ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Thursday, March 2, 2017

ለአርበኞቻችን፣ ለጀግኖቻችን ያለን ፍቅርና ክብር

ለአርበኞቻችን፣ ለጀግኖቻችን ያለንን ፍቅርና ክብር በተግባር ሊገለጽ ይገባል!

ፀሐፊ ፦በተረፈ ወርቁ

            ኢጣሊያዊው ዕውቅ የታሪክ ጸሐፊና ተመራማሪ ኮንት ሩሲኒ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ በጻፈው ዳጎስ ባለ መጽሐፉ ላይ ስለ አገራችን የረጅም ዘመናት ታሪክና ሥልጣኔ እንዲሁም የነጻነት አኩሪ ተጋድሎ እንዲህ ሲል ነበር የጻፈው፡-

                What role does fate intend, in the course of future moves within the Dark Continent, for the one African community which has succeeded in remaining free? More than two thousand years of history, of independence, defended with determination, of wars against everything and everybody are assuredly a great responsibility for a race of human beings to carry.

     ይህን የኮንት ሩሲኒ ስለ አገራችን የረጅም ዘመናት የነጻነት ተጋድሎና ታሪክ የሰጠውን ምስክርነት ያስቀደምኩበት ዋናው ምክንያት በዛሬው ጽሑፌ ስለ ጀግኖ አባቶቻችንና እናቶቻችን፣ በተለይም ደግሞ እነዚህ ጀግኖች ባለውለታዎቻችንን የታሪክ ሕያው ዘመናትን ተሻግሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሸጋገር ዘንድ የኢትዮጵያ ጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማኅበር እያደረገ ባለው ወቅታዊ እንቅስቃሴዎቹ ዙርያ ጥቂት የመወያያ ቁም ነገሮችን በማንሣት እንድንወያይ በማሰብ ነው፡፡

     እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር የነጻነት/የአርበኞችን የአልማዝ ኢዮቤልዩ መታሰቢያ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች በታላቅ ድምቀት በአገር አቀፍ ደረጃ ለማክበር ከወዲኹ በታላቅ ዝግጅት ላይ እንደኾነ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ሰምተናል፡፡ ማኅበሩ ከዚህ በዓል ጋር በተያያዘም ለጀግኖች አርበኞቻችን መታሰቢያ የሚኾን ቤተ-መዘክር/ሙዚየም ለማስገንባትም የተንቀሳቃሽ ስልክ አጭር መልእክት የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ እያደረገ ነው፡፡ ከዚህ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ታላቅና በጎ ዓላማ ጎን እንድንቆምም የቴሌ የድጋፍ መልእክት በየዕለቱ እየደረሰን ነው፡፡

ታዲያስ የኢትዮጵያ ጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ለዛሬው ክብርና ነጻነት ላበቁን አርበኞቻችን ታሪካቸው ሕያው ሆኖ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፍ ዘንድ የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ ምን ያህሎቻችን በተግባር ምላሽ እየሰጠን ይኾን … ብዬ ለመጠየቅ ወደድኹ …?! ዕውቋ አርቲስት እጅጋየሁ ሺባባው/ጂጂ ‹‹ዐድዋ›› በሚለው እጅግ ተወዳጅ ዜማዋ፡-

        የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነጻነት፣
        ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት፣
        ትናገር ዐድዋ ትናገር አገሬ፣
        እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ …! እንድትል በጥዑም ዜማዋ፡፡



      በእርግጥም መተኪያ የሌላትን፣ ክቡርና ውድ ሕይወታቸውን ሠውተው፣ ደማቸውን አፍሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ከቅኝ ገዢ ኃይሎች ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀው፣ እናት አገሬ እኛ ልጆችሽ በሕይወት ቆም እያለን የአንቺ ክብር፣ የሕዝቦችሽስ ነጻነት እንዴት ይደፈራል ብለው በዱር በገደል፣ በየተራራውና በየሸንተረሩ በታላቅና አኩሪ ተጋድሎ የአገራችን ነጻነትና ልዑላዊነት ያስከበሩና ታሪክ ስማቸውን በወርቀ ቀለም የከተበላቸውን፣ እነዚህን የምንጊዜም ባለውለታዎቻችን የሆኑት ጀግኖቻችን የሚገባቸውን ክብር አግኝተዋል፣ ሰፊ ዕውቅናም ተችሯቸዋል ብለን በሙሉ አፋችን ለመናገር የምንደፍር ኢትዮጵያውያን ወገኖች ያለን አይመስለኝም፡፡

            ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ፣
            የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ፡፡ የሚለው ይህ ለብዙዎቻችን ጆሮ እንግዳ ያልኾነ አጭር ስንኝ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ያደረጉት ውለታ የተዘነጋባቸውና ልፋታቸውና ድካማቸው ኹሉ እንደ ከንቱ የተቆጠረባቸው ጀግኖቻችን/አርበኞቻችን የውስጥ ብሶትና ቁጭት የወለደው እንጉርጉሮ ኾኖ ለዘመናት አብሮን የዘለቀ ነው፡፡ ይህን የባለውለታዎቻችንን ብሶትና እንጉርጉሮ፣ ወቀሳና ኀዘን ይበቃ ዘንድ ደግሞ ይህ ትውልድ ትልቅ የታሪክ ሐላፊነትና ሸክም በጫንቃው ላይ ተጥሎበታል፡፡

         አገራችንን ለነጻነትና ለሉዓላዊነት በተደረገ የጦር ሜዳ ውሎ- በጀግንነት፣ በዲፕሎማሲውና በፖለቲካው መስክ፣ በአርቱና በሥነ ጥበብ፣ በስፖርቱና በተሰማሩበት የሙያ መስክ ሁሉ የአገር ባለውለታ የሆኑ፣ የትውልድ አርአያና ተምሳሌት የሆኑ ዕንቁዎቻችንን የሚገባቸውን ክብርና ዕውቅና ልንሰጣቸው ይገባል፡፡ በዚህ ረገድም ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ መንግሥትና አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ለአገርና ለወገን ፍቅርና መቆርቆር ያላቸው ግለሰቦችና ባለሀብቶች የጀመሩትን ለእነዚህ ባለውለታዎቻችን፣ ጀግኖቻችን የሚገባቸውን ክብርና ዕውቅና እንዲያገኙ እያደረጉት ያለውን በጎ እንቅስቃሴ አጠናክረው በተቀናጀ መልኩ ይቀጥሉበት ዘንድ የሚገባ ነው፡፡

         በዚህ ረገድም ጀግኖቻችን፣ ዕንቁዎቻችን የሚገባው ክብርና ዕውቅና ይቸራቸው ዘንድ ሕያው ታሪካቸውና ሥራቸውም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፍ ዘንድ የኢትዮጵያ ጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማኅበር የጀመረውን እንቅስቃሴ በመደገፍና ሁላችንም ከዚህ በጎ ዓላማ ጎን በመቆም የበኩላችንን ጥረት ማድረግ እንዳለብን የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡
የአገራችንና የሕዝቦቻችን ኩራትና ክብር የሆነው የጀግኖቻችን አኩሪ የነጻነት ተጋድሎ ለሕያው ታሪካቸውና ውለታቸው መታሰቢያ የሚሆን ቤተ-መዘክር/ሙዚየም ለማሠራት የጀግኖች አርበኞች ማኅበር እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በሐሳብ፣ በሞራል፣ በሙያ፣ በዕውቀትና በገንዘብ የበኩላችንን ድጋፍ እናደርግ ዘንድ ደጋግሜ አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡
 
         ይህ የኢትዮጵያ ጥንታዊት አርበኞች ማኅበር የጀመረው ሥራ ከግብ ይደርስ ዘንድ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባለሀብቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ በኪነ ጥበብና በአርቱ ዙርያ የተሰማሩ፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን፣ እንዲሁም ደግሞ የአገራችን የረጅም ዘመን የነጻነት ተጋድሎ ታሪክና ሥልጣኔ ወኔና ጉልበት ሆኗቸው ነጻነታቸው በእኛ እርዳታ የተቀዳጁ የአፍሪካ አገራት፣ ሰላምን በማስክበር ግዴታ- ከሱዳን እስከ ኮንጎ፣ ከሶማሊያ እስከ ላይቤሪያና ኮርያ ልሣነ ምድር ድረስ ለሕዝቦች ነጻነትና ሰላምና ዋጋ የከፈሉ የጀግኖቻችን ባለውለታ የሆኑ የአፍሪካ አገሮች፣ የአፍሪካ ኅብረትና ሌሎችም ወዳጅ አገራት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በሰፊው የተቀናጀ ቅስቀሳ ሊደረግ ይገባል፡፡

        እስኪ አገራችን ኢትዮጵያና ጀግኖቻችን ለሌሎች አገራትና ሕዝቦች ነጻነትና ልዑላዊነት መከበር የዋሉትን ውለታ በጥቂቱ በማንሳት የዛሬውን መጣጥፌን ልቋጭ፡፡ የዛሬው የ90 ዓመቱ አዛውንት አርበኛ፣ የዚምባቡዌው መሪ ሮበርት ሙጋቤ ለአገራቸው ነጻነትና ለሕዝባቸው መብት በሚታገሉበት በዛን ቀውጢ ወቅት ወታደራዊ ሥልጠና የወሰዱት፣ ድጋፍና ማበረታቻ የተደረገላቸው ከአገራችን ከኢትዮጵያ ነው፡፡ ዚምባቡዌ ነጻነቷን እስክትቀዳጅ ድረስም የአገራችን ደጋፍና እገዛ አልተለያትም ነበር፡፡

          አገራችን ለናሚቢያ ነጻነት በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ቆማ ተሟግታለች፡፡ ለናሚቢያው ስዋፖና ለሞዛምቢኩ ሬናሞ ነጻ አውጪ የአርበኞች ፓርቲ የሬዲዮ ጣቢያቸውን በአዲስ አበባ እንዲከፍቱ ትልቅ ድጋፍ አድርጋለች፡፡ የነጻነት ትግላቸው ፍትሐዊ እንደሆነ በዓለም መድረክ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ አሰምታለች፡፡ ለመሆኑ ስንቶቻችን ነን ለኬንያው የነጻት ታጋይ ለሆኑት ለጆሞ ኬንያታ ሴት ልጅ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን በምትከታተልበት ወቅት ትምህርቷን እስክታጠናቅቅ ድረስ በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ በየወሩ 200 የኬንያ ሽልንግ የገንዘብ ድጎማ ይደረግላት እንደነበር የምናውቀው፡፡

         በተለይም ደግሞ አገራችን ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪካ የነጻነት ታጋይ ለኾኑት ለኔልሰን ማንዴላ ወታደራዊ ሥልጠና እንዲያገኙ ከማድረግ ጀምሮ የአፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ ጽ/ቤት በአዲስ አበባ እንዲከፈት፣ ለጥቁር ደቡብ አፍሪካ ታጋዮች ከወታደራዊ ሥልጠና ባሻገርም በቀድሞ የቀ.ኃ.ሥ. በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነጻ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ተመቻችቶላቸው ነበር፡፡

           የደቡብ አፍሪካው የነጻነት ታጋይና የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚው ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ/ታታ ማዲባ ‹‹Long Walk to Freedom›› በሚለው ዝነኛ መጽሐፉ ስለ ኢትዮጵያ ጉዞውና ቆይታው በተረከበት ምዕራፉ ላይ ከጠቀሳቸው እውነታዎች መካከል አንድ ሁለቱን ልጥቀስ፡፡

         ወጣቱ የነጻነት ታጋይ ማንዴላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሙሉ በሙሉ በጥቁር ኢትዮጵያውያን አብራሪዎችና የበረራ አስተናጋጆች የሚመራ መሆኑ እጅጉን ያሰገረመውና ያስደነቀው ነገር ነበር፡፡ እርሱና ወገኖቹ በባርነት ቀምበር ውስጥ ወድቀው በሚኖሩባት በአገሩ ደቡብ አፍሪካ እንዲህ ዓይነቱ የአእምሮ ጥበብና ትምህርት የሚጠይቅ ሥራ በነጮች እንጂ በጥቁሮች ሊሠራ እንደማይችል ለዓመታት የተሰበከው የዘረኛው የአፓርታይድ ሥርዓት ስብከት አእምሮውን በርዞት ነበርና ኢትዮጵያውያን ጥቁር ፓይለቶች በተመለከተበት ቅፅበት የዘረኛው የአፓርታይድ መርዘኛ ስብከት ከንቱ መሆኑን ነበር ያረጋገጠው፡፡

          ማንዴላ በዚህ የነጻነታችን ክብርና ኩራት በሆነው በአየር መንገዳችን በቃል ሊገለጽ የማይችል ክብርና ኩራት ነበር የተሰማው፡፡ ማዲባ በዚህ የአርበኞቻችን አኩሪ ተጋድሎ ነጻነታችን ባጎናጸፈው ክብር፣ መደመምና መደነቅ ውስጥ ሆኖ የሚበርበት አውሮፕላን የሱዳንን የአየር ክልል አልፎ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ሲገባ በመስኮቱ አሻግሮ የኢትዮጵያን ተራሮችና ሽንተረሮች በጥልቅ የነጻነት ስሜት ውስጥ ኾኖ በምናብ እንደወጋቸው በዚሁ መጽሐፉ ውስጥ እንዲህ ይተርክልናል፡፡

          እነዚህ ተራሮችና ሸለቆዎች፣ ሜዳና ሸንተረሮች ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞች ወራሪውን የኢጣሊያን ሰራዊት ያንበረከኩበት፣ እነዚህ ተራሮች በኢትዮጵያን ጀግኖች አባቶቻችን ደምና አጥንት የተዋቡ … ዘመናትን ያስረጁ  የነጻነት ተስፋ ጎሕ ያበሰሩ- ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡ በእነዚህ አድማስ ጥግን የነኩ በሚመስሉ ተራሮች ለአፍሪካውያን፣ ለጥቁር ሕዝቦችና ነጻነታቸውን ለሚያፈቅሩ ለሰው ልጆች ኹሉ የተበሰረ የነጻነት ሕያው ድምፅ ገደል ማሚቶ ዛሬም ጎልቶ፣ ደምቆ የሚሰማበት ነው …!!

            እንግዲህ ይህ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ አውስትራሊያ፣ ከህንድ እስከ ቻይና ተሰማ የኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞቻችንን ተጋድሎ፣ ያጎናጸፉንን ክብርና ኩራት በዚህች አጭር ገጽ ለመተረክ የሚታሰብ አይደለም፡፡ የእነዚህ አባቶቻችን ውለታም ፈፅሞ በገንዘብ የሚለካ አይደለም፤ ምክንያቱም ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት ነውና የተከፈለበት!!

        እናም በዚህ የደም መሥዋዕትነት የነጻነት አየርን ለመተንፈስ የታደልን እኛ ልጆቻቸው ዛሬ ለጀግኖች አርበኞቻችን ያለንን ክብርና ፍቅር በተግባር ለመግለፅ ሁላችንም ታሪካዊ ግዴታና ሓላፊነት አለብን፡፡ ስለሆነም የእነዚህን ጀግኖቻችንን ሕያው ታሪካቸውንና ገድላቸውን ለትውልድ ይተላለፍ ዘንድ የኢትዮጵያ ጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማኅበር- ለጀግኖቻችን መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ለማስገነባት ያሰበውን ቤተ-መዘክር ለመገንባት ሁላችንም የበኩላችንን ድጋፍና እገዛ በማድረግ ለባለውለታዎቻችን ያለን ፍቅርና ክብር በተግባር ሊገለጽ ይገባል፡፡ አበቃሁ!!

ሰላም!!

    

No comments:

Post a Comment