግር እጅግ ከሚማርኩኝና ሁሌም ባነባቸው ከማልሰለቻቸው ከመሪዎቻችን ንግግሮች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ በጣም ብዙ ትርጎሞችም አሉት፡፡ በዚህ ዘመን ይህን መሳይ ንግግር ባይጠበቅም አሁን ለምናወራለት ሀሳብ ግን ብዙ ትምህርቶችን የሚሰጥ ነው ብዬ ስላሰብኩ አቀረብኩት፡፡ የዐፄው ንግግር መነሻ የጣልያን ጦር አገራችንን መውረሩ ነው፡፡ መጨረሻው ደግሞ የተገመተው ሳይሆን በተቃራኒው በኢትዮጵያ አሸናፊነት መጠናቀቁ ነው፡፡ ይህን ነው እኔ ዕድገት ብዬ የምጠራው፡፡
አንድ ዓይነት አስተሳሰብ፣ አንድ ዓይነት ፍላጎት፣ አንድ ዓይነት ተነሳሽነት የተንፀባረቀበት ሆኖ ምንም አይነት ነገር ቢመጣ በዚህ መልክ ከተሄደ የሚፈለገውን ግብ መምታት እንደሚቻል አስተምሮ የራሱን አሻራ ትቶ ያለፈ ድንቅ ታሪክ ነው፡፡ለአሁኑ ማንነታችን መስታዎት ነው፡
እምነት የሁሉ መተሳሰሪያ ገመድ ነው፤ የጥንካሬ መነሻም መድረሻም በመሆን ያገለግላል፡፡ እምነት ያለው ሰው ሁሌም ጠንካራ ነው፡፡ ለመኖር እምነት ያስፈልገናል ለመተንፈስ እምነት ያስፈልጋል፡፡ለመብላት እምነት ያስፈልጋል፡፡ ወዳጅ ለማፍራት እምነት ያስፈልጋል፡፡ ለሁሉም እምነት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው ዐፄ ምኒልክ
‹‹ . . .ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ ለሚስትህ ለሀይማኖትህ ስትል በሀዘን እርዳኝ፡፡. . . ››  ያሉት ፡፡ ሀይማኖት የእምነት ማቀፊያ ነው ፡፡ ማቀፊው ሲመታ አስኳሉ እንደሚፈሰው እንቁላል ማንም ሀይማኖቱ እንዲነካ አይፈልግም፡፡ ሀይማኖቱ ተነካ ማለት እምነቱ ተነካ ማለት ነው፡፡ እምነቱ ሲነካ ደግሞ ማንነቱ አስተሳሰቡ ተነካ እንደማለት ነው፡፡ ይህም የሚያስከትለው ጣጣ እና ተያይዞ የሚመጣው ነገር ብዙ ነው፡፡ ቅዱስ መፅሐፍም ሁሉም ስለሀይማኖቱ እንዲቆም ይመክራል፡፡ (1ኛ ቆሮ.16፤13/የሐዋርያት ስራ 14፤22/ ዕብ.4፤14 ሌሎችም የበዙ)
በአድዋው ድል ችግረኞች፣ ደሀዎች ኋላ ቀር መሳሪያዎችን ተጠቃሚ የሆኑ ህዝቦች አውሮፓውያኑን ሲረቱ. . . ሲማርኩ. . . ሲገርፉ. . . ሲያባርሩ ማየት የተለመደ አይደልም፤ የለምም፡፡ እዚህ ግን ሆኗል፡፡ ቅኝ ላለመገዛት ሀገርን ሐይማኖትን ላለማጣት በህብረት መስዋዕት መሆንን አስተምሯል፡፡

በቅርብ ጊዜያት በግብፅ፣ በቱኒዚያ የተነሱትን መሪዎቻቸውን ለማስነሳት ያደረጉትን ተጋድሎ ስናይ ምን አጥተው ነው? ምን ጎሎባቸው ይሆን ብለናል፡፡ ይህም በመነሻዬ የተነሳሁትን ሀሳብ ይደግፋል፡፡ በህግ መገዛት እንዳለ ሆኖ ምንም ያህል በሀብት ደረጃ ጣራ ላይ ብንወጣ ውስጣዊ መሻት( ሰብዓዊ መብቶች ) የሚባሉትን ተያይዘው የሚመጡትን ጥያቄዎች ግን መመለስ ግድ ነው፡፡ ሰው በባህሪው ነፃነትን ይሻል፡፡ የሚፈልገውን ማድረግ ፣ ያሻውን መሆን ፣ የሚፈልገውን መውደድ ፣ የሚፈልገውን መጥላት፣ የሚፈልገውን ማምለክ፣ የሚፈልገውን መስራት፣ የሚፈልገውን አስተያየት መስጠት. . .ሌላም ሌላም፡፡ እዚህም ላይ ነው እንግዲህ ማንም መነካት የማይፈልገው፡፡ ድንበሬ ያለውን ቦታ ሲነኩበት፣ ልክ አይደለህምና እንደዚህ ሁን. . . . አትሁን. . . ሲባል፣ የራሴ ነው የሚለው ሲወሰድበት ሲጣልበት. . . ያኔ ፀብ ይጀመራል፡፡

‹‹ . . . ዓለም በሀይማኖት ጉዳይ ተዋጊ አይደለም፤ እንዲያውም አዋጊ ነው፤ ዓለም በፈለገው አቅጣጫ ነው የሚሰራ. . . የመንፈሳዊ ሕይወት ፍቅር የለውም፡፡ ሁሉም በዲሞክራሲ መብት ይለይለት ባይ ነው፡፡ . . .›› ይላሉ አባ ገ/መድህን ከበደ በ‹‹ ከህግ ስራ የሆኑት ሁሉ ከርግማን በታች ናቸው፡፡ (ገላ.3፤10) በሚለው መፅሐፋቸው፡፡

ዓለም ለሀይማኖት እሴቶች ቦታ እያጣች በመምጣቷ ቤተክርስቲያናት ሲቃጠሉ፣ ሲዘረፉ፣ የሌባ ማፍሪያ ምንጭ ሲሆኑ እንደቀድሞው አያሳስባትም፡፡ ክብርም አትሰጥም፡፡ መንግስታትም ሆነ መሪዎች ለመንፈሳዊ አስተሳሰብ ሳይሆን ለዲሞክራሲ አስተሳሰብ (ለዓለማዊ አስተሳሰብ) ቅድሚያ መስጠት ጀምረዋል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው አሁን አሁን በሀገራችን እያየን ያለነው ጉዳይ ነው፡፡ ዕድገትን ማምጣት የሚቻለው ገዳሞችን በመረበሽ፣ በማፍረስ የሽንኩርት ወይም የስኳር ልማት በማስጀመር ይመስላቸው ጀምሯል ፡፡ እንዲሁም የቤተክርስቲያንን ቦታ እና ይዞታ በመውሰድ ለአንድ ባለሀብት መሸጥ የተለመደ እየሆነ ነው ከዚህም አልፎ ስለ ሀገር ዕድገት የሚታሰበው ቤተክርስቲያን ታሪኬ ናቸው ቅርሶቼ ናቸው የምትላቸው ሀብትና ንብረቶቿን በማፍረስ እየሆነ ነው ፡፡
ከላይ ስነሳ እንዳልኩት ልማት ማለት ትልቅ ለመሆን ለሚደረግ ሽር ጉድ ነው፤ሂደት ነው፡፡ የስኳር ልማትም ይኑር፣ የአበባ ልማትም ይስፋፋ፣ የመንገድ፣ የውሃ፣ የኃይል ማመነንጫዎች ና የመኖሪያ ቤቶች ይገንቡ፡፡ እነዚህ ነገሮች ሲሟሉ ነው ወደ ተፈለገው አቅጣጫ በፍጥነት መሄድ የሚቻለው፡፡ ዕድገትንም ማቅረብ የሚቻለው፡፡ ነገር ግን ይህ ወይም ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ብቻም አይደልም ለእድገት መሰረቱ፡፡ መንፈሳዊ አስተሳሰብም ለዕድገት ቁልፍ ነው፡፡ ልንጠብቀውና ሁሌም ከግምት ውስጥ ልናስገባው ይገባል፡፡

አድገዋል የምንላቸው አሜሪካኖች የእምነት እሴቶች እና ውበቶች አጥተን በገንዘብ ወረቀታቸው ላይ ‹‹ IN GOD WE TRUST/ በእግዚሐብሔር እናምናለን ›› ብለው ፅፈዋል፡፡ በተጨማሪም ‹‹ GOD BLESS AMERICA/ እግዚአብሔር አሜሪካን ይባርክ ›› ብለውም መሪዎቿ በእያንዳንዷ በየንግግራቸው ያስገባሉ፣ ይላሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ምንም ብናድግ ምንም ብንበለፅግ የፈጣሪ እርዳታ አስፈላጊ መሆኑን እንዲሁም ያለ እምነት ሀገር እንደማትኖርና እግዚአብሔርን ሳያምኑ መኖር የትም እንደማያደርስ ነው፡፡ ግን አሜሪካኖች እንደዛ ናቸው ወይ ከተባለ አዎ ወይም አይደሉም ነው መልሱ፡፡ እኔ ላተኩር የፈለኩት ግን ‹‹ ማመን ›› የሚለው ቃል ትልቅ ቦታ እንዳለውና እምነት ወሳኝ መሆኑን ነው ፡፡ እነሱ ያላቸውን ተቀብለው እና አስማምተው ሲኖሩ እንደእኛ በእምነት የፀኑ እና የተገነቡ ሀገራት ደግሞ ያላቸውን በማፍረስ በአንድ ግዜ ማደግን ይሻሉ፡፡ ለዓመታት ስናኮራፋ ቆይተን ድንገት ሁሉ አማረሽ እየሆንን ነው፡፡ ችኩል የሆነ አስተሳሰብ ሲበዛ እየተንሰራፋ ነው፡፡ ማፍረስ፣ ማጥፋት፣ ማውደም ብቻ እየሆነ ነው፡፡ ልማት የሚል ቁንፅል መነሻ ለብዙ ጥያቄዎች መነሻ እየሆነ ነው፡፡
አንድም እምነት ልማትን አይቃወምም፡፡ ምን አልባት ሊባል የሚችለው ልማት ከመንፈሳዊ ህይወት ከመንፈሳዊ አስተሳሰብ ጋር ቢሆን መልካም ይሆን ነበር ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያን እና ያለፈ ታሪኳን ብንመለከት ምን ያህል በእምነት የጠነከረች እና የስልጣኔ( እድገት) ጣራ የነካች እንደነበረች ነው የሚያሳየን፡፡
ድሮ በዘመነ መሳፍንትም ይሁን ዘመናዊቷን ኢትዮጵያ ማለትም ከ1847 ጀምሮ እስከ ንጉስ ሀይለ ስላሴ ግዜ ብናይ ሁሉም ማለት በሚያስችል ሁኔታ ለቤተክርስቲያን ክብርና በውስጧም ላሉ ቅርሶቿና ትውፊቶቿ የሚጠነቀቁ ነበሩ፡፡ የአክሱም ሀውልትን ያየ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የጎበኘ፣ የፋሲለደስን ህንፃ ቤተመንግስት ያየ. . . . በዓለም የንግድ ግንኙነት ላይ የነበረንን ተፅዕኖ እና ተሰሚነት የሚያውቅና የሰማ ሁሌም መገረሙ መደነቁ አይቀርም፡፡

የጥንት የሮም ጳጳሳትና የካቶሊክ አባቶችም ወታደሮችን ድል አድርገው እንዲመጡ ባርከውና መርቀው እግዚአብሔር ከእነሱ ጋር እንዲሆን ተመኝተው ወደ ጦር ግንባር እንደሚልኳቸው ታሪክ ይናገራል፡፡ እግዚአብሔርን ሳይዝ የሚሄድ ወታደር ደግሞ መረታቱ ስለማይቀር ኢትዮጵያውያም የውጪ ጠላቶች ሲመጡ ታቦታትን በመሸከም የጦር አውድማዎች ላይ ጠላትን ድባቅ መተው ድልን ይጎናፀፉ ነበር፡፡ ሁሌም አሸናፊዎች ነበሩ፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ትልቁ እና ሁሌም የምንኮራበት የአድዋ ድልም ከአባቶቻችን ታላቅ ጀግንነት ጀርባ የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት እንደ ነበረ ግልፅ ነው፡፡ እምነት ያለው ያሸንፋል፡፡

ታዲያ ዛሬ ምን ነካን
 
     የዚህ ሁሉ ታሪክ ባለቤትና ድንቅ የጀብደኝነት ታሪክ እና የጀግኖች መናኸሪያ እንደነበረች ሲታይ . . . ዛሬ ምን ነካቸው ኢትዮጵያውያንን ያስብላል፡፡ እግዚአብሔር ሁሌም ኢትዮጵያን ስለሚጠብቅ እንጂ አሁን በዚህ ግዜ ጠላት ቢመጣ ምን እንደሚውጠን ማሰብ ቀላል ነው ነበር፡፡ የአባቶች ያቆዩት ሞራል እና በሰው ብዛት ካላሸነፍን በስተቀር እምነቱንማ ችላ እያልንና እየጣልን ነጥተናል፡፡ አውሮፓዊ አስተሳሰብ፣ ስግብግብነት ፍቅር ማጣት በሀገሪቱ ስር እየሰደደ ነው፡፡ ያ ሁሉ ስልጣኔ እና ዕድገት በነበረ ሰዓት ኢትዮጵያ አይደለም የራሷን ልትጥል የሌላ ዕምነት ተከታዮችንም በእንግድነት የምትቀበል በራሷ የምትኮራ፣ ኢትዮጵያዊነት በራሱ ኩራት የሆነባት የበሰለች ሀገር ነበረች፡፡ አሁንም መሆን ይቻላል፡፡
                                      
‹‹ ለወገንና ለሀገር የሚጠቅም ስራ ስሩ፤ለሆዳችሁ አትደሩ፣
                                                    ፍቅርና መቻቻል አይለያችሁ፡፡››
                                                                                                    አቡነ ጴጥሮስ

ዐፄ ምኒሊክ በማርያም ለምነው ያቆሟት ኢትዮጵያ፣ አቡነ ጴጥሮስን የመሠሉ ታላላቅ ሠማዕታት የተሰዉላት፣ እንደነ አበበ ቢቀላ በባዶ እግራቸው ደማቸውን የዘሩላት የሮጡላት ፣ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ቀን ከሌት ሰላም ውላ ሰላም እንድታድር በየዋሻው ገዳማቱ ሰውን ርቀው ሸሽተው በፀሎት ፈጣሪን የሚማፀኑላትን ውድ ልጆች የያዘች አሁን አሁን ግን እነዚህን ውድ ልጆቿን ለምን እንደማታከብር ግልፅ አይደለም፡፡ እነዚህ የተከበሩ ግለሰቦችና ሠማዕታት ቅድሚያ ለሀገራቸው ለሀይማኖታቸው ቦታ የሚሰጡ፣ ክብር ያላቸው ናቸው ፡፡ እኛ ያልሰራነውን ተአምር እና ጀብደኝነት የፈጸሙና እናት ሀገራችንን ላስከበሩ ሁሉ አክብሮትና ቦታ መስጠት ያስሞግስ ይሆን እነጂ አያስወቅስም፡፡ የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን ያድነን፡፡ አነሰም በዛም የሀገርን ስምና ዝና ከፍ ያደረጉ በመሆቸው ክብር ይገባቸዋል፡፡ አዲስ አበባ በትልልቅ የመንገድ አደባባዮች የተሞላች ናት፡፡ በድርጅት ማስታወቂያዎች ከመሙላት ይልቅ በሀገር በህዝብ የተከበሩ ግለሰቦችን ለማስታወስ ሀውልት ሊሰራላቸው እንጂ ታሪካቸው እንዲጠፋ መሯሯጥ የለብንም፡፡ የእነርሱን ታሪክ በማጥፋት ምን ዓይነት ትውልድ ልንገነባ እንደሆነ ግልፅ አይደለም፡፡ ዕምነት የሌለው?? ሀገሩን የማይወድ እና ለማንም አሳልፎ የሚሰጥ?? ከንቱ ትውልድ ከማፍራት አንተርፍም፡፡ ይህ ደግሞ ለማንም አይጠቅምም፡፡ እስቲ ይታየን ይህ ትውልድ እውነት እባክህን ናና ሀገርህን አልማ፣ አሳድግ ቢባል ይሰማል?? የሀገርህን ባህልና ስርዓት ተማር ቢባል ፍቃደኛ ይሆናል?? ዐፄ ሚኒሊክ የተናገሩትን
‹‹. . . ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ ለሚስትህ ለሀይማኖትህ ስትል በሀዘን እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልተውህም፡፡ ›› ቢባል አይስቅም?? እኔ ስጋት አለኝ፡፡
ለዚህ ሁሉ መፍትሄ የምትሰጠውና ዓለማዊውንም መንፈሳዊውንም የምታገናኝና ድልድይ ሆና ትልቅ ሚና በመጫወት በስነምግባር የታነፀ፣ ፈጣሪን የሚፈራና ሀገሩን የሚያከብር ህዝብን የሚወድ፣ መንፈሳዊ ፍቅር ያለበት፣ ለስራ ተነሳሽ የሆነ ትውልድ የምታፈራና የምታንፀው ደግሞ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ እንዲሁም ገዳማት ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የሐይማኖት ተቋማት ናቸው፡፡ ስለዚህ ቅድሚያ አትኩሮታችን መጀመር ያለበት እነዚህን ተቋማት በማክበርና አብሮ ለመስራት በመዘጋጀት ነው፡፡

የብዙ ሀይማኖት መገኛ፣ የብሔር ብሔረሰቦች ጥርቅም ወዘተ. . . እንላታለን፡፡ ይሁን መልካም ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ናይጄሪያውያን የበዛ የዕምነትና የሀይማኖት መሞከሪያ ቤተ-ምርምር (laboratory) መሆን ሀገር ከማሳደግ ይልቅ ረብሻ እና ጦርነትም ከማስፋፋት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ መግባባት መቻል በራሱ የአንድ ሀይማኖት መገለጫ መሆን አለበት፡፡ ሁሉም እየዘለለ በሚያነሳው ሀሳብ አንዱ መበደል የለበትም፡፡ ሁሉንም በእኩል ለማየት ሲባል የአንዱ እምነት ተቋም ሀብትና ንብረት ለሌላው መሰጠት የለበትም፡፡ በየትኛው ፈጠራችን ነው? የትኛው ለውጣችን ይሆን የእምነት ተቋሞች ላይ እጃችንን እንድናነሳ የሚያደርገን? የትኛው የዲሞክራሲ አስተሳሰብ ነው ለቅርሶች ቦታ እንዳንሰጥ የሚገፋን. . . መልስ የሚሻቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡
በእንደዚህ ሁኔታ ምንም ዓይነት ልማትም ሆነ ዕድገት ፈፅሞ መታሰብ የለበትም፡፡ መቀመጫን በመርፌ ወግቶ አረፍ በል እንደማለት ነው፡፡ እንደማሾፍም ነው የሚቆጠረው፡፡ ለማደግ ወይም ለልማት የምናመጣው ሀሳብ ያለንን የሚያጠናክር እንጂ የሚያዳክም መሆን የለበትም፡፡ ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን ሲባል የማይነካ እየተነካ. . . የማይባል እየተባለ. . . ሁሉንም እንደተፈለገ እየተጨፈለቀ አይደለም፡፡
‹‹ የጥበብ መጀመሪያ እግዚሐብሔርን መፍራት ነው ›› ይላል ዳዊት በመዝሙሩ (111 ፤ 10) የውስጥ ችግር ካልሆነ አድገዋል የምንላቸው አብዛኛዎቹ ሀገራት በሙሉ ለሐይማኖት አባቶቻቸው እንዲሁም ለእምነት ተቋሞቻቸው ክብርና ቦታ ይሰጣሉ፡፡( የሚሰጡበት መንገድ ትክክልም ይሁን አይሁን) በተቃራኒው እኛ ደግሞ ማጥፋት እየጀመርን ነው፡፡ ጥበብ ወይም እድገት መነሻው እግዚአብሔር ነው፡፡ እሱን ለሚወዱና ለሚያከብሩ ደግሞ አክብሮት ሊኖረን ይገባል፡፡

                                     
‹‹ . . .ክፉ ነገር ሀገራችንንም አያገኛትም፡፡
                                
ነፋስ እንዳይገባባችሁ በያላችሁበት ጠብቁ፡፡ ወንድሜ ወንድሜ ተባባሉ. . . ››
                                                                                                                       
አፄ ሚኒሊክ

የእውነት ኢትዮጵያችን የተደራጀ ጦር ቢኖራት፣ የእህል ጎተራዎቿ ቢሞሉ፣ የጥናት ማዕከላት ላይብረሪና ዩኒቨርስቲዎች ቢገነቡ፣ ሆስፒታሎች በየአካባቢው ቢኖሩ፣ መንገዶች ቢስፋፉ ደስታው የሁሉም ነው፡፡ መንግስትም ይህ አስፈላጊ እንደሆነ እንደሚያውቅ እገምታለሁ ይህንን ሊያሟላ እንደሚጥርም ግልፅ ነው፡፡ በዚህ ጥረት መካከል ግን ‹‹ ይህ ለምን ይሆናል›› . . . ‹‹ አረ. . አረ. . .›› ‹‹ ለማን አቤት እንበል›› የሚሉ ጥያቄዎች ሲነሱ ይሰማል፡፡ ቅሬታዎች እየበዙ ነው፡፡ ህዝብን መስማት ደግሞ ትልቅነት እንጂ ፈሪ መሆን አይደለም፡፡ ምንም ይሁን ምን ህዝብ ከመንግስት ይበልጣል፡፡ ህዝብ አዋቂ ነው፤ መንግስትም ከህዝብ መውጣትና መምሰል አለበት፡፡ ገና ሳናድግ ልማት ላይ ካልተስማማን ሁሉም ነገር ታጥቦ ጭቃ ነው የሚሆነው፡፡
ለሁሉም ክብር ይሰጥ በተለይ ለዕምነት ተቋማት፡፡

ምስጋና ለውድ የኢትዮጵያ ልጆች

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!

5 comments:

 1. Thank You Bisrat!

  ReplyDelete
 2. thank you bisra, it is an impressive writing!!!

  ReplyDelete
 3. thank you bisra,it is an impressive writing

  ReplyDelete
 4. ሰሜ ካለ ይኽው በቄ ነበር ። ለማነኛውም አግዝአብሄር ይስጥልን።

  ReplyDelete
 5. በጣም ጥሩ ፅሁፍ ነው፡፡ አንዳንዴ እውቀታችንን ለመልካም ካልተጠቀምንበት ወይንም ያወቅንበት መንገድ ትክክል ካልሆነ ጥፋቱ ከፍ ያለ ነው ለትውልድም ትልቅ ጠባሳ ትቶ ያልፋልና እያንዳንዱ እርምጃችንን ብናስብበት መልካም ነው፡፡

  ReplyDelete