ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Tuesday, July 24, 2012

‹‹ ኦፒየም ›› በየዓይነቱ በኢትዮጵያ።


ምድርን ሁሉ ካሰከረች የወርቅ ፅዋ መጎንጨት ይብቃ፡፡
ከመልካሙ መንገድ እንዳይወጣ ቅዱሳን መጻሕፍት ለኢትዮጵያዊው ያቆዩለት ማስጠንቀቂያ ፥

የእግዚአብሔርን መንገድ ብትተው፥ 

  •    የማታውቀው ጠላት የምድርህንና የድካምህን አዝመራ ይበላል:: [']
  •    በሬህ በፊትህ ይታረዳል፥ ከእርሱም አትበላም፤ አህያህ ከእጅህ በግድ ይወሰዳል፥ ወደ አንተም አይመለስም፤ በግህ ለጠላቶችህ ትሰጣለች፥ የሚረዳህም አታገኝም።[']
ተመክሮ፥ ምእራባውያን እና ኦፒየም በቻይና።

     አንድ የማውቀው የእስያ ሰው ሆንግ ኮንግ ዘመዶቹን ጠይቆ እንደተመለሰ አገኘሁትና ስንጨዋወት "አንተ የምን አገር ሰው ነው የምትባለው?" ብየ ጠየቅሁት። እሱም "የቻይና" አለኝ። አከታትሎም ስለ ሆንግ ኮንግ ታሪክ አጫወተኝ። በምእራባውያን የተጻፈ ታሪክ በማንበብ ስለ ቻይና የተወሰነ እውቀት ቢኖረኝም፡ ስለ ሆንግ ኮንግ ልዩ አስተዳደርና፣ እንዴት  ከቻይና ተነጥላ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛትነት እንደኖረች ሲያጫውተኝ፡ የሆንግ ኮንግን እና የቻይናን ታሪክ ከቻይና ሰው በመስማቴ ተመስጨ በጥሞና አዳመጥኩት። እንዲህም አለኝ፥


"
ቻይና በጣም ሰፊ አገር ነበረች፣ የማታመርተውም ምርት አልነበረም። ሁሉም ማእድን፣ ቅመማቅመምና ቁሳቁስ ተሟልቶ ይገኝባት ነበር። ብዙ አይነት ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች የሚኖሩባትና ብዙ ምርቶች የሚመረቱባት ትልቅ አገር ስለነበረች ከሌላ ከውጭ አገር የምትፈልገው ትርፍ ነገር አልነበረም።

"
ምእራባውያን በተለይ ደግሞ እንግሊዞችና ፈረንሳዮች እነሱ ለቻይና ማቅረብ የሚችሉት ተፈላጊ ምርት ባይኖራቸውም ቻይና ውስጥ የሚገኙ ብዙ  ጥሬ ሃብቶችን ይፈልጉ ነበር። ሆኖም ግን ጥሬ እቃዎችን ወይንም ደግሞ እንደ ሻይ፣ ሃርና፣ አንጸባራቂ ሸክላን የሚመስሉ  የቻይና ምርቶችን  ለማግኜት  ከወርቅ ቀጥሎ ውድ የሆነውን ብር እያቀረቡ መገብየት ውድ ሆነባቸው።   ጥሬ እቃዎቿንም እንደፈለጉ  ማግኘት ይችሉ ዘንድ ቻይና በሮቿን ከፍት እንድታደርግላቸው ምእራባውያን ቢሞክሩም ቻይና ፈቃደኛ አልሆነችም። በዚህ ጊዜ እንግሊዞች ቻይናን ለመከፋፈልና ቻይናዎችንም ለማንበርከክ ታጥቀው ተነሱ። ለዚህም ግባቸው ብዙ ልዩ ልዩ የተንኮል እርሾዎችን ጠነሰሱ። ከነዚህ እርሾዎች አንዱ ኦፒየም ነው። እንግሊዞች ኦፒየም የሚባል አደንዣዥ እፅ እያዘጋጁ በድብቅ ወደ ቻይና ማስገባት ጀመሩ። የቻይናም መንግሥት ብዙ የቻይና ሰዎች በኦፒየም እፅ እየደነዘዙና አገርን የሚያደኸዩ ብኩኖች እየሆኑ መምጣታቸውን በማየት ይህ አደንዛዥ እፅ ወደ ቻይና እንዳይገባ መቆጣጠር ጀመረ።  በየድንበሩም ሁሉ የኦፒየም ቁጥጥር ተጠናክረ። በዚህ ጊዜ የቻይና መንግሥት ባደረገው ክትትል ተደብቆ የገባ በብዙ ሚሊዮን ፓውንድ የሚገመት  የኦፒየም አደንዛዥ እጽ አገኘና ሰብስቦ አቃጠለው።

"
ወደ ቻይና በድብቅ ያስገቡት አደንዛዥ የኦፒየም እፅ ስለተቃጠለባቸው እንግሊዞች ተበሳጩ። ጦርነት ለመክፈት ዝግጅት አድርገው በቻይና ላይ ዘመቱ። ዋና ዋና የሆኑትን የቻይና ወደቦችና ከተሞች  በተለይም የካንቶንን ጠቅላይ ግዛት በወታደራዊ ዘመቻ ተቆጣጠሩ። በቀላሉም በቻይኖች ላ ወታደራዊ የበላይነትን አሳዩ። ያገኙትን ወታደራዊ የበላይነት በመጠቀም የቻይናን ንጉሥና መሳፍንቶችን አስፈራርተው ከቻይና ጋር  የውዴታ ግዴታ ውል ተፈራረሙ። በዚህ ውል መሠረት ቻይና ወደቦቿን ለእንግሊዝ ክፍት ለማድረግ ተስማማች።  እንደገናም በዚህ ውል መሠረት እንግሊዝ ለተቃጠለባት ኦፒየም ቻይና ስድስት ሚሊዮን ዶላር በብር (silver) እንድትከፍል ተስማማች፡ ከዚህም ሌላ ቻይና የእንግሊዝ ነጋዴዎችን በቻይና እንዳይነግዱ ስለከለከለች በዚህ ምክንያት የእንግሊዝ ነጋዴዎች  ለደረሰባቸው በደል ካሣ ሶስት ሚሊዮን ዶላር ቻይና ለእንግሊዝ እንድትከፍል፣ በተጨማሪም እንግሊዝ በጦርነት ላወጣችው ወጭ ቻይና አስራ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ካሣ ለእንግሊዝ እንድትከፍል በውዴታ ግዴታ ተስማማች። 
                         
ምስል - "ምእራባውያን ቻይናን ሲቀራመቱ" አንድ ሰዓሊ እንደገለጸው።
በተጨማሪም በዚህ ውል  ቻይና  የሆንግ ኮንግን ደሴት ካሣ አድርጋ ለእንግሊዝ እንድትሰጥ በውሉ ተገደደች። ከዚህ ጊዜ በኋላ በፈረንጆች አቆጣጠር በ፲፰፻፺፰ .. (1898) የማሻሻያ ውል ተደርጎ ሌሎችም መሬቶች ተጨምረው ለእንግሊዝ ለዘጠና ዘጠኝ አመት እንዲሰጡ የውዴታ ግዴታ ስምምነት ተደረገ። በተከታታይም ፈረንሳይና ሌሎችም ምእራባዊ  አገሮች  ያልተመጣጠነ ተመሳሳይ ውል ከቻይና ጋር ተፈራረሙ። ከእንግሊዝ ጋር ስለሆንግ ኮንግ የተደረገው ውል ፺፱ (99) ዓመት ያለቀው በ፲፱፻፺፯ .. (1997) ነበር። ይህ ጊዜ ሲያልቅ ቻይና አጎልብታ ስለነበር በልዩ አስተዳደር ስምም ቢሆን ሆንግ ኮንግን መልሳ አገኘች።"
ይህ የሆንግ ኮንግ ሰው ከዚህ በላይ ያለውን ታሪክ ሲያጫውተኝ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ታሪክ እንደተሰራ አስታወሰኝ።  ምእራባውያን ኢትዮጵያን በሁሉም አቅጣጫ በመክበብ አስጨንቀው ህዝቦቿን እንዴት እንደከፋፈሉ፣ ወደቦቿንም እንዴት እንደተቀራመቱ ብዙ ሰው በግልጽ የሚያውቀው ታሪክ በመሆኑ በዛ ላይ ጊዜ ሳላጠፋ ለወገኖቼ ለማካፈል ከዚህ የማቀርበውና ይህ የቻይና ሰው ትረካ ያስገነዘበኝ ዋና ነጥብ እሱም የኦፒየምን ሚስጢር ነው።  
ኦፒየም በየዓይነቱ በኢትዮጵያ።
   
       ክንችር
 ብሎ የተዘጋውን የቻይና በር በርግዶ ለመክፈት ያበቃቸውና የቋመጡለትን የቻይናን ጥሬ ሃብትና ምርት እንዳሻቸው ለመዛቅ ያስቻላቸውን ኦፒየም ምእራባውያን ወደ ጎን አልጣሉትም። እነዚህ ሰዎች በባህላቸው አርኪ ውጤት ያገኙበትን ብልሃት እንዲያውም ያሻሽሉታል እንጂ አይረሱትም። አመርቂ ትርፍን ከገበዩበት ከቻይና ሙከራቸው በኋላ ምእራባውያን የኦፒየምን ሚስጢር በብዙ በተራቀቀ መንገድ በዓለም ላይ አሁንም ይጠቀሙበታል። ኢትዮጵያ ደግሞ የዚህ የተራቀቀው የኦፒየም ጨዋታ ዋና ሰላባ ከሆነች ሰንብታለች።

እንግሊዞች ብዙ የቻይና ሰዎችን ኦፒየም የሚሹ የኦፒየም ሱሰኞች ያደረጉበት ምክንያት የቻይናን ጥሬ እቃዎችና ምርቶች ብዙ ገንዘብ ሳያወጡ ለማግኜት ሲሉ  ነበር። ዛሬም እንደትናንትናው፥ እንዲያውም ከትናንትናው በበለጠ ጉጉት፥ ምእራባውያን ጥሬ ሃብቶችን ይሻሉ። አሁንም እንደ ትናንትናው እነዚህንም ጥሬ ሃብቶች ለማግኜት የሚሹት ወጭን ሳያወጡ ነው። ወጭ ሳያወጡ የሌሎችን ሃብቶች መውሰድ የሚችሉት ደግሞ ጥሬ ሃብት የሚፈልጉባቸውን ሰዎች በቻይና እንዳደረጉት አእምሯቸውን በማደንዘዝ ወይም በመበከል ነው። አእምሮን ከጥቅም ውጭ ለማድረግ ደግሞ ለቻይና ካዘጋጁት ኦፒየም የሚበልጡ ብዙ አይነት የአእምሮ ማኮላሻ እርሾዎችን አዘጋጅተዋል። እነዚህንም እርሾዎች በመጠቀም የፈለጉትን በር ይከፍታሉ፣ የሚፈልጉትን ጥሬ እቃም ሆነ ሃብት በነጻ ወይም በወደቀ ዋጋ  እንደፈለጉ ይዝቃሉ። ለመሆኑ እነዚህ ዘመናዊ ኦፒየሞች ምንድን ናቸው?

ምእራባውያን ካዘጋጇቸው ዘመናዊ ኦፒየሞች ውስጥ ፍልስፍና፣ ርእዮተ ዓለም ከጦር መሣሪያ ጋር፣ ምእራባዊ ባህል፣ ምእራባዊ ርእዮተ ዓለም፣ ምእራባዊ እምነት፣ ፍሬ የማይሰጡ ሸቀጦች፣ ማዳበሪያ፣ ዶላር፣ ፓውንድ ወዘተ አንዳንዶቹ ናቸው። ቻይናን ለማደንዘዝና ህዝቦቿንም ለመከፋፈል ምእራባውያን ጥቂት ወጪን አውጥተዋል። ሕዝቦቿን ለማስከርና ኢትዮጵያን ለመከፋፈል ምእራባውያን የተጠቀሙት ኦፒየም ብዙ ወጪን አላስወጣቸውም። ኢትዮጵያን ለማመስ የተጠቀሙት  ብልሃት ኢትዮጵያውያንን በፍልስፍናዎችና ከአንድነት ማህበር በሚለዩ እምነቶች አእምሯቸውን ዋልጌ ማድረግ ነበር።   የምእራብ ሰዎች ቻይና ውስጥ የተጠቀሙት አንድ ኦፒየም ብቻ ስለነበር ቻይና ተንገዳግዳም ቢሆን እንደገና የመቆም እድል አገኜች። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ኦፒየምን በተራቀቀ መንገድ በብዙ መልክ በየአይነቱ ስላስገቡት በኢትዮጵያ የተፈጠረው ደዌ  እና የደረሰው ጉዳት ከባድ ነው።

የምእራባውያን ፍልስፍናና ርእዮተ ዓለም መጀመሪያ ሲያዩት ማራኪ፣ ሲቀምሱት ጣፋጭ ሆኖ  ነበር ለኢትዮጵያውያን የቀረበው። ፍልስፍናዎቹን ቀምሰው የፍልስፍናዎቹ ምርኮኛ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን በጣም ጥቂት ነበሩ። ፍልስፍናዎቹና ርእዮተ ዓለሞቹ  ኢትዮጵያውያንን ሱሰኛ ማድረግ ብቻ ሳይሆን እንዲያውም ቅምሻው እየጨመረ ሲሄድ ሁሉንም  ከሱሰኝነት ወደ እብድነት አሸጋገሩ። ድሮ አንድ ኢትዮጵያዊ በአስራ አምስት አመቱ በሬ ጠምዶ ያርስ ነበር። እህልም ዘርቶ ያጭድ ነበር። ወገኑንም ይመግብ ነበር። አቅሙ ገና ከሆነ ደግሞ ወይ ከብት ያግዳል፡ ወይም እግዚአብሔርን በማመስገን ሥራ ላይ ይሰማራል። ቁምነገር ክብር የሚሰጠው ስነምግባር ነበር። ይህን የማያደርግ ወጣት አልነበረም። አልፎ አልፎ ከነበረ ደግሞ እንደዚህ አይነቱ ዋልጌ ተብሎ ይጠራል። ምናልባትም ያን ጊዜ ዋልጌ ሊኖር የሚችለው ዋልጌው የአእምሮ ህመምተኛ ቢሆን ነው። አሁን ግን የምእራባውያን ትምህርት  ኢትዮጵያውያንን በዋልጌነት ስላሰለጠነ ዘመን ተገላብጦ ዋልጌነት በቁምነገር ላይ የበላይነትን ተጎናጽፏል። በሬ አጥምዶ ማረስ ወይም ከብት መጠበቅ፣ ወይም እግዚአብሔርን በንጽህና ማገልገል ፈላጊ የሌላቸው  የተናቁ ሙያወች ሲሆኑ፤ ወገንን በማጭበርበር እራስን ማድለብ የሚደነቅ ቅልጥፍና ተብሎ ተወድሷል። ጫት እየቃሙ ስለ ሊበራሊዝም መደስኮር ወይም ስለ ግሪክ ፋላስፎች ማላዘን ወይም ስለ እንግሊዝ ኳስ ተጫዋቾች ሲያወሩ ውሎ ሲያወሩ ማደር  ክብር የሚሰጣቸው ምግባሮች ሆነዋል፣ ስልጣኔ እየተባለ የሚጠራው አዲሱ ባህልም ይሄው ነው። በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ከትልቅ እስከ ትንሽ፣ ከአገር አስተዳዳሪ እስከ ቸርቻሪ ድረስ በዋልጌዎች ወይም በዘመኑ ኣጠራር ማክሰርን እንጅ ማበርከትን በማያውቁ ዱርየዎች የተጨናነቀች አገር ሆናለች።   

የዋልጌነት፡
 ግብሮች።

     በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አንድ ዱርየ ካለ ይህ ዱርየ ቤተሰቡ በሚኖሩበት ቤት ውስጥ ሥራው ምንድን ነውዱርየው በሬ ጠምዶ፣ አርሶ፣ አጭዶና ከምሮ ወደ ጎተራ የሚገባ እህል ወይም ምግብ ወደ ቤቱ ይዞ አይመጣም።  ሃሺሽ ወይም መጠጥ ለመግዣ ቤት ውስጥ ያለውን እቃ እያወጣ ይሸጣል። ቤት ውስጥ ያለ ወርቅ፣ ብር፣ ቅርሳ ቅርስ፣ ልብስ፣ እህል፣ ወንበር፣ ጠረጴዛ ሁሉ አይቀረውም።  ገንዘብ ካለም ይሰርቃል። ቤተሰቦቹ የሚበሉት እስኪያጡ ድረስ የሚኖርበትን ቤት ያራቁታል። ቤተሰቦቹ ቢራቡ፣ ቢጠሙ፣ ቢታረዙ ዱርየው ግድ የለውም። ትንሽ ቆይቶም ዱረየዎቹ ጓደኞቹ የሃሰት የቤት ባለቤትነት ማስረጃ ወረቀት ያዘጋጁለትና የቤተሰቦቹን ቤት ይሸጣል። ቤተሰቦቹም ማደሪያ ያጣሉ። እሱም ማደሪያ አይኖረውም።

ኢትዮጵያ በተለይም ካለፈው ምእተ አመት ጀምሮ በዚህ አይነት አኗኗር በመታመስ ላይ ትገኛለች። የአንድ ዱርየ የጥፋት ሥራ አንድን ቤተሰብ በሙሉ ከመልካም ኑሮ ውጭ ካደረገ አንዲት አገር ቁጥር ስፍር የሌላቸው ዱርየዎችን ይዛ  ልትኖር ትችላለችን? ከማራኪነቱ የተነሳ በምእራባውያን የተነደፈውን የኢትዮጵያ ትምህርት ያለጥያቄ ከመጎንጨት አልፎ ቀረብ ብሎ በአትኩሮት የሚመረምረው ጠፋ እንጂ፤ በእውን ቢመረምሩት ትምህርቱ በየቀኑ ብዙ ዱርየዎችን እያፈራ ኖሯል። ከዚህ ዋንጫ የተጎነጨ ሰው እግዚአብሔር በፈጠረለት ዓለምን በሚያይበት አይኑ ላይ የምእራባውያን መነጽር ተደንቅሯል። መነጽሩም የቀረበው በፍልስፍና ወይም በርእዮተ ዓለም መልክ  ነው። ይህ መነጽር የአስተሳሰብ በሺታ ውይም እብደት ነው፥ ኢትዮጵያዊነትንና ለኢትዮጵያ የሚገኝ ጥቅምን ያስጥላል።  ለመረጃ ያህል ይህን ምእራባዊ መነጽር ከኢትዮጵያዊ አይን ጋር በጥቂት ምሳሌዎች እናነጻጽር።

በኢትዮጵያዊ ትምህርት ኢትዮጵያ የተመረጠች የእግዚአብሔር አገር ናት። እግዚአብሔርን ማገልገል ዋነኛ ሥራዋ ነው። እግዚአብሔርን የሚያገለግል ሕዝብ ደግሞ በግብሩ እግዚአብሔርን መምሰል ይኖርበታል።

በምእራባዊ ትምህርት እግዚአብሔር የለም፣ ኢትዮጵያም በአፍሪካ ውስጥ ያለች ሺፍታዎች በማስገደድ የተቆጣጠሯቸውን የተለያዩ ሰዎች ሰብስበውና እራሳቸውን ንጉሥ አድርገው  አገር ብለው የጠሯት ቦታ ናት። ልክ እንደሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች ደግሞ የራሷ የሆነ ስልጣኔ የላትም። ስለጣኔው የመጣው ከአርቦችና ከምእራባውያን ነው።

በኢትዮጵያዊ ትምህርት ላሊበላ የተሠራው ለዳግማዊ ኢየሩሳሌም ተምሳሌትነት በእግዚአብሔር ትእዛዝና  በመላእክት እርዳታ ነው። ዳግማዊ ኢየሩሳሌም ላሊበላ የሚያሳየው የኢትዮጵያውያን ኃይል እግዚአብሔር መሆኑን ነው።

በምእራባዊ ትምህርት መሠረት ላሊበላ በየትኛውም ቦታ ማንም የሌላ አገር ሰው እንደሚሠራው አይነት የተራራ ሥር ዋሻ ነው። ጥቁሮች ላሊበላን የሚያህል ሥራ ለመወጠንም ሆነ ሥራውን ለማከናወን የሚያበቃ የአእምሮ ትጋትና ታታሪነት ስለሌላቸው ምናልባት ላሊበላን የሠሩት ታሪካቸውን በጽሁፍ ያልተው ምእራባውያን ሳይሆኑ አይቀሩም።

በኢትዮጵያዊ ትምህርት በትጋት በማረስና በመሥራት ለቀለብ የሚሆንና አገርን የሚመግብ ምርትን ማምረት ያስፈልጋል። ይህን እህል በጎተራ በማስቀመጥ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ተካፍሎ አብሮ መብላት መልካም ነው።

በምእራባውያን ትምህርት የብልጽግና ጎዳና ማለት ኢትዮጵያውያን ካላቸው ጥሬ ሃብት ምርጡን እህል፣ ምርጡን ቡና፣ ምርጡን ሰንጋ፣ የሁሉንም ነገር ምርጥ ምርጡን ወደውጭ አገር መላክ ሲችሉና በምትኩ ብዙ ዶላር ሲያስገቡ ነው። ዶላሩ ነዳጅ ይገዛል፣ የመኪና መንገድ ይሠራል ውጭ አገር ያንሸራሽራል።

በኢትዮጵያዊ ትምህርት ድር ቢያብር አንበሳ ያስራል። ኢትዮጵያ አንድ አገር ሆና መኖሯ ለኢትዮጵያውያን ብዙ ጥቅምን ይሰጣል። ሠርቶ ለማደር፣ ቤት ለመስራት፣ ልጆችን ወልዶ ለማሳደግ፣ ፈጣሪን ለማመስገን፣ከጉልበተኛ ጥቃት ለመዳንና ለሌሎችም ብዙ መሠረታዊ ጉዳዮች የአገር አንድነት ጥቅም አለው።

በምእራባዊ ትምህርት (ምእራባውያን እራሳቸው ሳይፈልጉት ሌሎችን አድርጉ እያሉ እንደሚያስተምሩት) ጥቅም ያለው የአገር አንድነት ሳይሆን እያንዳንዱ ጎሳ የራሱን የጎጥ መንግስት ማቋቋም ሲችል ነው። እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ ምእራባውያን የሚፈልጉትን ሃብት ከፈለጉት ሠፈር ያለወጪ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።

የኢትዮጵያዊ ትምህርት ዓላማ ኢትዮጵያዊው ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲያድርበት በዚህም ምክንያት ክፉ ከመሥራት፣ ከመስረቅ፣ ከመግደል፣ ፍርድን ከማጓደል እንዲርቅ ማድረግ ነው። በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ባንድ ላይ ሆነው እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ፣ እርስ በርስ እንዲፈቃቀሩ፣ አገራቸውን በጋራ እንዲጠብቁ፣ ሁሉም ሰው ግብረገብነት  ያለው ንቁና ትጉህ ኢትዮጵያዊ እንዲሆን ነው።

የምእራባዊው ትምህርት አላማ ኢትዮጵያዊውን የዓለም ጉልበተኞች አላማ ተገዢ (global citizen) እንዲሆን ማድረግ ነው። በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያዊው ባህሪውም ሆነ ምግባሩ ለውጭ አገር ሰዎች ፍላጎት ተገዢ፣ ምርቱም የውጭ አገር ሰዎችን ብቻ የሚመግብ እንዲሆን፣ ኢትዮጵያ የምትኖረውም ለምእራባውያን ጥቅምን ለመስጠት ብቻ እንዲሆን ማድረግ ነው።   
፩ኛ ሰንጠረዥ - የኢትዮጵያዊቷ ከአመት አመት ዶሮ የመግዛት አቅም ሰንጠረዥ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር።
  
ከላይ ከመግቢያው እንዳየነው ኢትዮጵያውያን ከእግዚአብሔር መንገድ ከተለዩ የድካማቸውን አዝመራ አይናቸው እያየ የውጭ አገር ሰዎች ይበሉባቸዋል ተብሎ በመጽሐፍ እንደተጻፈ እነሆ በአሁኑ ሰዓት አንድ ኢትዮጵያዊ ዶላር እንኳን ይዞ ቡና ሊገበይ ወደ ገበያ ሲወርድ አንድ ኪሎ ግራም የቆሸሸ ቡና ለመግዛት ቢያንስ ሰባት ዶላር ያስፈልገዋል። የውጭ አገር ሰዎች አገራቸውን ሳይለቁ  አንድ ኪሎ ግራም ምርጥ ቡና  ከኢትዮጵያ ሲገዙ ለኢትዮጵያውያን የሚሰጡት ሁለት ዶላር ከከሃምሳ ሳንቲም ነው  [አንዳንድ ጊዜም የሚሰጡት እስከ ዘጠና ሳንቲም ዝቅ ይላል።[በዚህ ላይ የውጭ አገር ሰዎች የሚወስዱት እጅግ  ምርጥ ምርጡን ነው። ብር በዶላር ፊት የበለጠ እየወደቀ ሲመጣ ደግሞ የውጭ አገር ሰዎች  አንድ ኪሎ ምርጥ ቡና ለመውሰድ ለኢትዮጵያውያን በእርግጥ የሚሰጡት ከአምሳ ሳንቲም ያነሰ እየሆነ ነው የሚመጣው። ይህን  ከውጭ ሰዎች ጋር የሚደረግ ያልተመጣጠነ ግንኙነት በማየት ኢትዮጵያ  በዚህ በምእራባውያን "የነጻ" ገበያ ፍልስፍና መንገድ ስትጓዝ ኢትዮጵያውያን እየተራቡና እየጠወለጉ፣ የኑሮ አዘቅት  ውስጥም እየገቡ እንደሆነ ማየት አያዳግትም። 
ከላይ በሰንጠረዡ እንደምናየው ኢትዮጵያዊቷ ዶሮም ሆነ ሌሎች ለኑሮ የሚያስፈልጓትን እቃወች ለመግዛት የሚያስፈልጋት የብር መጠን በድንገት እንዳሻቀበ እናያለን። የውጭ አገር ሰዎች ግን ውጭ አገር ሆነው ዶሮ ከኢትዮጵያ ማስገባት ቢሹ እንዲያውም ከድሮው ባነሰ ዋጋ ነው ዶሮውን የሚያገኙት። ይህ የሆነው በሁለት ምክንያቶች ሊሆን ይችላል።  አንደኛው ምክንያት  በኢትዮጵያ አሁን ያለው አስተዳደር ድንገተኛ የገንዘብ ማባዛት ማድረጉ ነው። []ሁለተኛውና ያነሰው ምክንያት ደግሞ ብር ክዶላር ጋር ያለው የልውውጥ አቅም እንዲቀንስ መደረጉ ነው።  ገንዘብ ማባዛት ምን ማለት ነው? ለምሳሌ በአንድ ሰፈር ውስጥ አሥር ዶሮዎች፣ አሥር ሰዎችና አሥር ብር አለ እንበል።  ዶሮዎቹን ለመግዛት ያለው ጠቅላላ ገንዘብ አሥር ብር ብቻ ስለሆነ የአንድ ዶሮ አማካይ ዋጋ አንድ ብር ቢሆን ነው። አንድ የሰፈር ጉልበተኛ ተጨማሪ ሰላሳ ብር ቢያትምና  በሰፈሩ ቢበትነው አሁን አርባ ብር፣ አሥር ዶሮዎችና፣ አሥር ሰዎች  በሰፈሩ ውስጥ ስላሉ የአንድ ዶሮ ዋጋ በአማካይ አራት ብር ይሆናል። አሁን ብሩ ስለበዛና እንዲህ አይነት ብር በጉልበተኞች ወይም በዘራፊዎች እንደተፈለገ በሚታተምበት አገር ውስጥ ደግሞ ትርኢተኞች ስለማይጠፉ የተባዛው ብር እኩል ለሁሉም አይከፋፈልም። ስለዚህ ከነዚህ አሥር ሰዎች ውስጥ ሁለቱ ብልጦች ሆነው ሌሎችን አደንዝዘው ብራቸውን በመንጠቅ አስራ ስድስት አስራ ስድስት  ብር ወደ ኪሳቸው አስገቡ እንበል። አሁን ለብልጦቹ አንዳንድ ዶሮ ስለሚያንሳቸው አራት አራት ዶሮዎች ይገዙና  ሁለት ዶሮዎች ገበያው ላይ ይቀራሉ። የቀሩት ስምንት ሰዎች የቀረችውን ስምንት ብር ሲከፋፈሏት አንድ አንድ ብር ይደርሳቸዋል። በመዘዋወር ላይ ያለው የብር መጠን ከድሮው ስለበዛ በአንድ ብር ዶሮ መግዛት አይቻልምና ዶሮውን ትተው ሽሮ ፍለጋ ይሄዳሉ። ሽሮም ካልተገኘ ጦማቸውን ያድራሉ። ለኛ ኢኮኖሚክስ የሚባለውን የባእዳን ትምህርት ላልተማርን ሰዎች የሚገባን የኢትዮጵያውያን የአሁኑ ዘመን አኗኗር አጭር አገላለጽ ይህ ነው። ኢትዮጵያውያን ዶሮውን ያያሉ ከዶሮው ግን አይበሉም። ያማረው ቡና ተጭኖ ወደውጭ ሲላክ ያያሉ፣ እነሱ ግን የሚያምረው ቡና ይቅርና በአጃክስ ሳሙና ካልታጠበ የማይጠራውን ቡና እንኳን አያገኙም። ዶላር እየተባለ የሚጠራው የወረቀት ኦፒየም እጅግ ሱስ ከማስያዙ የተነሳ ለሱ ሲባል የማይሸጥ መሬት፣ የማይሰራ ወንጀል፣ የማይፈርስ ገዳም የለም። የውጭ አገር አዛዦች አንድ ዶላር በሶስት ብር መቀየሩ ቀርቶ በአስራ ሰባት ብር ይቀየር ሲሉ ትእዛዛቸው ይፈጸማል። እንዲያውም በማናለብኝነት ብር እንደተፈለገ  የሚታተምበት አንዱ ምክንያት ከውጭ አገር የሚገኘውን ዶላር ለመሰብሰብ ሳይሆን አይቀርም።


፪ኛ ሰንጠረዢ  - እንደ ኢትአቆጣጠር በ፳፻፬ (2012 Euro. Cal) የገበያ ዋጋ። [] 
ለዶላር ሲባል እህል የሚያበቅለው መሬት አበባ ይዘራበታል። ለዶላር ኢትዮጵያውያን በግብርና ሊሠማሩባቸው የሚችሉ መሬቶች ለውጭ አገር ሰዎች ይሰጣሉ። ለዶላር ገዳማት ይፈርሳሉ። ለዶላር ኢትዮጵያውያን ይራባሉ። አሁን በኢትዮጵያ ከምንም ነገር የበለጠ የሚፈለገው ኦፒየም ዶላር ስለሆነ፣ ኦፒየሙ ዶላርም ሱስ እንዳስያዘ ስላወቀው በዋዛ ኢትዮጵያ አይደርስም። ዶላር ኢትዮጵያ ሲደርስ ከሰብል ምርጥ ምርጡን፣ ከሰንጋም ምርጥ ምርጡን፣ ከወርቅም ምርጥ ምርጡን መጀመሪያ ወደ ውጭ አሻግሮ ነው። ከላይ ያየነው ዱርየ ለመጠጥና ለሃሺሽ የቤተሰቦቹን ነብረት እያወጣ እንደቸረቸረው ሁሉ በአደንዛዡ ምእራባዊ ትምህርት አእምሯቸውን የሳቱና እስከ ስልጣን ኮሪቻ ድረስ የደረሱት የኢትዮጵያ ዱርየዎች ኦፒየሙን ዶላር ለማግኜት ሲሉ ምርጥ ምርጡንና ብዙውን ጠቃሚ የኢትዮጵያ ንብረት  ወደውጭ ስለሚያሻግሩት  ኢትዮጵያዊው አገር ውስጥ የቀረ ለመብልና ለመጠጥ የሚሆን ሰብል፣ ለቁም ነገር የሚሆን  ሃብትም የለውም። ሌላው ቀርቶ  አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ጊዜ ዘጠና ከመቶ የሚሆኑት በቀን አንድ ጊዜ እንኳን የሚበሉት የሌላቸው ረሃብተኞች ናቸው።  


ለመሆኑ ዶላር አገር ውስጥ ገብቶ ምን ይሠራልዶላር እንደ ብር ወረቀት ነው። አይበላም፣ አይጠጣም ወይም አይለበስም። ዶላር ከውጭ አገር  ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ኢትዮጵያ ውስጥ ልገዛው የምችለው ምን ምርት አለ? ወይም  ምን ጥሬ  እቃ አለ? ብሎ ነው። 
ምስል  - ምእራባውያን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሚያደርጉትን የርቀት ምጥመጣ አንድ ሰአሊ እንደገለጸው።
ሊገዛ የመጣበትም ምክንያት ኢትዮጵያውያንን ለመመገብ ወይም ጥማታቸውን ለማርካት ሳይሆን የውጭ

አገር ሰዎችን ለመመገብ፣  ወይም ጥማታቸውን ለማርካት ነው። ዶላር ኢትዮጵያ ውስጥ  ገብቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ከቀረ ወይም ወደ ውጭ አገር ተመልሶ ከውጭ አገር ጠቃሚ ምርት ገዝቶ ያን ምርት ወደ ኢትዮጵያ ካላስገባ ዶላር ለኢትዮጵያ የውድቀት ምንጭ የሆነ ኦፒየም ነው። ዶላር ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በውጭ አገር ጉልበት ስለፈሰሰበት የውጭ አገር ሰዎችን አገልግሎ ሥራውን ፈጽሟል። ኢትዮጵያ ምርት ወይም ጥሬ እቃ ገዝቶ ያን ምርት  ወደ ውጭ አገር ሲያሻግር ደግሞ ዶላር ለውጭ  አገር ጨማሪ ጥቅምን ሰጥቷል። 

አሁን  ይህን ዶላር ይዞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያስቀረ ሰው ዶላሩን ይዞ ወደ ውጭ አገር ቢመጣና ውጭ አገር በዚህ ዶላር ቤት ገዝቶ መኖር ቢጀምር ይህ ሰው በኢትዮጵያ ላይ ትልቅ ጉዳትን አድርሷል፤ ምክንያቱም በሂሳቡ ስሌት ኢትዮጵያ ልጆቿን አስርባ ምርጥ ጥሬ ሃብቷን ወይም ምርቷን  ለውጭ አገር ሰዎች በነጻ አደለች እንደማለት ነው። በዚህ ግብይት ለሷ ለራሷ የቀረ ምንም ንብረት ወይም ፍሬ የለም።   እንግዲህ ዶላር በኢትዮጵያ ያለው ታሪክ ይሄው ነው። ዶላር በስሙ ከኢትዮጵያ ብዙ ቡና ወይም ብዙ ሰንጋ ወይም ብዙ ለዘይት የሚሆን የዘር ፍሬ ወይም ብዙ ማር ይወስዳል፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ ሃብት ከኢትዮጵያ ካጋፈፈ በኋላ ወደ ውጭ አገር ተመልሶ ሊትዮጵያ የሚሆን ፍሬን ሳይገበይ ውጭ አገር ይቀራል። የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች እየተባሉ በውጭ አገር የሚኖሩ የሚወስዱት ይህንኑ ዶላር ነው። በዶላሩ የሚገበዩትን ሁሉ የሚያስቀሩት እዛው ውጭ አገር ነው። በውጭ አገር የሚኖሩ ጆሮ ጠቢዎችም የሚወስዱት ይህንኑ ከኢትዮጵያ ብዙ ሃብት የሟጠጠውን ዶላር ነው። እነዚህ ጆሮ ጠቢዎች ይህን ዶላር በውጭ አገር ቢራና ውስኪ ይራጩበታል። ወይም ብዙ ሃብት የሟጠጠው ዶላር በዋሺንግተን ዲሲ ሎቢይስቶች ይቀጠሩበታል። ሎቢይስቶቹም ለኢትዮጵያ የሚያስገኙት አንድም ፍሬ የለም፣ ነገር ግን የሚውጡት ገንዘብ ቁጥር ስፍር የለውም። ዶላር ትንሽ የሚጨበጥ ነገር አምጥቷል እንኳን ቢባል  የሚጨበጠው ነገር እራሱ ሌላ ኦፒየም ነው።   ለምሳሌ ማዳበሪያ። ኢትዮጵያውያን  ምርት እያመረትን ብዙ ጥቅም ለማይሰጥ ገቢ ለውጭ አገር ሰዎች መላካችን ጎድቶናልና የምናመርተውን እራሳችን እንብላ እንዳይሉ ደግሞ ማዳበሪያ በሚባለው ኦፒየም ተይዘዋል። ዶላሩን ገብይተው ማዳበሪያ ካልገዙበት መሬቱ እራሱ የኦፒየም ሱሰኛ ሆኗልና እህል አያበቅልም። ሌሎችም በዶላር የሚገበዩ ብዙ ነገሮች እንዲሁ የኦፒየም ባህሪ ያላቸው ውጤቶች ናቸው።   እንደ ቻይና የተሟላ ምርት ያላት እራሷን የቻለች አገር እንዳትሆን ደግሞ ምእራባውያን ፍልስፍናቸውና ሰላዮቻቸውን፣ አረቦች ደግሞ ኃይማኖታቸውን ተጠቅመው ሁለቱም በኢትዮጵያ ላይ በመተባበር ህዝቦቿን አለያይተዋል፤ ገነጣጥለዋታልም። ያለወደብም አስቀርተዋታል። ታዲያ ምን ይሻላል?

በኦፒየም ሱስ መያዝ ከባድ በሺታ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አፈሩ ሳይቀር በሱስ ተይዟል። ከዚህ ሱስ ለመላቀቅ መንገድ አለ ነገር ግን ጥበብ ያስፈልገዋል። ጥበበኛ መሪም ያስፈልጋል። ታዲያ ጥበበኛ መሪ እግዚአብሔር ነውና ኢትዮጵያውያን ሳንውል ሳናድር ጣሊያን ኢትዮጵያን ልትውጥ ስትገሰግስ አድዋ ላይ ከግድግዳ ጋር ወዳላተማት፣ ምእራባውያን ኢትዮጵያን ለመጉረስ ቋምጠው በጣሊያን ለማስያዝ በሸረቡ ጊዜ ለኢትዮጵያ ሲል በተንኮለኞቹ ሸራቢዎች ላይ ጦርነትን እንደበረዶ ወደ አወረደባቸው   ወደ ጥበበኛው መሪያችን፣ ወደ ሃያሉ ንጉሥ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ። እሱ የበይ ተመልካች ሳያደርገን ጓሯችን የሚያፈራውን ፍሬ፣ የሰባውንም ሰንጋችን ለኛ ያደርገዋል። ከምንጫችንም የሚፈልቀውን ውኃ ያጠጣናል።

ሰለ ቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ፣ ስለ ቅዱሳን መላእክት ልመና፣ መንገዱን ሰለጠበቁ ስለቀደሙ አባቶቻችን ጸሎት፣ ስለ ቅዱሳን ሰማእታትም ሲል እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይታረቃት። አሜን።

ሙሉጌታ።
ሐምሌ  ቀን ፳፻፬ . .
_________________________________________________________

 [
ክብረ ነገስት። ፵ወ፩ በእንተ በረከተ ነገሥት።
 [
]ኦሪት ዘዳግም ፳፰ ፴፩
 [
] Index Mundi data portal
 [
የኢትዮጵያውያን አማካይ ገቢን፣ የእቃወች ዋጋ፣ የዶላርና የኢትዮጵያ ቁሳቁሶችን በተመለከተ ምንጮቹ የሚከተሉት ናቸው
         http://nazret.com/2008
         http://www.ezega.com
         http://www.numbeo.com
         ftp://ftp.fao.org (poultry sector country review)
         http://www.businessweek.com/news/2012
 []PM Meles Zenawi quoted by Tadesse Kuma, Dynamics of Food Prices in Ethiopia, 24 May 2012
 
[] ከካፒታል ጋዜጣና Index Mundi  ዘገባዎች የተጠናቀረ ሰንጠረዥ

     ከላይ
 በመጠኑ የሰፈሩትን ማነጻጸሪያወች በማየት የምእራባውያን ትምህርት ኢትዮጵያዊውን ከእግዚአብሔር ጸጋ እንዴት እንደለየው እናያለን። በውጭ አገር ትምህርት አእምሮው በመደንዘዙ ምክንያት ኢትዮጵያዊው ከእግዚአብሔር ጸጋ መለየት ብቻ ሳይሆን እስኪናቅ ድረስ፣ እስኪጠላ ድረስ፣ የሚበላው እስኪያጣ ድረስ፣  እግዚአብሔር የፈጠረለትን መሬት፣ ውኃ፣ የመሬቱን ፍሬዎች ሁሉ አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ፣ ከነዚህም ከውጭ አገር ሰዎች ተመጽዋች እስኪሆን ድረስ ተዋርዷል።  የምእራባዊ ፍልስፍና ተማራኪ የሆነ ሰው እኔ እና ወገኖቼ እንዲህ አይነት የወደፊት ተስፋ አለን ብሎ መናገር እንኳን አይችልም። ይህ ሰው ሁልጊዜ የሚቀጥለው ቀን አዳሩ እንዴት እንደሚሆን ምእራባውያን እንዲነግሩት ይጠብቃል፣ እየጠበቀም ያንቀላፋል። ለራሱም ሆነ ለወገኖቹ ክብር የለውም። እራሱን እና ወገኖቹን ተስፋ የሌላቸው፣ በተፈጥሮ ስጦታ ማነስ ምክንያት በአስተሳሰብ የተበደሉ አድርጎ ይመለከታል። ኢትዮጵያዊ ደካማ ነውና ፍልስፍናና አስተሳሰብ፣ የመንገድንም አኪያሄድ ሁሉ መዋስ ያለበት ከምእራባውያን ነው ብሎ ያምናል። እንደዚህ አይነት ሰዎች ደግሞ በኢትዮጵያ ስለበዙ በስልጣን ኮሪቻ ላይ እስከመቀመጥ ደርሰዋል። እንደተማሩትም ዱቄታቸውን በአመድ ሲቀይሩ እናያለን።

የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ከሚባለው ኦፒየም ኢትዮጵያዊው ያገኜው ነገር ምንድን ነው? ሁሉም እንደሚያውቀው ከእንደዚህ አይነት ፍልስፍና ኢትዮጵያዊው ያገኜው ትርፍ ማጣትን፣ ውርደትን እና ልመናን መጨመር ብቻ ነው። ከዚህ ፍልስፍና ያላነሰ ጥፋት የሚያደርሰው ሌላው ኦፒየም ደግሞ ማንኛውም ሃብትና ንብረት፣ ክብርንም ጨምሮ፡ በዶላር የመቀየር ሱስ ነው። 

7 comments:

  1. Bexame Gerume!!!!!!!!

    ReplyDelete
  2. ሰናይ ውእቱ በጊዜ ኮነ እውነት እልሃለሁ እጅግ ግሩም ነው
    ዲ/ን ጌታመሳይ ሀ/ሚካኤል

    ReplyDelete
  3. ሰናይ ውእቱ በጊዜ ኮነ እውነት እልሃለሁ እጅግ ግሩም ነው
    ዲ/ን ጌታመሳይ ሀ/ሚካኤል

    ReplyDelete
  4. ሰናይ ውእቱ በጊዜ ኮነ እውነት እልሃለሁ እጅግ ግሩም ነው
    ዲ/ን ጌታመሳይ ሀ/ሚካኤል

    ReplyDelete
  5. ሰናይ ውእቱ በጊዜ ኮነ እውነት እልሃለሁ እጅግ ግሩም ነው
    ዲ/ን ጌታመሳይ ሀ/ሚካኤል

    ReplyDelete
  6. ሰናይ ውእቱ በጊዜ ኮነ እውነት እልሃለሁ እጅግ ግሩም ነው
    ዲ/ን ጌታመሳይ ሀ/ሚካኤል

    ReplyDelete
  7. እጅግ ምርጥ ጽሁፍ ነው፤ብስራት እባክህ በዚሁ ቀጥል። ከ አሁኑ እየተወያየን የሱሱን ማርከሻ እንፈልግ።

    ReplyDelete