ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Wednesday, November 22, 2017

ዘረኛ አትሁን ፤ በማንነትህ አትታበይ !!

         
          የነገስታት ልጅና ሰመርያ ለምትባለው ሀገር ንጉስ የነበረው 'አክዓብ' በክፋት ተነሳስቶ የድሃውን የናቡቴን የአትክልት ቦታ ለመውሰድ ተመኘ፡፡ ስጠኝ ብሎ ቢጠይቀውም ምስኪኑ ናቡቴ ርስቴንማ አልሰጥህም ብሎ መለሰለት፡፡ በዚህም ንግግር ንጉሱ ተቆጣ በጣም ተበሳጨ፡፡ ሚስቱ ኤልዛቤል ይህን ባየች ጊዜ መሬቱን እንዴት እንደምትወስደው እኔ መፍትሔ አለኝ ብላ በውሸት ወንጀል አስከስሳ የድሃውን የናቡቴን ርስት ቀሙት ፤ ተደብድቦም እንዲገደል አደረጉት፡፡ ብዙም ሳይቆይ ንጉስ አክዓብ እና ሚስቱንም የድሃው የናቡቴ አምላክ እግዚአብሔር ተበቀላቸው፡፡
በማንነህ ወይም በከበሩ ቤተሰቦችህ ወይም በዘር ማንዘሮችህ አትታበይ፣ የአንተ ያልሆነን ባለህ ዕውቀት ፣ ባለህ ገንዘብ ተመክተህ የኔ ካልሆነ አትበል፡፡ አይሁዳውያን የአብርሃም ዘርና ዘመዶች ነን ብለው ሲኮሩና ሲኮፈሱ ጌታችን "የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ስራ ባደረገችሁ ነበር " ብሎ እንደገሰፃቸው ቅዱስ መፅሐፉ ይነግረናል፡፡

         ብላቴናው ዳዊትን ብንወስድ ከድሆች ወገን የተገኘ እረኛ ነበር፡፡  ነገር ግን በጎነቱና ፃድቅነቱ ከፍ ያለ ክብርን አሰጥተው የከበረ ንጉስ አደረጉት ፡፡ የሰው ልጅ  ከምንም ቢነሳ የት መድረስ እንዳለበት የፈጠረው አምላክ ይወስን እንጂ ነገ ምን እንደምንሆን እንኳን የማናውቅ እኛ እንዴት ስለሌላ ለማውራት እንችላለን? ጥቁሩን ነጭ ፤ ነጩን ጥቁር የሚያደርግ ፈራጅ ዳኛ እያለ የኛ እንዲህ መሆን ምን ይባላል?


           ሌሎችን ከድሃ ወይም ከዝቅተኛ ደረጃ ካለው ቤተሰብ በመገኘታቸው እየናቅን ከከበሩ ሰዎች ወገኖች ነን ብለን መመካት ምን ይጠቅመናል? ሁላችን ከአንድ አባት አይደለንም? ወዳጆቼ የሰማያዊ ንጉስ የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን ምክንያት ፍፁም የከበርን ነን፡፡  እርሱ ለአንዳችን ሳይሆን ለሁላችን አባት ነው፡፡ በስጋ በሀብት በዕውቀት በከበሩ ዘመዶችህ ወይም ዘሮችህ ብትታበይ ግን "እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ. . .  የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ፡፡ " ከተባሉት ውስጥ ትሆናለህ፡፡

       እግዚአብሔር 'ሳዖል'ን ከታናሽና ከተናቁት  የእስራኤል ጎሳዎች ለእስራኤል ንጉስ አድርጎ እንደመረጠው ይታወቃል፡፡ የተናቀችውን እና የጋለሞታይቱን ልጅ ዮፍታሔን እስራኤልን እንዲመራና ከአሞናውያን እጅ እንዲያድናቸው አድርጓል፡፡ እንዲሁም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን የመረጠው ከልዑላን ፣ ከከበሩ ሰዎች መካከል ሳይሆን ከአሳ አጥማጆችና ካልተማሩ ከምስኪኖች መካከል ነው እንጂ ከጠቢባንና ባለፀጎች ከሆኑት አልነበረም፡፡ ስለዚህ በማንነትህ መታበይና መኩራት ከክርስትና በተቃራኒው መቆም ነው፡፡   የቀደመ መልካም ታሪካችን እና ሀገራዊ ስብዕናችን ዛሬን ሊያሻግረን ካልቻለ ምኑን እኛው ሆንን?  ወዳጆቼ ዘር የሚጠቅመው ለእህል ብቻ ነው ፤ ዘረኛ አትሁን!! አትታበይ!!

No comments:

Post a Comment