አውዳዓመት ሲመጣ ወዳጅ ከዘመድ ይጠያየቃል፡፡ ‹‹ እንኳን አደረሳችሁ›› ‹‹ እንኳን አብሮ አደረሰን›› ማለት ባህላችን ነው፡፡ እኔም እንኳን አደረሳችሁ ብያለሁ፡፡ እነሆ ታላቁ አውዳዓመት ፋሲካ ሊደርስልንበጣት የሚቆጠሩ ጥቂት ቀናት ቀርተውታል፡፡ በተለይ ያለፉትን ሁለቱን ወራት በፆምና በፀሎት ለፈፀሙ ለኢ.ኦ.ተ.ቤ አማኞች በዓሉ ከምንም በላይ ነው፡፡ ቀጣዮቹ ሳምንታትና ቀናት በበዓላት የተሞሉ ናቸው ስቅለት፣ ፋሲካ( ትንሳዔ)፣ ዳግማ ትንሳኤ በሽበሽ ነው፡፡ ለሁለት ወራትም ከብዙ ነገር የራቀው ሆድም ያገኘውን ያፍሳል፡፡ እዚህ ላይ ብዙ ግዜ የሚገርመኝ ፆም ከመግባቱ በፊት ያለው ግርግርና እንዲሁም ደግሞ ፆሙ ሲፈታ ያለው ውክቢያና ፈንጠዝያ ነው፡፡ መንደሮች ይደማምቃሉ፣ ቅምቀማ( መጠጫ) ቦታዎችም ከአፍ እስከ ገደብ ይሞላሉ፤ ግሮሰሪዎች፣ ስጋ መሸጫዎችንም እንዲሁ በስራ ይወጠራሉ፡፡ በዚህ ወቅት አንባቢ ማግኘት ይከብዳል፤ ቤተመፅሐፍቶቻችን ይቀዛቀዛሉ፣ጋዜጣ አንባቢ ብዙም አይገኝ፡፡ ‹‹ ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ›› እንደሚባለው ሁሉም በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ የተቻለውን ያደርጋል፡፡ ሲልም ካቅም በላይ የሆኑ ነገሮችን ከማድረግ ወደ ኋላ የሚል የለም፡፡ በዓል ነዋ! ይህ ነገራችን ቢቀረፍና እራሳችንን ሆነን በዓሉን ብናከብር መልካም ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነት ጣራ በነካበትና ሁሉ ነገር ውድ በሆነበት ሁኔታ ከአቅም ጋር የማይሄድ ወጪ ማድረግ ትርፉ ብስጭትና ማማረር ነው፡፡ ይህ መማረር ምናልባትም ከመንግስት አልፎ ‹ እግዚአብሔር›ንም ወደ ማማረር ሊያመጣ ይችላል፡፡ ይሄኔ ጉዳዩ ከበድ ይላል፡፡
በዓላት ሲመጡ ሌላው የሚነሳው ነገር የገበያ ነገር ነው፡፡ ገበያ ሲባል ደግሞ መርካቶ ነው ትዝ የሚለን፡፡ በበዓል ወቅት እግሮች ሁሉ ወደ መርካቶ ነው ቢባል ማጋገን ላይሆን ይችላል፡፡ የሚገርመው አንዳንዱ በተቃራኒው የሚሸምተው እንኳን ባይኖረው ግፊያውንና ግርግሩን ለመመልከት ወደ ቦታው ሄዶ ይጋፋል፡፡ ነገር ግን የበዛው ገበያተኛና ለበዓል የሚሆኑ ነገሮችን ለመሸመት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በተለይ ለበዓል ማድመቂያ ናቸው የተባሉት ዕቃዎች የሚሸጡባቸው ቦታዎች ደመቅመቅ ይላሉ፡፡ ዶሮ ተራ፣ በግ ተራ ፣ ሽንኩርት ተራ፣ አልባሳት መሸጫዎች(ሚሊተሪ ተራ፣ ዱባይ .. )፣ ቤት ማሳመር ዕቃዎች መሸጫ ሱቆች፣ ሁሉም ማለት ይቻላል ስራ ይበዛባቸዋል፡፡ አሁን አሁን መርካቶ እንደከዚህ ቀደሙ መሆኗ ቀርቶ በህንፃዎች እየተሞላች ነው፡፡ ይህም ግርግሩን በትንሹም ቢሆን ቢቀንሰውም መርካቶ አሁንም ያው መርካቶ ነው፡፡
ታዲያ ወደ ስፍራው የሚሄደው ሠው ቢያንስ አንድ ነገር ሳይገዛ አይመለስም፡፡ ‹‹መርካቶ መጥቶ . . . ምን ጠፍቶ ›› እንደሚባለው በጣም ርካሽ ዋጋ ካላቸው ዕቃ አንስቶ በጣም ውድ ሊባሉ እስከሚችሉ ዕቃዎች ድረስ ሁሉን ማግኘት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው እስካሁን ድረስ የመርካቶ ተወዳጅነት ያልቀነሰው፡፡ ነዳዴዎችም ቢሆኑ የበዓል ስራን ሁሌም እንዲኖርላቸው ይፈልጋሉ፡፡ በተለይ በዓል ሊደርስ ሲል ያለውን ሳምንት እንደ ሀብት ማካበቻ ነው የሚቆጥሩት፡፡ ለእነሱ በዚህ ሳምንት የሚያገኙት ትርፍ ከምንም በላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ገበያተኛው የታዘዘውንን የሚከፍልበት ወቅት ስለሆነ ፡፡ በመርካቶ ነጋዴዎች አጠራር ይህ ሳምንት ‹‹ ከማን አንሼ ›› ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡ ከማን አንሼ ሲባል አዲስ አበባ እስታዲየም ያለው የአንድ ክለብ ደጋፊዎች የሚቀመጡበት ቦታ ትዝ እንደሚላችሁ እገምታለሁ፡፡ ጉዳዩ ግን ከማን አንሼ ተብሎ በተለምዶ ከሚጠራው ቦታ እንዳሉት የእስታዲየም ደጋፊዎች አይዟችሁ በርቱ የሚባልበትና ቡድናቸውን የሚያበረታቱበት ሳይሆን በተቃራኒው ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የመርካቶ ነጋዴዎች መርካቶ የተገኘውን ሸማቹን ህዝብ ኪሱን ባዶ አድርጎና አራቁቶ መሸኘት ነው ስራቸው፡፡ ‹‹ እሺ. . .ትንሽ ቀንስ ›› ብሎ ነገር የለም፡፡
እዚህ ላይ ‹‹ከማን አንሼ ሳምንት›› ለምን ተባለ ከተባለ ምክንያቱ ይህ ነው፤ በዓላት ሲመጡ ብዙዎቻችን ያለ የሌለንን አውጥተን ኪሳችንንም አራቁተንም ከፍ ሲልም ብድር ወስደንም ቢሆን በዓሉን መክበርና ማሳለፍ እንፈልጋልን፡፡ ያልሆነውን መሆን እንፈልጋለን፤ ያልበላንን እናካለን ፡፡ ለምን ሲባል ጎረቤት የሚባል ጠላት ስላለ፡፡ ሞተን ነው ቆመን ከጎረቤት የምናንሰው! የሚል አጉል ፈሊጥ አለብን፡፡ ይህ ማንነትንና ምንነትን ያለማወቅ ችግር ደግሞ ለበዓል ነጋዴዎች ኪስ ማዳበሪያ ነው፡፡ በፊት 50 ብር ይገዛ የነበረውን ዕቃ 100 ብር ቢሉት ባይዋጥለትም ከመግዛት ወደ ኋላ አይልም ሲባል ቢግደረደርም ከመግዛት ወደ ኋላ አይልም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው የበዓል ሸማች ቤቱ ሞልቶና ምንም ሲጎድል ማየት አይፈልግም፡፡ ጎሎበትም መሳቀቅ አይፈልግም፡፡ ከአካባቢ፣ ከጎረቤት አንሶ መታየት ውርደት ነው፡፡ ይህን መጥፎ አስተሳሰባችን የገባቸው ደግሞ ነጋዴዎችም መጠቀሚያ አድርገውታል፡፡ ለዛውም ቆንጆ ስም ሰጥተውት፡፡ ‹‹ ከማን አንሼ ሳምንት!!›› ሁሉም ከማን አንሼ ብሎ ያዘዙትን ይከፍላቸዋል፡፡ ባዶውን ይመልሱታል፡፡ እዚህ ላይ ነጋዴን ለምን እንዲህ ታደርጋለህ ባይባልም የበዛ ስግብግብነት ግን መልካም አይደልም፡፡ አምላክም አይወደውም፡፡ ቢቻል ግን ይህንን ከማን አንሼ ስሜት አስወግደን በራሳችን ኮርተን ፣ ተመስጌን እያልን ብንኖር አውዳዓመቱም በሰላም ያልፋል እኛም ዕዳ ውስጥ አንዘፈቅም፡፡

መልካም የ‹‹ከማን አንሼ ሳምንት›› ለነጋዴዎች
መልካም በዓል ለሁላችሁም፡፡
No comments:
Post a Comment