ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Tuesday, June 19, 2012

ታዲያ እኔ ምንድር ነኝ? ማነኝ?

ፀሐፊ፡ በ ኢትዮጵያዊው ፍቅረ መድኅን 

አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ጠየቀ፡-
 ምንድር ነኝ? ማነኝ? መለሰም፡-
አንደኛ - የሥላሴ ፍጡር ፣ ሰው ነኝ፡፡
ሁለተኛ - ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡
ሦስተኛ፣ አራተኛ… እያለ ወደላይም ወደታችም፣ወደፊትም ወደኋላም፣ወደግራም ወደቀኝም ሊሳብ እና ሊቀጥል ይችላል፡፡ቁም ነገሩ ወደፊት ማራመዱ ፣ሰውን ኹሉ በሰውነት አንድነቱ መቀበሉ ነው፡፡እኔ ደግሞ እንደ ሰውነቴ በአገሬ ሆኜ ምንድር ነኝ? ማነኝ? ስል ጠየቅኹ፡፡ስለዛም ‘ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡’ አልኩ፡፡
 ቋንቋዬ ያ ወይንም ይሄ ሊኾን ይችላል፡፡

አባቴ፣እናቱ አባታቸው ኦሮሞ እናታቸው ደግሞ አማራ እንደኾኑ ይናገሩ እንደነበር ይናገራል፡፡አባቱ ደግሞ አባታቸው ትግሬ እናታቸው ሳሆ እንደነበሩ ሰምቷል፡፡
 እናቴ፣አባቷ በአባቱ ጉራጌ በእናቱ ደግሞ የሸዋ ኦሮሞ እንደኾነ ነግሯታል፡፡ እናቷ ደግሞ አባቷ አማራ እናቷ አገው እንደኾኑ ነግራታለች፡፡ኸረ ለኛም ለልጅ ልጆቿ ነግራናለች፡፡አዎ አስታውሳለሁ፡፡ነፍሱን ይማርና ያባቴንም አባት እንዲሁ፡፡ 
እኔ እንግዲህ ምንድር ነኝ? ማነኝ? 
እኔ ከላይ እንደተጠቀሰው እንደ ወላጆቼ አባባል ብቻ ብሄድ እንኳ ከአያቶቼ ሳልዘል፡-ኦሮሞ፣አማራ፣ጉራጌ፣ትግሬ፣አገው እና ሳሆ ነኝ ማለትም አይደል? ወደ ቅድመ አያቶቼ እና ከዚያም ባልፍማ እኔነቴ እየበዛ እየበዛ ዘመደ ብዙ መኾኔ አያጠያይቅም፡፡ተመስገን ነው ላወቀበት፡፡

 አሁን ባለ ትዳር ነኝ፡፡አግብቻለሁ፡፡ 
ሚስቴ ፣ አባቷ አባታቸው ከንባታ እናታቸው ደግሞ ሃድያ እንደኾኑ እንደነሯት ነግራኛለች፡፡እናቷ ደግሞ አባታቸው አማራ እናታቸው ደግሞ የሐረር ኦሮሞ እንደኾኑ እንደሚናገሩ ትናገራለች፡፡ልብ በሉልኝ ፣ለኹላችን ልብ ይስጠንና፡፡ በአካሌ፣በሚስቴም በኩል እንዲሁ ስንቆጥር ከአያቶቿ አላለፍንም እንጂ ጨምረን እንበዛ ነበር፡፡ነገሩ በዝተናል፡፡ በእውነትም ብዙ ነን ፡፡እንደው እንቁጠር ካልን እንጂ፡፡ ከምር እንቁጠር ብንልማ መች ተዘልቆ? ማሰቡም ያደክማል፡፡የምድር አሸዋ ይቆጠራል? እንደው ብዙ ስንኾን አንድ ነን ማለቱ ይበጀናል፡፡ 

ይቀጥላል፡-
 ባለቤቴ እና እኔ ልጆች ወልደናል፡፡ ልጆቻችን ምንድር ናቸው? የማን ናቸው? ለምታነቡቱ ቀላል የቤት ሥራ ሰጥቻለሁ፡፡ጥያቄው የወጣበትን ምንባብ እያነበቡ እንደመመለስ ዓይነት፡፡በእንግልጣሩ “ኦፕን ቡክ ቴስት” (open book test) እንደሚሉት መኾኑ ነው፡፡ 

ገና ይቀጥላል፡፡ እኔ ግን ላበቃ ነው፡፡ 
ባለቤቴ፣ፈጣሪ ይመስገን እና አራት እህቶች እና ወንድሞች አሏት፡፡ እኔ ደግሞ ስድስት ፡፡እኔ እና ባለቤቴ ስንጨመር ድምሩ 12 አልሆነም? ወንድሜ እቴ የምንባባለው፡፡ ኾኗል፡፡ኸረ ከዚያም ይበልጣል ፡፡ በጣም በጣም… ፡፡ ምክንያቱም ከእኔ እህቶች እና ወንድሞች አራቱ ከእርሷ ደግሞ ሦስቱ አግብተዋል ፡፡ እነዚሁ ደግሞ ኢትዮጵያን በአራቱም አቅጣጫ ተሳልመዋታል፡፡ኸረ በስምንቱም አቅጣጫ ፡፡ ከዚያም ደግሞ ይልቃል፡፡

 በሰሜን ፣ በደቡብ ፣ በምስራቅ ፣ በምዕራብ ፣
 በባሕር ፣ በመስዕ ፣ በሊባ ፣ በአዜብ ፣ የቀራቸው የለም ፡፡ “ ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የቀራቸው የለም፡፡አዳርሰውታል፡፡አዳርሰነዋል፡፡ከኹሉ ተጋብተናል፡፡ ተጋብተዋል፡፡” እያልኋችሁ እንደኾነ መቼም ለናንተ አይነገርም፡፡ “ ሠርገኛ ጤፍ ማለት ነን እኮ ” ነው ያሉት እኒያ ኢትዮጵያዊ የአምቦ ሰው?

ታዲያ እኔ ምንድር ነኝ? ማነኝ? 
አንደኛ - የሥላሴ ፍጡር ፣ ሰው ነኝ፡፡ ሁለተኛ - ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ሁሉንም ፡፡

4 comments:

  1. ETHIOPIAWI NEGN . Nice ideia keep it up BRO.

    ReplyDelete
  2. nice ideia push it up men,,,,,,,,,,,,,,

    ReplyDelete
  3. ya man nice ideia push it up ,,,,,,,,,,,,,,,,

    ReplyDelete
  4. እውነት ነው ያልከው ወዳጀ ።

    ReplyDelete