ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Wednesday, August 19, 2015

ደብረ ታቦር

       ደብር ማለት ተራራ ማለት ሲሆን ፤ ታቦር ደግሞ የተራራው ስም ነው፡፡ ቃሉ በአንድነት ሲነበብ ደብረ ታቦር ይሆናል፡፡ ይህም የታቦር  ተራራ የሚል ትርጉም ይሠጠናል፡፡ ደብረ ታቦር ከገሊላ ባሕር በምዕራባዊ በኩል 10 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ተራራ ሲሆን ከፍታው ከባሕር ወለል በላይ 572 ሜትር ይሆናል፡፡ ከተራራው አናት ላይ 100 ሜትር በ400 ሜትር ስፋት ያለው ደልዳላ መስክ ይገኛል፡፡ በቅዱስ ወንጌል እንደምናገኘው በዚህ ተራራ ጌታችን በዘመነ ሥጋዌው በሚያስተምርበት ወቅት ምስጢረ መንግስቱንና ብርሃነ መለኮቱን ገልጧል፡፡ በዚህ የተነሳ ይህ ተራራ በክርስትና ታሪክ ትልቅ ስፍራ አለው፡፡ በማቴ. 17፡ 1-13 ላይ የተፈጸመው ተዓምር እንዲህ ነበር፡፡
          ጌታችን አዕማድ ተብለው የሚጠሩ ሶስቱን ሐዋርያት ይዞ ወደ ተራራ ወጣ፤ በዚያም በፊታቸው ልብሱ እንደ በረዶ ነጭ ሆነ፡፡
መልኩም ተለወጠ፡፡ ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፤ በዚህ ጊዜ ሙሴ እና ኤልያስ ተገልጠው ማነጋገር ጀመሩ፡፡ ሙሴ በኦሪት ፊትህን አሳየኝ ብሎ የለመነውን ከሙታን አስነስቶ ስለ ክብሩ የቀናውን ኤልያስንም ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ ክብሩን አሳይቷቸዋል፡፡ ሙሴ በህገ ጋብቻ ያለፈ ነብይ ነው፡፡ ኤልያስ ደግሞ በድንግልና እና  በምነና ኖሮ ያረገ ነው፡፡ ሁለቱ መገለጣቸው ቤተክርስትያን በጋብቻ እንዲሁም በድንግልና (በምነና) የሚኖሩ አባቶች መኖሪያ እንደሆነች ለመግለፅ ነው፡፡ ከሶስቱ ሐዋርያት አንዱ ቅዱስ ጴጥሮስ በሁለተኛይቱ መልዕክት 2ኛ ጴጥ. 1፡ 17-18 ‹‹ ከከገናናው ክብር በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና እኛም በቅዱስ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ  ሰማን፡፡ ›› እንዳለ፤ በማቴ. 17፡4-5 ላይ ጌታ ሆይ በዚህ ለኛ መሆን መልካም ነው ብትወድስ በዚህ ሶስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንስራ አለ፡፡

 እዚህ ላይ ‹‹ ብትወድስ›› ያለው (ፈቃድ የጠየቀው) ከዚህ በፊት በቂሳርያ አይሁንብህ አይደረግብህ በማለቱ ተገስፆ ስለነበር ነው፡፡ ማቴ. 16-22፡፡
በዚህ ግዜ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው ከደመናውም በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ ተሰማ፡፡ ይህ ድምፅ አብ ስለ ልጁ የመሰከረበት ነበር፡፡ ሐዋርያት ይህን ድምፅ ሰምተው የጌታችንን መለኮታዊ ክብር አይተው በፊታቸው ወደቁ፡፡ እጅግም ፈርተው ነበር፤ ጌታችን ዳሰሰና አነሳቸው ፤ ተነሱ አትፍሩ አላቸው፡፡ በዚህ መልኩ አምላክነቱን ገለጠላቸው፡፡ የሕያው እግዚአብሔር ልጁ መሆኑን ምስጢር ተረዱ፡፡   ስለዚህ ደብረ ታቦር ምስጢረ መንግስቱንና ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት በዓል በመሆኑ በቤተክርስቲያናችን ከዘጠኙ የጌታችን ዐበይት በዓላት አንዱ ስለሆነ ነሐሴ 13 ቀን በዓሉን ታከብራለች፡፡
ደብረ ታቦር የቤተክርስቲያን ምሳሌ ነው ፡፡ ከምሳሌዎቹ በጥቂቱ ስናነሳ፡-


  1. ደብረ ታቦር ድል ለማድረግ የሚመች ተራራ ነው፡፡ አካባቢው ከፍ ያለና ከታች ያሉትን ሸለቆዎች ሁሉ ለመቆጣጠር የሚመች ስለሆነ ነገስታቱ ለጦርነት ይመርጡታል፤ በጦርነትም ታቦርን የያዘ ድል ያደርግ ነበር፡፡ ለምሳሌ ፡- ዲቦራና ባርቅ ሲሣራን ድል ያደረጉት ይህንን ተራራ በመያዛቸው ነውሀ፤ መሳ. 4፡7 ታሪኩን ስናነብ እንደምናገኘው ከጦርነቱ በፊት ነቢይቱ ዲቦራ ባርቅን ጠርታ ይህንኑ ነግራዋለች ፤በዚህ አባባሏ ባርቅ ድል ለማድረግ ወደ ታቦር ተራራ መውጣት እንደነበረበት እንረዳለን፡፡ በመሆኑም ባርቅ ይህን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ሰምቶ ወደ ታቦር ወጣ፡፡ ከዚያም ኃይልን አግኝቶ በመውረድ ሲሣራን ድል አደረገ፡፡  እንደዚህ ቤተክርስቲያን የደብረ ታቦር ምሳሌ በመሆኗ ድል ማድረጊያ ቦታ ናት፡፡ ወደ እርሷ የመጣ ኃይል አግኝቶ ጠላቱን ያሸንፋል፡፡ በእግዚአብሔር ኃይል በፆምና በፀሎት መንፈሳዊ ተግባራትንም በማድረግ ሰይጣንን ድል ያደርጋል፡፡
  2. ደብረ ታቦር 572 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን ፤ ከዚህ የተነሳ ወደ ላይ ሲወጡት አስቸጋሪ ዳገት ሆኖ ከወጡት በኋላ አናቱ ላይ ሲደረስ መስክ አለ፡፡ በዚህ የተነሳ ወደዚህ ተራራ የሚወጣ ሰው ሁሉ ከብዙ ድካም በኋላ ደልዳላውን ስፍራ (መስክ) ሲመለከት ደስ ይሰኛል፡፡ ድካሙንም ይረሳል፡፡ ቤተክርስቲያንም የደብረ ታቦር ታራረ ምሳሌ በመሆኗ ለጊዜው ሲቀርቧት ዳገት ትሆናለች፡፡ ፁሙ ፀልዩ ስገዱ መፅውቱ ስለምትል ታስፈራለች ፤ ከቀረቧት በኋላ ግን በውስጧ መኖር ሲጀምሩ ሰላም ትሰጣለች ፤ ፍፃሜዋ ደስ የሚያሰኝ እና ሰላማዊ ስለሆነች ታሳርፋለች፡፡ ጌታችን በወንጌሉ፡- ዩሐ. 14-27 ሰላሜን እተውላችኋለሁ፡፡ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ እኔየምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም የሚለን ለዚህ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ደብረ ታቦር የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ይህን ተረድተን ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ መሆን ለኛ መልካም ነው እንዳለ እኛም ይህን ቃል እንድንፈፅም ከታቦር ቤተክርስቲያን ላንርቅ ቃል እንግባ፡፡


በታላቁ ገዳም በደብረ ሊባኖስ የደብረ ታቦር በዓል በልዩ ሁኔታ ይከበራል፡፡ በሰዓታቱ ፣ በማዕሌቱ ፣ በቅዳሴው ፣ በወንጌል አገልግሎት እንዲሁም የገዳሙ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ይዘክሩታል፤ የሚማሩት ትምህርት እንዲገለፅላቸው ፈጣሪያቸውን ይማፀኑበታል፡፡

የደብረ ታቦር ምስጢር በእኛም ሕይወትና በልቦናችን ብርሃኑን እንዲያበራልን ወደቤተክርሰቲያን መቅረብ ይገባናል፡፡ ለዚህም እግዚአብሔር አምላክ ይርዳን ፡፡ አሜን!!!
(ምንጭ፡- ፊልጶስ በሐምሌ 
በመምህር አባ ወ/ገብርኤል ገ/ኢየሱስ እና ዲያቆን አባ ገብረ ጻድቅ ነገ )  

1 comment: