አንቺን የያዘ ሠው ምን ይጎድልበታል፣
በምልጃሽ በረከት ቤቱ ሞልቶለታል፡፡
*******************ግላዊ ምስጋና፦
እመ አምላክ.... የጌታዬ እናት ለእኔ እና ለቤተሰቤ ያደረግሽውን ባወራ ብመሠክር ማን ያምናል? የትኛውስ ቃል ይመጥንሽ ይሆን? እንዴትስ ብፅፈው የልቤ ይደርስ ይሆን? ገና ያኔ ምንም ከማላውቅበት ....ከልጅነቴ አንስተሽ በሃጢያት እስከተጨማለኩበት የዛሬው ...የእስከ አሁኑ ማንነቴ ድረስ የእናትነት ፍቅርሽ እና ጥበቃሽ አልተለየኝም፡፡
ማርያም ሆይ፦
" የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? " ብላ ኤልሳቤጥ መመስከሯ ቢያንስብሽ እንጂ ክብርሽን አይገልፅም፡፡ ድንግል እናቴ.....እናቴ መሆንሽን ዘለዓለም እንዳወራ እርጂኝ፤ ስመሠክር ልኑር፡፡
ከብዙ ፈተና እና መከራ ታድገሺኛል፡፡ ሠዎች የሸረቡትን የተንኮል መረብ በጣጥሰሽ ጥለሺልኛል፡፡ ማንም ባልነበረኝ ጊዜ በጭንቀቴ ጊዜ ከጎኔ የነበርሽ.... ስምሽን ስጠራ ብቻ ሳይሆን ገና ስምሽን ለመጥራት ሳስብ ሃዘኔና ጭንቀቴ ብን ብሎ የሚጠፋው ፤እንባዬን የምታደርቂ .... መፅናናትን የምታላብሺኝ እኔ ምን ስለሆንኩኝ ይሆን?
ይህ ሁሉ ፍቅር ለእኔ ይገባኛልን? ለእኔ የሆንሽውን አረ ለማን ሆነሻል? መታደሌስ እንዴት ይገለፅ ይሆን? ያልታደለ አንቺን ይክዳል ያንቺ ፍቅርና በረከት....ቤቴ የሞላውስ ምስኪኑ እኔስ ምን እባል ይሆን? በምንስ ሚዛን እመዘን እሠፈር ይሆን? ሁሌም ከሃሳብ ከጭንቀት እንደምትጠብቂያቸው የሚያምኑትን ቤተሰቦቼን የመከራ ጊዜያቸው አብቅቶ ያልጠበቁትን.....የደስታ መዓት ያፈሰስሽባቸው ፣ የሚሆኑት ጠፍቶ የደስታ ሲቃ ተናንቋቸው የሚጨብጡት አጥተው እንደ ህፃን እንዲቦርቁ ያደረክሽ የአምላኬ እናት እመ አምላክ አንቺ ብቻ እኮ ነሽ፡፡
"ማርያም" እናቴ ከስምሽ ፍቅር ይዞኛል፤ ከእናትነትሽ ....እቅፍሽ ሞቆኛል፤ ከምስልሽ ስር ተንበርክኬ.... ማን አለኝ ያላንቺ ብዬ ስለምንሽ ሳለቅስ ስማፀንሽ ምላሽሽ አንጀት ያርሳል፡፡ ደረት አስነፍቶ ያስኬዳል፡፡ ከቅዱሳን ፃድቃን ሠማዕታት ሁሉ የምትበለጪ አንዳቸውም ከክብርሽ ጫፍ የማይደርሱ ከእግዚአብሔር አብ ጎን ቆመሽ የምድርን ጥያቄ ለልጅሽ ለወዳጅሽ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የምታቀርቢ ታማኝነትሽ ምልጃሽ የማይፋቅ የአዳም ኩራት የሆንሽ አማላጃችን እኮ አንቺን የሚመጥን ምን ነገር አለ?
አንቺ እኮ ሠው በጠፋ ጊዜ...አዳም በጨነቀው ሰዓት... ሕዝበ አዳም ተደምሮ ተጨምቆ ያንቺን ያህል ንፅዕና ባልነበረው ጊዜ የተገኘሽ.... የመዳናችን መነሻ መሠረታችን ነሽ፡፡ የጠፋውን በግ ድልድይ ሆነሽ ከጌታው ፣ ከፈጣሪው ያገናኘሽ እመ-ዓለም እመ-ብዙሃን የሁላችን እናት አንቺ እኮ ፍፁም፣ ድንቅና ልዩ ነሽ፡፡
ማርያም እናቴ ሆይ፦
አንቺን የካድኩኝ እንደው የሕይወት እስትንፋሴ ይቆረጥ!! እንደ ዓጢያቴ ቢሆን ኖሮ እንዴትስ እግዚአብሔር ፊት እቆም ነበር? ይህን ተገንዝቦ ይሆን እንዴ ፈጣሪ እንደ አስታራቂ.... እንደ መጠለያ አንቺን ...የሰጠን? ኦ ማርያም ምንኛ መታደል ነው !!! እንደ ስምሽ ማር እንደሆንሽ በምን ቃል ልመስክር?
ድንግል ሆይ ውስጤ ባንቺ ፍቅር የተሞላ እና የስራዬ ፣ የኑሮዬ ....የህይወቴ መመሪያ ህጌ አንቺ ነሽ... ባንቺ በሚመጣብኝ ድርድር የለኝም....ምንም ነገር ከአንቺ አይበልጥብኝም፡፡
ሁሌም በፍቅርሽ ጥላ በምልጃሽ በረከት እኖር ዘንድ ባርኪኝ፣ ቀድሺኝ!!
"ማርያም ማርያም ብዬ ስምሽን ልጥራው፣
አይደክመኝም እኔ ብደጋግመው፡፡"
ክብሯ በእኔ በደካማው መገለፅ ለማይችለው ለእመቤታችን ለቅድስተ ቅዱሳን ፣ ንፅዒተ ንፁዓን ፣ እመ ብዙሃን ወወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ዘላለማዊ ክብር ይሁን፡፡
መታሰቢያነቱ እጅግ በጣም ለምወድሽ በእምነት መጠንከር እስከ ምን ድረስ እንደሆነ ላስተማርሽኝ ጠንካራዋ (ያልተዘመረልሽ ጀግና) እህቴ ፀሐይ ገብሬ
በህይወት እያለሁ አምላከ ተክለሃይማኖት ደስታሽን እና አለምሽን ያሳየኝ፡፡
መጋቢት 21 , 2007 ዓ.ም
WAW BETAM YAMERAL YANTEW YOHANNES DANIEL BERTA
ReplyDelete