ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Wednesday, May 1, 2013

የይሁዳ አንበሳ

ከዘማሪ ‹ይልማ ሀይሉ› መዝሙር የተወሰደ

ህማሙን ልናገር አንደበት ቢያጥረኝም
መቼም ምንም ቋንቋ ለዚህ አይገኝም
ከረጅሙ ባጭር ከሰፊው በጠባብ
ስለከፈለልኝ ስለጌታ ላስብ
በጌቴ ሰማኔ ባታክልቱ ቦታ
ምድሪቷ ተሞልታ በታላቅ ፀጥታ
የአዳምን ልጅ ስቃይ በደሉን ሊሸከም
ጌታችን አዘነ ተጨነቀ በጣም
ሐዋርያት ደክመው ተኝተው ነበረ
ይሁዳ ከአይሁድ እንደተማከረ
ጭፍሮች እየመራ ጌታውን ሊያስገድል
የተሰራለትን ቸርነት ሳይቆጥር
ፋና እያበሩ ጭፍሮቹ ሲመጡ
ጌታን ሊያንገላቱት እንደዛ ሲቆጡ
የአምላኩን ጠላቶች መንገድ እየመራ
ይሁዳ ብቅ አለ ከቀያፋ ጋራ

Monday, April 29, 2013

ሆሣዕና በአርያም …!!!


ፀሐፊ ፡- ፍቅር ለይኩን፡፡
READ IN PDF


         ‹‹ሆሣዕና›› ቃሉ የዕብራይስጥ ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹አሁን አድን›› ማለት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ከፋሲካ በፊት ያለው እሁድ የሆሣዕና እሁድ በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ ዕለትም በቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው መዝሙር፣ ማኅሌቱ፣ ቅዳሴውና ማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት ዕለቱ በታላቅና እጅግ ደማቅ በሆነ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት የሚዘከርበት ነው፡፡ ይህ በዓል እጅግ በደማቅና ልብን በሚመስጥ መንፈሳዊ ሥርዓትና ድምቀት ከሚከበርባቸው ቅዱሳን ገዳማትና መካናት መካከል የአክሱሟ ርዕሰ አድባራት ጽዮን ማርያም እና በዚህ በአዲስ አበባችን ደግሞ የእንጦጦ ማርያም በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ሆሣዕና የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ወደ ኢሩሳሌም በታላቅ ድል የገባበት ዕለት ነው፡፡ አስቀድሞ በመጽሐፍ ቅዱስ በነቢዩ ዘካርያስ፡‹‹ለጽዮን ልጅ፡- እነሆ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያቱ ግልገል በውርንጭላይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት፡፡›› ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ፡፡ ጌታ፣ አምላክና መድኃኒት የሆነው ኢየሱስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡

Saturday, April 27, 2013

ፋሲካ፦ “ሥጋዊ ወመንፈሳዊ”


ፀሐፊ፡ ኤፍሬም እሸቴ  
  

(ኤፍሬም እሸቴ - ኢትዮጵያዊ)

         በኢትዮጵያውያን ዘንድ በታላቅ ሁኔታ ከሚከበሩት በዓላት መካከል ትንሣኤ ወይም ፋሲካ አንዱና ዋነኛው ነው። ሃይማኖታዊ ትርጓሜው እና ምንነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ባህላዊ አከባበሩ እና ምንነቱም ከኢትዮጵያውያን ባህላዊ ማንነት ጋር በጥልቅ የተያያዘ ነው። እንኳን በአገር ቤት ያለው በሰው አገር ያለነውም እንኳን ብንሆን እንደ አቅሚቲ የአገር ቤቱን መንፈስ በያዘ ሁኔታ እናከብራለን። ስለዚህ ፋሲካው መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን ሥጋዊ/ ባህላዊ አንድምታው ከፍ ያለ ነው ማለት ነው።
አለቃ ዘነብ የተባለው የአጼ ቴዎድሮስ ታሪክ ፀሐፊ አንባቢውን እያዋዛ የመከረበትንመጽሐፈ ጨዋታየተሰኘውን መጽሐፉንሥጋዊ ወመንፈሳዊ” (ሥጋዊ እና መንፈሳዊ) እንዳለው ስለ ፋሲካ ያለችኝን ወግ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ ብዬ ብከፍላት ኋላ ለሚከተለው ሐሳብ ጥሩ ገላጭ ይሆናል። ዘነብ ኢትዮጵያዊ ሲል ራሱን እንደገለጸ ኩረጃዬን ሙሉ ለማድረግ ኤፍሬም ኢትዮጵያዊ ብያለሁ፣ ቢያንስ ለዚህ ጽሑፍ። ኢትዮጵያዊነታችንን ከፍ አድርገን በክብር ልናሳይ የሚገባበት ዘመንም ስለሆነ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይሆንልኛል።
በጥንተ ታሪኩ ፋሲካ የሚጀምረው ከእስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነጻ የመውጣት ታሪክ ታሪክ ጋር ተያይዞ ነው። ሕዝበ እስራኤል ለረዥም ዘመን በግብጽ አገር በባርነት ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ በቤተ መንግሥቱ ያደገው ሙሴ መሪ ሆኗቸው ወደ አገራቸው ለመመለስ የጀመሩትን ጉዞ መሠረት ያደረገ በዓል ነው። ግብጻዊው ገዢ የሚያየውን ተአምራት ተቀብሎ ሕዝቡን ሊለቅ እና ነጻነታቸውን ሊመልስላቸው ባለመፍቀዱ ከተከሰተው ከባዱ ቅጣት ማለትም የግብጻውያኑ የበኩር ልጆች መቅሰፍታዊ ሞት ጋር ይገናኛል።

Wednesday, April 24, 2013

አገርን ፍለጋ

ፀሐፊ፡- ዮሴፍ ይልማ
yilmajoseph_1978@yahoo.com
የጨርቋን ጫፍ ጥለት፣
በአቧራ ነትቦ ባንዲራ ያለበት፡፡
ጭምድ አርጎ ይዞ ህፃኑ ጠየቀ
ግራ ቀኝ እያየ እየተሳቀቀ
አገራችሁ ሂዱሰዎቹ የሚሉን
የት ነው አገራችን?
ጥለትሽ ላይ ያለው ያገርሽ መለያ
የት ናት ኢትዮጵያ?
የት ጋር ተጀምራ የት ጋር ነውምታልቀው?
አፈርና ወንዙ ባህል ሐይማኖቱ የት ጋር ነውሚለየው?
እዚህ አይደለችም? ወደምንሄድበት እዚያ ናት ኢትዮጵያ?
ወጥተን ነበር እንዴ ከናታቻን ጉያ?
ውስጥ ሆነን ውጭ ነበርን?
እንደዚ ጨክነው አጣድፈዉሚገፉን
ወዴት ነው ምንሄደው?
ወዴት ናት አገሬ?

Thursday, April 4, 2013

ደብረ ዘይት፡- የዓለማችን ታሪክ ፍፃሜ ቅዱስ ተራራ


ፀሐፊ፡- በፍቅር ለይኩን

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ቀኖና መሠረት የዓብይ ጾም ወይም የሑዳዴ ጾም አምስተኛ ሳምንት ‹‹ደብረ ዘይት›› በመባል ይጠራል፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት አስተምህሮ የዓብይ ጾም ሳምንታት በሙሉ ከክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ታሪክ ጋር የተያያዘ የራሳቸው የሆነ ስያሜ አላቸው፡፡
የዚህ ስያሜ አመንጪም የ6ኛው መቶ ክ/ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቅና የዜማ ደራሲ የሆነው ቅዱስ ያሬድ እንደሆነ ነው የታሪክ ድርሳናት የሚመሰክሩት፡፡ ገና አውሮፓና እስያ በከፊል፣ አሜሪካና እንዲሁም የተቀረው የዓለማችን ክፍል በሙሉ ባልነበሩበትና ወንጌልን ባልሰሙበት በዛ የጥንት ዘመን ኢትዮጵያውያን ታላላቅ የሆኑና ዓለምን ዕፁብ ድንቅ ያሰኙ የሥነ ሕንጻ ጥበብና ክህሎት የተንጸባረቀባቸው ቤተ መቅደሶችን ገንብተው፣ መጽሐፍትን መርምረው፣ ዜማ ደርሰው፣ ቅኔ ፈጥረው ልዩ በሆነ መንፈሳዊ ሥርዓት ለረዥም ዘመናት አምላካቸውን ሲያመልኩ ቆይተዋል፡፡
አውሮፓ የሙዚቃ ኖታ ለመፍጠር አይደደለም ገና እንኳን ለማሰብ ባልደፈሩበት በጥንቱ ዘመን ቅዱስ ያሬድ ከሺሕ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ዜማ ከነምልክቱ ወይም ኖታው በቀመር ዛሬ ዓለም የሚደነቅበትን ሰማያዊና መንፈሳዊ ምሥጢር ያለበትን የቤተ ክርስቲያኒቱን አምልኮተ ሥርዓት መሠረት ለመጣል ችሏል፡፡