ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Sunday, July 1, 2012

ዘረኝነት ኢ-ክርስቲያናዊ የሆነ ተዛማችና ክፉ ወረርሽኝ ነው፡፡


ፀሐፊ፡ ፍቅር ለይኩን፡፡

         ለዚህ ጹሑፍ መነሻ የሆነኝ በደጀ ብርሃን ብሎግ ላይ የተስተናገደው ናኦድ ቤተ-ሥላሴ በዘረኝነት/በጎጠኝነት ዙሪያ ያስነበበው ምሬት የተቀላቀለበት አጭር መጣጥፍ ነው፡፡ የ1997ቱን ድኅረ ምርጫን ተከትሎ በሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ደም አፋሳሽ ግጭትና ቀውስ ምክንያት እስከ አሁን ድረስ ምክንያቱ ባልገባኝና ምላሽ በላገኘሁበት በወቅቱ በነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከኢትዮጵያውያን የረጅም ዘመን የማኅበራዊ ኑሮና የአብሮነት እሴቶችና ዋጋዎች በተቃረነ መልኩ «ከትግራውያን ጋር ለቅሶ አትደራረሱ እሳትም አትጫጫሩ…» እስከሚል የዘለቀ መመሪያ መሰል አዋጅ ተላልፎ ነበር፡፡
እናም በዚሁ አዋጅ ጦስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለን የክፍል ጓደኛዬ የሆነች ከአክሱም የመጣች ወጣት ሴት ለሦስት ዓመታት በቆየችበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማደሪያ ክፍሏ ያሉ ከሌሎች ክልሎች የመጡ ጓደኞቿ እንዳገለሏትና ሰላምታ እንኳን እንደነፈጓት የነገረችኝ እንባዋ በሁለቱ ጉንጮቿ እየወረዱ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንድ እና ግልጽ ነው የትግራይ ልጅ በመሆኗ ነበር፡፡ ዘረኝነት ባለ ብዙ መልክ ነው መገለጫውም የዛኑ ያህል ደግሞ ውስብስብና ባለ ብዙ ኅብር ነው፡፡
በዘረኝነት ዙሪያ ብዙ አከራካሪ የሆኑ መጽሐፍቶችና የምርምር ጥናት ጹሑፎች ለንባብ በቅተዋል፡፡ የሰው ልጆችን አመጣጥና ታሪክ በሚያጠኑ ሰዎች መካከልም ይኸው የዘር ጉዳይ ብዙ አወዛጋቢ ክርክሮችንና አለመግባባቶችን ያስነሳ ጉዳይ ነው፡፡ ወደዛ ሰፊ ክርክርና ሙግት ለመግባት አልሻም፡፡ ይሁንና ለበርካታ መቶ ዓመታት በዚሁ ዘረኝነት ጠንቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካንና አፍሪካውያንን ላይ ታሪክ በጥቁር መዝገቡ የከተበው ዘግናኝና አሳፋሪ ስደት፣ ሞትና እልቂት በአፍሪካውያን ሕዝቦች ላይ ደርሷል፣ አሁንም በምድራችን የዚሁ የዘረኝነት ጦስ ደፋው ገና ተከፍሎ ያበቃ አይመስልም፡፡

«አፍሪካውያን ወይም በአጠቃላይ «ጥቁሮች» ከሰው ዘር ሊያስመድባቸው የሚችል ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበረሰባዊ መሰረት የላቸውም» የሚልና አንዳንድ አውሮፓዊ የስነ ሰብእ ተመራማሪዎችም (Anthropologists) «የጥቁር ዝርያ በአጠቃላይ ሰው የመሆን እድገቱ የተገታበት በሰውና በእንሳሳ መካከል ያለ ፍጥረት ነው…» እስከሚል ድፍረት የሄደ ገለጻቸውን በዳጎስ መጻሕፍቶቻቸው አስነብበውናል፡፡ ከዛም ባለፈ ብዙ ጥቁር አፍሪካውያን ወገኖቻችን አውሮፓ ድረስ ተጓጉዘው በትላልቅ ቤተ መዘክሮችና የእንሰሳት መጠበቂያ ዙዎች ውስጥ በሕይወት እንዳሉ እንዲጎበኙ እንደ ዱር አራዊት ለእይታ የቀረቡበት አሳፋሪ ታሪክም በምድራችን ላይ ሆኗል፡፡
በዘረኝነት ጠንቅ በዓለማችን ላይ የደረሱትን አሰቃቂ እልቂቶች ሁሉ መጥቀስ ባይቻልም በ፳ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ በጀርመኑ አምባ ገነን በአዶልፍ ሂትለር ምክንያት ፮ ሚሊዮን በሚጠጉ አይሁዳውይንና ዝርያ አይሁዳውያን ላይ የደረሰው እልቂት ግን በዘመናችን ተወዳዳሪና አቻ ያልተገኘለት የዘር ማጥፋት ዘመቻ ነው፡፡ አዶልፍ ሂትለር ጀርመናውያን ልዩና ምርጥና ዘር (Arians) ስለሆኑ ዓለምን የማስተዳደር ስልጣንም ሆነ ብቃት ያላቸው ብቸኛ የዓለማችን ዝርያዎች ጀርመናውያን መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን ከጀርመን ዝርያ ውጭ ያሉ የሰው ልጅ ዝርያዎች ሁሉ ግን ለዓለማችን ርግማንና መዓት ስለሆኑ ከምድረ ገጽ መጥፋት እንዳለባቸው በማመኑና በመወሰኑ የዘር ማጥፋት ዘመቻውን ከአይሁዳውያን ጀመረ፡፡ አይሁዳውያን እንደ አይጥ ከያሉበትና ከተሸሸጉበት እየታደኑ በዘግናኝ ሁኔታ እንዲያልቁ ሆኑ፡፡ ዓለማችን በሰሰቀቀን እና በእፍረት አንገቷን ደፋች፡፡ የሆሎካስቱ እልቂት በእርግጥም እጅግ ዘግኛኝ ነበር፡፡
በእኛው በአፍሪካ ምድር በ፳፩ኛው መቶ ክ/ዘመን በሩዋንዳውያኑ ቱትሲና ሁትሱ መካከል የደረሰው የዘር ማጥፋት ዘመቻና የዘረኝነት ጦስ የወለደው የእርስ በርስ እልቂት ዓለምን ጉድ ያሰኘና ወደ ስምንት መቶ ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ያለቁበት አሰቃቂ የቅርብ ታሪክ ነው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ እልቂቶች ጀርባ ደግሞ የዘረኝነትን ጎማ ከሚያሽከረክሩት መካከል የቆዳ ቀለም፣ ዝርያ፣ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባሕል፣ አንዳንዴም ሃይማኖት በአብዛኛው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በደጀ ብርሃን ብሎግ ለንባብ የበቃው የናኦድ የዘረኝነት ጠንቅ መጣጥፍ በኢትዮጵያውያን መካከል በእኛ ዘመን ብዙ ጥፋቶችን እያደረሰና ለብዙ ዘመናት የቆየቱን አብሮ የመኖር የማኅበረሰባችን ዋጋዎችና እሴቶች የሚንድ የዘረኝነት ወረርሽኝ በሕዝባችን መካከል እየተስፋፋ እንዳለና ወዴት እየሄድን ነው የሚል መልእክት የተንጸባረቀበት መጣጥፍ ነው፡፡
በእርግጥ ሰው መሰሉን የመፈለግና ወደመሰሉ የመጠጋት ባሕርይው ተፈጥሮአዊ ነው ግን ይህ ተፈጥሮአዊ የሆነ መፈላለግና መሳሳብ ስህተት የሚሆነው ከመጠን አልፎ ከራስ ውጭ ለሌሎች በቋንቋ፣ በውልደትና በባሕል…ወዘተ የማይመስሉንን ሰዎች ማግለል፣ መናቅና ማናናቅ ሲጀምርና በግልጽም ሆነ በስውር ጥላቻንና ትንኮሳን ማድረግ ውስት ሲገባ ያን ጊዜ አደጋ ውስጥ እንዳለን ማሳያ ነው፡፡ ሰው በቋንቋ የሚግባባውን ባሕሉንና ሃይማኖቱን የሚጋራው ሰው ሆነ ቡድን ሲያገኝ ወደዛ ልቡ የመሸፈቱ ነገር ተፈጥሮአዊውና ሰዋዊ ባሕርይ ስለመሆኑ ማንም የማይክደው ሐቅ ነው፡፡ ክፋቱ በእኛ ዘመን እየሆነ ያለው ግን ከእኔ ወይም ከእኛ ውጭ ያሉትን ማንኳሰስና ወገንተኝነት የሚንጸባረቅበት የዘረኝነት/የጎጠኝነት/ የመንደረተኝነት አካሄድን በዘመናችን እየታዘብን መሆኑ ነው፡፡
በሕዝባችን መሀል እየተስፋፋ ያለው የዘረኝነት/የጎጠኝነት/የወንዘኝነት ወረርሽኝና ልዩነቶቻችንን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሰፋ ያለው ቋንቋቸውን፣ ባሕላቸውንና የተወለዱበትን ብሔር እንደ ልዩ መገለጫና ኩራት እያደረጉ ይህን ስሜታቸውን በንግግራቸውና በስራቸው እየገለጹ ያሉ ሰዎች መበራከታቸው ነው፡፡ ለመሆኑ በእኛ ትውልድ እንዲህ አበያ በሬ እንደገባበት በረት በቋንቋ፣ በብሔር አንዳንዴም በሃይማኖት ምክንያት እያተራመሰን ያለው «የዘረኝነት/የጎጠኝነት/የመንደርተኝነት» ጠንቅ ምን መነሻና መድረሻ አለው ከመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ከሳይንስ አንጻር ያለው እውነታስ ምን ይመስላል፡፡
ከመጽሐፍ ቅዱስ ወይም ከክርስትና ሕይወት አንጻር «ዘረኝነት» ምን መሰረት አለው፡፡ አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ/ክርስትና ራሱ ዘረኛ ነው እስከማለት ድፍረት የደረሱበትን ንባብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይጠቅሳሉ፡፡ ለዚህም መከራከሪያ አሳብ ሲያቀርቡ «እግዚአብሔር ከሰው ዘር አይሁዳውያንን ከሰውም አብርሃምን ለይቶ መርጧል» በማለት ክርክር ያነሳሉ፡፡ እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ደረቅ ንባቦችንም በመጥቀስ ከዚህ የበለጠ ሊጠቀስ የሚችል ምን ዓይነት ዘረኝነት አካሄድ ሊኖር ይችላል በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ስለዚህ ዘረኝነት እራሱ መንፈሳዊ/መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ያለው ያለና ሊኖር የሚገባው መቼም ልናስወግደው የማይቻል በተፈጥሮአችን አብሮን ያለ እውነት ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡
በእኔ እሳቤ እውነታው ግን እነዚህ ሰዎች እንደሚከራከሩት ሳይሆን የእግዚአብሔር ምርጫ ከዘር ወይም ከአንድ ማኅበረሰብ/ብሔርና ቤተሰብ እሳቤ በጣም የራቀ መሆኑንና ዋናው እግዚአብሔር አምላክ ትኩረት ያደረገበት እውነታ በታሪክ ውስጥ እርሱን ለመፈለግ የቀና ልብ ያላቸውን ሕዝቦችም ሆነ ግለሰቦች የመጥራትና የመምረጥ ሁኔታ እንዳለ ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን፡፡ የአብርሃም እግዚአብሔርን የመፈለግ ጽኑ ፍላጎትም ከዘሩ፣ ከወገኖቹና ከቤተሰቡ ስለመመረጡ ዐቢይ ምክንያት እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንትም ሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ያለው ስለ አብርሃም ፈጣሪን ስለመፈለግ ያሳየውን ጽኑ ፍላጎት በትውፊት ጭምር እውነታውን አጠናክረው ይተርኩልናል፡፡ አብርሃም ከጣኦት አምላኪ ቤተሰቡ አፈንግጦ በፈጣሪን ፍለጋ ጉዞው «አምላከ ጸሐይ ተናበበኒ» በማለት እውነተኛውን አምላክ የመፈለግ ጽኑ ፍላጎቱን አሳይቷል በማለት ይተረካል በእኛ ቤተ ክርስቲያን አባቶች፡፡
የእነዚህን መጽሐፍ ቅዱስን ዘረኛ ነው በማለት የሚወቅሱ ሰዎችን ክርክር/እሳቤ ከንቱ የሚያደርግ ሌላ እውነታ ደግሞ እስቲ እንይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘር ውስጥ ከአሕዛብ ወገን የሆነቸው ሞዓባዊቷ ሩት መጠቀሷን ልብ ይሏል፡፡ ይህች አሕዛብ ሴት አምላክሽ አምላኬ ሕዝብሽ ሕዝቤ ይሆናል በማለት ነበር ከአንቺ ጋር ከሞት በቀር ምንም አይለየን በማለት አይሁዳዊቷን ኖኃሚንን በመከተል ከወገኗ እና ከሕዝቧ ተለይታ ወደ ቤተልሄም የመጣቸው፡፡ እግዚአብሔር ሰዎችን ሆነ ሕዝቦችን የለየበት ወይም የመረጠበት ዋናው ነገር እግዚአብሔርን የመፈለግ ቅን ልብ እንጂ አንዳንዶች እንደሚሉት የዘር ወይም የአንድ ብሔር ጉዳይ ሆኖ አይደለም፡፡
በአዲስ ኪዳን ዘመንም ቢሆን በአይሁዳውያንና በአሕዛብ መካከል የነበረው ልዩነት መነሻ ያደረገው የዘር ጉዳይ ሳይሆን የባሕልና የልማድ ሁናቴ እንደነበረ በግልጽ እናያለን፡፡ ይህም በአሕዛብ መካከል ይደረግ የነበረው ክፋትና አመጻ የሞላበት ልምምድና ስርዓቶች እንደነበሩ በግልጽ እናያለን፡፡ ጳውሎስንና ጴጥሮስን እስኪከፋፉ ድርስ ልዩነትን የፈጠባቸው በአይሁድና በአሕዛብ መካከል የነበረው የዘርኝነት ጉዳይ ወይም የዘር ልዩነት ሳይሆን ሥርዓት፣ ትውፊት፣ የአባቶቻቸው ወግና ባሕል የፈጠረው ልዩነት ነበር፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በሰው ልጆች መካከል ታላቅ ልዩነትን ፈጥሮ የነበረውን ጥላቻና መከፋፈል ክርስቶስ ኢየሱስ የሰው ልጆች የገነቡትን የዘረኝነት ግንብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማፍረስ የኃጢአትን ዋጋ በመክፈል በራሱ አንድ አዲስ ሰውን ፈጥሮአል፡፡ በዛ አዲስ ሕይወት ውስጥ ላሉ ሰዎች ደግሞ አይሁድ፣ አሕዛብ፣ ግሪክ፣ ባሪያ ጨዋ… የሚባል ልዩነት የለም፡፡ ክርስቶስ ሁሉን ነው በሁሉም ነውና፡፡
ጌታችንና መዽኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘራቸውና በባሕላቸው ምክንያት የተናቁትንና የተገፉትን ሰዎች ቀርቦ በፍቅር በማነጋገርና ለችግራቸው መፍትሔ በመሆን በአይሁዳውያን ዘንድ እጅግ ከተናቁትና ከተጠሉት ሕዝቦች መካከል ሰማርይቷን ሴት ተቀብሎ በማነጋገር ያን ሰዎች የገነቡትን የልዩነት ግድግዳ አፍርሶ የልቡን ጥልቅ ፍቅርና ትህትና ያለ ምንም ልዩነት አሳይቷል፡፡
አሳዛኙ እውነታ ይህ በክርስቶስ ኢየሱስ የተናደ የልዩነት ግድግዳ ቋንቋን፣ የተወለዱበትን ብሔር መነሻ ያደረጉ የዘረኝነት ውርሶችና ቁርሽዎች በዚህ ዘመን ከፖለቲካውና ከዓለማዊው መድረክ ሸርተት ብለው ወጥተው ወደ እምነት ተቋማቶቻችን ውስጥ ሰተት ብለው ገብተው ይኸው ቁምስቅላችን እያሳየን ነው፡፡ ይህ የዘረኝነት መንፈስ መንፈሳዊው ሰፈር ገብቶ አገርን ሲያተራምስና ወገንን ሲያቆስልና አንገትን ሲያስደፋ ማየት መርገምት ይመስለኛል፡፡ ይህ የዘረኝነት/የወንዘኝነት/የጎጥኝነት/የመንደርተኝነት አባዜ የምድራዊውን ሕይወት ክልል አልፎ በቤተ እምነቶች ጎልቶ ሲታይ ደግሞ የሚያሳፍር ብቻ ሳይሆን የሚያሳምም ነው፡፡
በመጨረሻም በጹሑፌ ማጠቃለያ የዘር/የዘረኝነትን ጉዳይ በተመለከተ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ እየወጡ ያሉ ጥናቶችና የምርምር ጹሑፎች የሚነግሩን ሐቅ ቢኖር ግን ዘር/ዘርን በተመለከተ ያሉ እሳቤዎችና ትንታኔዎች ሁሉ ምንም ሳይንሳዊ መሰረት የሌላቸው የኅብረተሰብ ፈጠራ ውጤት መሆናቸውን በግልጽ እየተናገሩ ነው፡፡ በሳይንስ በዲ.ኤን.ኤ ዘርፍ እየተደረጉ ያሉ ጥናቶችም ስለ ዘር የነበሩና የቆዩ አስተሳሰቦች እውነታ እንደሌላቸው በማሳየት ላይ ናቸው፡፡ Race the Power of an Illusion በሚል ጥናታዊ ጹሑፍ ያቀረቡ አንድ በኒዮርክ ዩኒቨርስቲ የሚገኙ ፕሮፌሰር ስለዚሁ ስለ ዘር ጉዳይ ጥናት ባተቱበት መጣጥፋቸው እንደገለጹት፡-
«Contemporary science is now challenging the very concept of race. Anthropologists who have studied race and genetic composition have determined that no single gene exists that can justify categorizing ourselves according to "races."»
ይህ ሳይንሳዊ ሐቅ የሚያረጋግጥልን ነገር ቢኖር መጽሐፍ ቅዱስ ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት የተናገረውን እውነት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ ምዕ ፲፯ ላይ ለግሪካውያን እንደተናገረው፡- ምናልባት እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ ሰዎችን ከአንድ ወገን ፈጠረ፡፡  ዛሬ ዛሬ ዘርን መነሻ አድርገው የሚናፈሱ እሳቤዎች ምንም ዓይነት ሳይንሳዊው ሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ እንደሌላቸው በግልጽና በሰፊው እየተነገረና እየተጻፈ ነው፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ክቡር ደም ከወገን፣ ከቋንቋ፣ ከሕዝብ፣ ከነገድ ሁሉ ተዋጅተን አዲስ መንፈሳዊ ቋንቋና ሰማያዊ ዜግነትን የተቀበልን ሕዝቦች ሆነናል፡፡ ይህ ማንነት ደግሞ ከምንምና ከማንም ጋር የሚወዳደር አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዘመኑ ለነበሩ ክርስቲያኖች እጅግ ስለሚኩራሩበትና ሌሎችን ስለሚንቁበት አይሁዳዊ ማንነታቸው ሲናገር ከዚህ ሁሉ በላይ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን እንጂ በዚህ መኩራትና መኩራራት ቢያስፈልግ ከእርሱ በላይ ማንም እንደማይኖር ከገለጸ በኋላ ይህን ሁሉ ምድራዊ ማንነቱን ስለ ክርስቶስ እውነት ረብ የለሽ አድርጎ መቁጠሩንና ነገር ግን ሚበልጠውንና በእጅጉ የሚሻለውን ሰማያዊ ማንነትና መንፈሳዊ ዜግነት በመቀበል ሰዎች በአዲስ እና ሰማያዊ ሕይወት እየኖሩ ዘንድ የሚያተጋቸው፡፡
እንደ ክርስቲያን ወይም እንደ መንፈሳዊ ሰው ሁላችንም በክርስቶስ ኢየሱስ አንድና ሰማያዊ ዜጋ የሆንበትን አዲስ ሕይወት እየኖርንና ለሌሎችም ይህን ሕይወት እያካፈልን እንድንኖር የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር እንዲረዳን በመመኘት ልሰናበት፡፡

ሰላም! ሻሎም!

8 comments:

  1. wow Really i appreciet you ! i have no words to but i realy thanks you and God bless you.
    .......
    From Sweden

    ReplyDelete
  2. Good view...well explained keep it up!!!

    ReplyDelete
  3. thank you, God bless our country!!!!!!!!!!!!!!

    ReplyDelete
  4. betam yemiamir tsihuf dink new melkam bilehal

    ReplyDelete
  5. behagerachen laye eyetaye yalewen ye zeragnenat yehaymanot menakore egeziyabeher kehagerachen yaswetalen
    tebaberanena tekebaberan hagerachenen kerehabe kedenkurena alakken bealem mesale enhun ersebers anenakes abatoch enatoch yakoyulenen hagerachenen anafeeres egna kaletabekenat manem aykomelatem hagerachen beselam betenore yemegemeriy tetekamiowch egna nane
    behaymanote ena yaplos ena degmoyekefa nagn atebelu kerstose selhulu hatyat nawyemotaw
    bezeragenate ena ayhudawi ena samerawi atebelusewen yemiyasedkaw serwna haymanotu naw

    ReplyDelete
  6. ethnicity is a serious problem in ethiopia now a days that need to be addressed timely
    but where did u get the statment that says opposition said to segregate tigreans that is completlety false that must be corrected..never never they said that instead eprdf' not tgreans.
    eprdf is organization but tigre is race
    .so make distinction b/n z two.there may be be false interprtation as EPRDF=TPLF.BUT THEY DIDNT SAY ANYTHING ABOUT TIGREANS

    ReplyDelete
    Replies
    1. hake nawe kale hiwet yasemaln thank u

      Delete
  7. kale hiwet yasemalen tsegawun yabzalih

    ReplyDelete